Mamo Mihretu -FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በቅርቡ በ100 ቢሊየን ብር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በቅርቡ ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ የሰነድ መዋእለ ነዋይ ገበያ (Ethiopian securities exchange) ውስጥ ዋነኛ መዋዕለ ነዋይ አድራጊ እና በገበያው ባለቤትነት ውስጥም የራሱ ድርሻ የሚኖረው መሆኑን የተቋሙ ዋና ሀላፊ አቶ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ። 

ማሞ ምህረቱ ይህን ያሉት በዚህ ሳምንት  ለኢትዮጵያ የሰነድ መዋእለ ነዋይ ገበያ ምስረታ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ኤፍ ኤስ ዲ አፍሪካ ከተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር የትብብር ስምምነት ሲፈረም ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ለሚደረግ ኢንቨስትመንት የረጅም ጊዜ ብድርን ለማግኘት በአይነቱ አዲስ የሆነ የፋይናንስ ገበያ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያ ወደ  ስራ ሲገባም በአፍሪካ 30ኛው ይሆናል ተብሏል።

ገበያውን ወደ ስራ የሚያስገቡ የተለያዩ ቅድመ ስራዎችን የሚያከናውን የፕሮጀክት ቡድንም ከብሄራዊ ባንክ ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እንዲሁም ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ አባላት ተካተውበት ወደስራ ገብቷል። በኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያ ላይ ተሳታፊ ለመሆንም በርካታ አለማቀፍ የዘርፉ አንቀሳቃሾች ፍላጎት ማሳየታቸው ተገልጿል።

ለመሆኑ ለኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ አዲስ ገጽታ የሚሰጠው “የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያ” ምንድ ነው?

የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱን የፋይናንስ ገበያ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልግ ገንዘብ ማግኛ መንገድ ካለው ጉዳይ አንዱ የኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያን(Ethiopia securities exchange market) እንዲቋቋም ማድረግ ነው።ይህ ገበያ ኩባንያዎች የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት አክስዮንና የብድር ሰነዶችን በመሸጥ የሚሳተፉበት ገበያ ሲሆን በጥቅሉም የካፒታል ገበያ ከሚባለው ውስጥ የሚመደብ ነው።

በብዙ ያደጉ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ የሚሰራበት ይህን አይነት ገበያ ለማቋቋም የኢትዮጵያ መንግስት የጀመራቸው ስራዎች አሉት።ባለፈው አመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አዋጅም በሀገሪቱ ለሚቋቋሙ የዚህ አይነት ፋይናንስ ገበያዎች ህጋዊ እውቅናን ለመስጠት እንዲያግዝ ነው። በአዋጁ መሰረት የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የሚል ስያሜ ያለው ተቋም ይኖራል።ባለስልጣኑም እየተቋቋመ ነው።ባለስልጣኑ አዋጁን ተከትሎ በሀገሪቱ ለሚቋቋሙ የፋይናንስ ገበያዎችና በገበያ ውስጥ ለሚሳተፉ አካላት ፍቃድ ከመስጠት አንስቶ የተለያዩ የቁጥጥር ስራዎችን የሚሰራ ነው።

ከዚህ ሁሉ በሁዋላ ታድያ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ለውጥን የሚያመጣ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት የሚሆን ገንዘቦችን ለማግኘት ሁነኛ አማራጭ የሚሆን ገበያ ይቋቋማል ተብሎ ይጠበቃል ; እሱም ” የኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያ” ወይንም (Ethiopia securities exchange market)የሚባል ስያሜ ይኖረዋል ።

የሰነድ መዋእለ ነዋይ ገበያ ሲቋቋም ዋነኛ ተዋናይ የግሉ ዘርፍ ሲሆን መንግስት ለገበያው ዋስትና ለመስጠት ጥቂት ድርሻ እንዲኖረው እንደሚደረግና ; መንግስትንም ወክሎ የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያው ባለድርሻ የሚሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመን ሆልዲንግ መሆኑ ድርሻውም የገበያውን ሩብ ሊሆን እንደሚችል ሰምተናል።

የሰነድ ገበያው ሲቋቋም በመጀርያው ዙር ሁለት ዋና ዋና ስራዎችን ያከናውናል

አንዱ ፣ ኩባንያዎች የአክስዮን ድርሻ እንዲሸጡ የገበያ ቦታ መሆን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ኩባንያዎች ሲቋቋሙ ለመጀመርያ ጊዜ በይፋ ድርሻ ይሸጣሉ እንጂ ፣ ኩባንያዎቹ አንዴ ከተቋቋሙ በኋላ በኩባንያው አክስዮን ያላቸው ግለሰቦች ወይንም ተቋማት ድርሻቸውን ለሌላ ግለሰብ ወይንም ተቋም መሸጥ ቢፈልጉ እንዲሁም ሌላ ተጨማሪ አክዮን ማቅረብ ቢፈለጉ በሁለትዮሽ በሚደረግ ስምምነት እንጂ ይፋዊ የሆነ ገበያ አልነበረውም።

በካፒታል ገበያ አዋጁ መሰረት ከሚቋቋሙት ገበያዎች ውስጥ የመጀመርያው እንደሚሆን በሚጠበቀው የኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያ ግለሰቦች በእጃቸው ያለ የኩባንያ አክስዮንም ሆነ ራሳቸው ኩባንያዎች ድርሻ የሚሸጡበት ይሆናል።ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ የገበያ አይነት ነው።

ሁለተኛው ፣  የተለያዩ የብድር ሰነዶች ወይንም ቦንዶች በሰነድ ገበያው ለግብይት የሚቀርቡ ይሆናል ። ኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብን ለመበደር ቦንድ ጥቅም ላይ ሲውል የቆየው ብሄራዊ ባንክ ከንግድ ባንኮች ገንዘብን መበደር ሲፈልግ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስቴር ሲሸጠው የነበረው ቦንድ ወይንም የግምጃ ቤት ሰነድ እየተባለ የሚጠራው ነው። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የብድር ሰነድ ገበያ የመጀመርያ ደረጃ የሰነድ ገበያ በሚል እንደሚታወቅ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ወደፊት የሚኖራት የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያ ግን ሁለተኛ ደረጃ የሰነድ ገበያ(secondary bond market) ሆኖም ያገለግላል። በዚህ ገበያ ላይ በመጀመርያው ገበያ ላይ ሰነድ የገዙ ተቋማት ሰነዱን መልሰው ለሌላ አካል መሸጥ ይችላሉ። 

ለአብነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚሆን በሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር ዋጋ ያለው ሰነድን ግለሰቦች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከገዙ በኋላ ቦንዱ የያዘውን ገንዘብ ለማስመለስ አምስት አመት መጠበቅ ሊኖርባቸው ይችላል።

ነገር ግን ይህ ሰነድ ያለው ግለሰብ ገንዘቡን ቢፈልገው የሰነዱ ጊዜ ካላበቃ የሚሸጥበት ገበያ የለውም።ሁለተኛ ደረጃ ገበያ ሲኖር ግን ሰነዱን ለሶስተኛ ወገን ሽጦ ገንዘቡን ማግኘት ይችላል።ሰነዱን የገዛው ሰውም ጊዜው ሲደርስ ከዋናው የሰነድ ባለቤት በቦንድ ያበደረውን ገንዘብ ሊቀበል ይችላል። ይህም ብቻ ሳይሆን የሰነድ ገበያው ኩባንያዎች ለኢንቨስትመንት የሚሆን ገንዘብን የመተማመኛ ሰነድን እየሰጡ እንዲበደሩ ያስችላቸዋል።የገበያው ተግባራዊ መሆንም ባንክን ብቻ የብድር ምንጭ ላደረገው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ አማራጭን ያመጣለታል።

 መንግስት የሰነድ ገበያው ውጤታማ እንዲሆን ከወዲሁ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ወለድ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ይገልጻል። መንግስት ከዚህ ቀደም በግምጃ ቤት ሰነድ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲዎች የተከማቸ ገንዘብን ሲበደር ከአንድ በመቶ የማይበልጥ ወለድን ነበር የሚያስበው። የወለዱ ማነስም ብዙ ገንዘብ ያላቸው ድርጅቶች የመንግስትን ሰነድ ከመግዛት እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል።

ከ2012 አ.ም ጀምሮ ግን ብሄራዊ ባንክ የሰነድ ገበያ ወለድን በገበያ ውድድር እንዲሆን በማድረግ እንደ አዲስ በጀመረው ሽያጭ በሰነድ ገንዘብ ለሚያቀርቡለት ተቋማት በአማካይ 7 እና 8 በመቶ ወለድን ማሰብ በመጀመሩ በርካታ ቢሊየን ብሮችን ማግኘት ጀምሯል።

የሰነድ ገበያው የወለድ ምጣኔ በገበያ ውድድር እንዲሆን መደረጉም ኢትዮጵያ የሚኖራት የካፒታል ገበያ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚረዳው ይጠበቃል።በሰነድ መዋእለ ነዋይ ገበያ የሚገኝ የኢንቨስትመንት ገንዘብ ራሱን የቻለ አማራጭ ከመሆኑም ባለፈ በህትመት ወደ ገበያ የሚገባ ገንዘብን በመቀነስ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ያግዛል።

 የሰነድ መዋእለ ነዋይ ገበያይዞ የሚመጣቸውአዳዲስ ስራዎች

ኢትዮጵያ የሰነድ መዋእለ ነዋይ ማገበያያ የካፒታል ገበያ ሲኖራት ብዙ አይነት ስራዎች አብረው ለሀገሪቱ ይተዋወቃሉ። በካፒታል ገበያ ውስጥ የማቀላጠፍ ሚና  የሚኖራቸው የሰነድ አገበያይ ደላሎች(capital market intermidiery)ይኖራሉ ። የኢንቨስትመንት ባንኮች እንዲመሰረቱ መንገድ ይጠርጋል፣  የጋራ ኢንቨስትመንት አከናዋኞችም በሰፊው ስለሚኖሩ ዘርፈ ብዙ የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

ታዲያ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ አዲስ ገጽታን የሚሰጠው ገበያ መች ይቋቋማል? ለሚለው ጥያቄ የብሄራዊ ባንክ አማካሪ አቶ መለስ ምናለ  ሲመልሱ  ፣ ገበያው መች እንደሚቋቋም በትክክል ቀኑን መናገር ቢከብድም በቅርቡ እንደሚቋቋም ፣ ለዚህም ለገበያው የሚያስፈልግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ ስራዎችን አጠናቆና አክስዮን ሽጦ በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]