ዋዜማ ሬድዮ፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሸብር እና በህገመንግስት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዛሬ ረፋድ ላይ ተሰይሞ ፍርድ መስጠቱን የዋዜማ ሪፖርተር ዘግባለች፡፡


በመዝገቡ ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ገድሏል ተብሎ አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ጥላሁን ያሚ ላይ ከሳሽ አቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃዎቹነን በማቅረብ በሞት ፍርድ እንዲቀጣ ችሎቱን የጠየቀ ቢሆንም ችሎቱ የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት አስተላልፏል፡፡
ድምፃዊው ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓም ከምሽት 3፡30 ገደማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ኮንዶኒየም አካባቢ ነበር በጥይት የተገደለው፡፡


በጥፋቱ ተሳትፈዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች እና የተከሳሾች መከላከያ ለአንድ አመት ያህል ሲመረምር የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎትም ዛሬ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔው ሰጥቷል፡፡


በመዝገቡ የተካተተው ሌላው ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ደግሞ ሽጉጥ ገዝቶ ለአንደኛ ተከሳሽ በመሽጥ በወንጀሉ ተባባሪ ስለመሆኑ አቃቤ ህግ ባቀረበው ማስረጃ መሰረት የ18 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት ለፖሊስ ማሳወቅ ሲገባው መረጃን ደብቆ በመያዝ የተከሰሰው ሌላኛው ተከሳሽ አብዲ አለማየሁ ደግሞ የ6 ወራት ቀላል እስራት ተወስኖበታል፡፡


ከዚህ ቀደም በወንጀሉ ተባባሪነት ተጠርጥራ በዚህ መዝገብ ተካታ የነበረችውን ላምሮት ከማል የከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት በነፃ አሰናብቷት የነበረ ቢሆንም አቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ አሁንም በእስር ላይ ሆና ጉዳይዋን በበላይ ፍርድ ቤት እየተከታተለች ትገኛለች፡፡ [ዋዜማ ሬድዮ]