ዋዜማ- በፌደራል ከተሞች ጉዳይ ጥላ ውስጥ የወደቀው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፤ በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ለውሳኔ የቀረቡ ጉዳዮችን አስተናግዷል። በአወያዮች፣ በምሁራን ፓናል አባላት እንዲሁም በምክረ ሀሳብ አጠናቃሪ ቡድን አባላት ላይ ቅሬታዎች የቀረቡ ሲሆን፤ ከ10 የሚልቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኮሚሽኑ ቅሬታ ለማቅረብ ፊርማ እያሰባሰቡ መሆናቸውን ሰምተናል። 

የልዩ ኃይል አደረጃጀታቸውን ያላፈረሱ ክልሎች

“በተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች” አጀንዳ ውስጥ ከተካተቱ ንዑስ አጀንዳዎች መካከል “የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና አደረጃጀት” ጉዳይ ይገኝበታል። በንዑስ አጀንዳው አማካኝነት ምክክር ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የክልል ልዩ ኃይሎች ጉዳይ የሚገኝበት ሲሆን፤ አሁንም የልዩ ኃይል አደረጃጀትን ያላፈረሱ ክልሎች መኖራቸው በምክክር ሂደቱ መነሳቱን ምንጮች ነግረውናል። ምንም እንኳን የክልሎች የልዩ ኃይል አደረጃጀት እንዲፈርስ የተወሰነ ቢሆንም፤ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች በተለያየ መልክና ስያሜ የልዩ ኃይል ሠራዊታቸውን ሳይበትኑ ማስቀጠላቸውን ያነሱ ተመካካሪዎች፤ ውሳኔው በሁሉም ክልሎች በዕኩልነት  ተግባራዊ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ሰምተናል። 

የሶማሌ ክልል ባለድርሻ አካላትን ወክለው በጉባኤው እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች፤ ከክልሉ ጋር በሚጎራበቱ የሶማሊያ አካባቢዎች የአልሸባብ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን በማንሳት ክልሉ አሸባሪዎችን ለመታገል የልዩ ኃይል አደረጃጀቱን እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል። ይሁንና የሁሉም ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት እንዲፈርስ የቀረበው ምክረ ሀሳብ ሚዛን መድፋቱን ሰምተናል። በዚህም እንደ ሶማሌ ባሉ ክልሎች የአካባቢውን ቋንቋ እና ስነ ልቦና የሚያውቁ የፌደራል ጸጥታ አካላት እንዲሰማሩ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ምንጮች ጠቁመዋል። 

ክልሎች የልዩ ኃይል አደረጃጀታቸውን ማፍረሳቸውን ቢገልጡም፤ በፖሊስና አድማ ብተና ስም ዘመናዊ ትጥቆችን የታጠቀ ሰራዊት አደራጅተዋል የሚል ሀሳብ የሰነዘሩ ተመካካሪዎች በበኩላቸው፤ የክልሎችን የመሳሪያ እና የሰራዊት አቅም የሚቆጣጠር አደረጃጀት በፌደራል ደረጃ እንዲቋቋም ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸውን ሰምተናል። እነዚህ ምክረ ሀሳቦች የሥራ ቡድኑ ውሳኔ እንዲያሳልፍባቸው የቀረቡ ናቸው። 

ወርሃዊ ደሞዝ የሚከፈለው የሚሊሻ ሠራዊት

የክልሎች ልዩ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ እንዲፈርሱ ከቀረበው ምክረ ሀሳብ በተጨማሪ፤ ወጥ የሆነ የሚሊሻ ሠራዊት አደረጃጀት እንዲፈጠር ምክረ ሀሳብ ቀርቧል። ይህ ሠራዊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የትጥቅ ሁኔታ እና የስልጠና መንገድ እንዲኖረው መጠየቁን የነገሩን ምንጮች፤ የሠራዊቱ አባላት ወርሃዊ ደሞዝ እንዲቆረጥላቸው ምክረ ሀሳብ መቅረቡንም ጠቁመዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሚሊሻ ሠራዊት አባላት መኖራቸውን ያነሱ ተመካካሪዎች ደግሞ፤ ወርሃዊ ደሞዝ መክፍል የመንግስትን የበጀት አቅም የሚፈትን መሆኑን እንዳነሱ ሰምተናል። ይሁንና የሥራ ቡድኑ አባላት በጉዳዩ ዙሪያ ውሳኔ እንዲያሳልፉ በምክረ ሀሳብ መቅረቡን አረጋግጠናል።  

ዕድል የሚነፍጉ አወያዮች

በስልታዊ ቡድን ደረጃ ምክክር መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አስተያየትና ሀሳብ ለመስጠት እድል ማግኘት ከባድ እየሆነ መምጣቱን ምንጮች ነግረውናል። በተለይም በመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ አጀንዳ ላይ እየተመካከሩ የሚገኙ ተመካካሪዎች፤ እጅ በማውጣት ሀሳብ ለማቅረብ የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ጥረት በአወያዮች የተነሳ እንቅፋት እንደገጠመው ምንጮች ነግረውናል። አወያዮች የመናገር ዕድል የሚሰጡበት መንገድ ላይ ቅሬታ ያላቸውና የ“አካሄድ” ጥያቄ ለማንሳት የሞከሩ ተመካካሪዎችም የመናገር ዕድል እንዳላገኙ ሰምተናል።

የመናገር ዕድል ተሰጥቷቸው አስተያየት የሚሰነዝሩ ተመካካሪዎች የሚያነሷቸው ሀሳቦች በብዛት መመሳሰላቸው ጉዳዩ ሆን ተብሎ የሚከናወን እንደሆነ ይጠቁማል የሚሉ ተመካካሪዎች፤ “ማን ምን አይነት ሀሳብ ያነሳል?” የሚለው ተጠንቷል የሚል ጥርጥሬ እንዳላቸው ገልጠዋል።

የአወያዮች ገለልተኝነት፣ ከተመካካሪዎች መካከል “የተመረጡ” የምክረ ሀሳብ አጠናቃሪ ቡድን አባላት “በአብዛኛው” ወደ አንድ ወገን ያጋደሉ መሆን ቅሬታ ያሳደረባቸው ጉዳይ መሆኑን ያነሱ ተመካካሪዎች ለኮሚሽኑ ቅሬታ ማቅረባቸውንም ምንጮች ገልጠዋል። 

ማስፈራሪያ የደረሳቸው ተመካካሪዎች

በምክክር ሂደቱ ጠንካራ ሀሳብ ከሰነዘሩና የብልጽግና ፓርቲ አባላት ካነሷቸው ምክረ ሀሳቦች የሚለዩ ምክረ ሀሳቦችን ካነሱ ተመካካሪዎች መካከል፤ በተለያየ መንገድ “ማስፈራሪያ” የደረሳቸው መኖራቸውን ተወያዮች ነግረውናል። የድርድር መልክ ያላቸውና “ይህንን ጉዳይ እንድናደርግላችሁ፤ በዚህ ጉዳይ ያላችሁን አቋም አስተካክሉ” የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡም ሰምተናል።  

ቅሬታቸው ምላሽ ያላገኘ ፓርቲዎች

በምክክሩ አካሄድና በተስተዋሉ ክፍተቶች ዙሪያ ለኮሚሽኑ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ሰምተናል። ለኮሚሽነሮች በቀጥታ በደብዳቤ የቀረበ ቅሬታን ጨምሮ፤ ኮሚሽኑ በዘረጋው የቅሬታ ማቅረቢያ አሠራር መሰረት የቀረቡና ከ10 ቀናት በላይ ያስቆጠሩ ቅሬታዎች እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውንም የአንድ ፓርቲ አመራር ለዋዜማ ገልጠዋል።  ይሁንና አሁንም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቅሬታ የገባቸው ፓርቲዎች በጋራ ቅሬታቸውን ለማቅረብ ፊርማ እያሰባሰቡ መሆናቸው ታውቋል። ከ10 በላይ የሚሆኑት ፓርቲዎች፤ ራሳቸውን ከምክክሩ እስከማግለል የደረሰ ውሳኔ ላይ የሚያደርሳቸው ጉዳይ እንደገጠማቸው መግለጣቸውንም ምንጮች ጠቁመዋል። [ዋዜማ]