PHOTO-FILE

[ዋዜማ ራዲዮ]- ቀድሞ በትግራይ ክልል ስር የነበሩና ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ክልል መተዳደር በጀመሩ አካባቢዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ አከፋፈል በየደረጃው ያሉ ሃላፊዎችን አላስማማም። ከመንግሥት ደሞዝ እየተከፈላቸው ካሉት ሠራተኞች መካከል በሕይወት የሌሉ፣ ወደ ሥራ ገበታቸው ያልተመለሱ እና ከአማፂው ሕወሓት ጋር ወደ በረሀ ወርደው መንግሥትን እየተዋጉ ነው የተባሉ ይገኙበታል።

በትግራይ ክልል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ መደበኛው የመንግሥት ሥራ ከሁለት ወራት በላይ ተቋርጦ ነበር። ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መሰየሙን ተከትሎ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀረቧል። አንዳንዶች ወደ ሥራ ሲመለሱ ሌሎች ሕወሓትን ተከትለው “ወደ በረሀ ወርደዋል”። በጦርነቱ ሒደት ቀድሞ በትግራይ ክልል ይተዳደሩ የነበሩ አንዳንድ አካባቢዎችን በኃይል የተቆጣጠረው የአማራ ክልል መንግሥት በያዛቸው አካባቢዎች ላሉ የበላይ አመራሮች (የፖለቲካ ተሿሚዎች) ደሞዝ መክፈል የጀመረው ብዙም ሳይቆይ ነው። ለበታች ሠራተኞች ደግሞ በትግራይ ክልል መንግሥት በኩል ከፌደራሉ መንግሥት በጀት ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው ተደርጓል።

ዋዜማ በደቡብ ትግራይ (አሁን በአማራ ክልል እየተዳደረ ያለው) የፋይናንስና አስተዳደር ሠራተኞችን ጠይቃ እንደተረዳችው ማን በሥራ ገበታው ላይ እንዳለና እንደሌለ ተገቢ ቁጥጥር ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኗል። በጸጥታ ችግር ምክንያት የተረጋጋ የመንግሥት ሥራ ማካሄድ አለመቻሉ የሠራተኞች ቁጥጥርን አዳጋች አድርጎታል። ክልሉ አሁንም ቀድሞ በነበረው የደሞዝ መክፈያ ሰነድ እየተጠቀመ ነው።

የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ካሳ ረዳ ለዋዜማ ራዲዮ እንደገለጹት ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት የመንግሥት ሠራተኞች ሲከፈላቸው በነበረው የገንዘብ መክፈያ (ፔሮል) ዛሬም (የሚያዚያ ወር መጀመሪያ) በተመሳሳይ መንገድ የፌዴራል መንግሥት እየከፈለ መሆኑን ተናግረዋል።

በራያ ግንባር ጦርነት ሲከፈት አካባቢውን ለቀው የወጡ እና በአሁኑ ወቅት የት እንዳሉ የማይታውቁ የአካባቢ አመራሮች ዛሬም በስማቸው ገንዘቡ ወጥቶ በባንክ ደብተር ቁጥራቸው ገቢ እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ ካሳ ለዋዜማ አረጋግጠዋል። ከእነዚህ አመራሮች አንዳንዶቹ ገና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ እና ትጥቅ ይዘው የጠፉ አመራሮች መሆናቸውን ከንቲባው ጠቁመዋል።

ከንቲባው እንዳሉት ይህንኑ በተመለከተ ለፌዴራል የገንዘብ ሚኒስቴር ማስተካከያ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ገልጸው ይሁን እንጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስካሁን ማስተካከል እንዳልቻለ ተናግረዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደ ትንሳኤ መኮነን በበኩላቸው አላማጣ ከተማን ጨምሮ በባላ፣ ዋጃ እና በሌሎች በዙሪያው በሚገኙ ከተሞች እና ወረዳዎች የሚሰሩ የመንግሥት ሠራተኞችን አስመልክተው በሥራ ገበታቸው የተገኙ እና ያልተገኙ በሚል ለመንግሥት በየወሩ ሪፖርት ቢልኩም የቀድሞው የተከፋዮች ዝርዝር አሁንም አልተስተካከለም።

የአማራ ክልል መንግሥት ደመወዝ የሚከፍለው ለፖለቲካ ተሿሚ የበላይ አመራሮች እንጂ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች አለመሆኑን የገለጹት አቶ ወልደ ትንሳኤ በአላማጣ እና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ከፌደራል መንግሥት በቀጥታ በትግራይ ክልል በኩል እንደሚከፈላቸው ተናግረዋል።

በአላማጣ ከተማ አስተዳደር፣ በዋጃ ፣ በጥሙጋ እና በባላ ከተሞች በተለያዩ የአመራር ቦታዎች የተመደቡ የሥራ ሀላፊዎችን ደመወዝ የአማራ ክልል መንግሥት እየከፈለ እንደሚገኝም የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

ቀደም ሲል በጦርነት የደመወዝ ክፍያ ተቋርጦ እንደነበር ያስታወሱት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ካሳ ረዳ የአማራ ክልል መንግሥት ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች የሁለት ወር ደመወዝ መክፈሉን እና የሥራ ማስኬጃ በጀት መድቦ ከተማዋ መንቀሳቀስ መጀመሯን ተናግረዋል።

“ በዚያን ወቅት በሥራ ገበታቸው ያልተገኙ የህወሓት አመራሮችን ተከትለው የጠፉ ግለሰቦችን ለይተን ደመወዝ እንዳይከፈል ማድረግ ችለን ነበር ፤ ይሁን እንጂ በፌዴራል መንግሥት እንዲከፈል መመሪያ ሲመጣ ጫካ ገብተው መንግሥትን የሚወጉ የሕወሓት ታጣቂዎች ሳይቀር በባንክ ቁጥራቸው ደመወዛቸውን እንዲያገኙ ሆኗል” ሲሉ አቶ ካሳ ረዳ ተናግረዋል።

ዋዜማ ራዲዮ ይህንኑ በማስመልከት ገንዘብ ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጣት ጠይቃ ነበር ። የተቋሙ ኮሚኒኬሽን ባለሙያ ገንዘቡ በየወሩ ለትግራይ ክልል ገቢ እንደሚደረግ እና በሥራ ገበታቸው የተገኙትን አጣርቶ ደመወዝ መክፈል ያለበት ክልሉ እንጂ የገንዘብ ሚኒስቴር አይደለም ብለዋል። ስለሆነም የትግራይ ክልል ይህንን ችላ ብሎ በሥራ ገበታቸው ያልተገኙ ሰዎች ደመወዝ እየከፈለ ከሆነ መጠየቅ ያለበት ክልሉ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።

የትግራይ ክልል ፕላን እና ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ካሕሳይ ብርሃነ በበኩላቸው ለዋዜማ እንደገለጹት ከህወሓት ታጣቂዎች ጋር ተከትለው ወደ “በረሀ የገቡ እና በሕይወት የሌሉ ሰዎች ሳይቀር ደመወዝ ይከፈላቸዋል” የሚለውን እስካሁን እንደማያውቁና የተባለው እውነት ሆኖ ከተገኘ ግን በየወረዳው ተመድበው ይህንኑ መቆጣጠር የነበረባቸው አመራሮች ተጠያቂ ይሆናሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]