ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 27ኛ ቀን በሥራ ቡድኖች ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው ምክክር ቀጥሎ ውሏል። በሰባቱ የሥራ ቡድኖች ቅዳሜ ነሐሴ 02 ቀን የጀመረው የተጠናቀሩ የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦች ላይ አስተያየት የመስጠት ሂደት የቀጠለ ሲሆን፤ የፌደራል ከተሞች ጉዳይን እየተመካከረበት በሚገኘው የሥራ ቡድን 7 ደግሞ የተጠናቀረው የአጀንዳ ምክረ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ተነቧል። የሥራ ቡድኑን ምክረ ሀሳብ እንዲያጠናቅሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው 30 ተመካካሪዎች፤ ከሌሎች የሥራ ቡድኖች አንጻር ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ያጠናቀሩት ምክረ ሀሳብ በአመዛኙ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ያካተተ መሆኑን የገለጡልን ምንጮች፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እና መቀመጫ ትሁን” የሚለው ምክረ ሀሳብ አሁንም የልዩነት ማዕከል መሆኑን ጠቁመዋል። 

ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት ምክረ ሀሳብ

የአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ አቋም ጉዳይ አሁንም በተመካካሪዎች ዘንድ ልዩነትን ፈጥሮ የቀጠለ ጉዳይ ሲሆን፤ ተጠናቅሮ በቀረበው የሥራ ቡድኑ ምክረ ሀሳብ ላይ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ መሆኗ በሕገ መንግስቱ ይስፈር” የሚለው አማራጭ ምክረ ሀሳብ መካተቱ ተቃውሞ አስከትሏል። ይህንን ምክረ ሀሳብ ደግፈው የተከራከሩ ተመካካሪዎች፤ ይህ ድንጋጌ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 እንዲሰፍር መጠየቃቸውን ሰምተናል። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5፤ ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ስለሚኖራት “ልዩ ጥቅም” የሚደነግግ ሲሆን፤ በምክክሩ “ልዩ ጥቅም” የሚለው ድንጋጌ እንዲቀር ስምምነት ላይ መደረሱን የገለጡልን ምንጮች፤ በንዑስ አንቀጹ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ” ትሁን የሚል ድንጋጌ እንዲካተት መጠየቁን ነግረውናል። 

ለተመካካሪዎች የቀረበውን ምክረ ሀሳብ ተከትሎ በተሰጡ አስተያየቶች፤ በሁለቱም ወገን “ማሳመኛ” ያሏቸውን ነጥቦች ያነሱ ተመካካሪዎች ቢኖሩም፤ አሁንም ስምምነት ላይ አለመደረሱን ሰምተናል። በተመካካሪዎች የተነሱ አስተያየቶች ተካተው የአጀንዳው ምክረ ሀሳብ ዳግም እንዲቀርብ መወሰኑን የጠቀሱልን ምንጮች፤ በዋናነት የከተማዋን ሕጋዊ አቋም በሚመለከት የቀረቡት ሁለት አማራጮች አከራካሪ ሆነው መቀጠላቸው አይቀሬ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የመንግስት አደረጃጀት አጀንዳ አራቱ ጉዳዮች

የመንግስት አደረጃጀትን ጉዳይ እየተመካከረበት በሚገኘው የሥራ ቡድን፤ አራት ጉዳዮች ስምምነት አልተደረሰባቸውም በሚል መለየታቸውን ምንጮች ነግረውናል። የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦችን አጠናቅረው እንዲያቀርቡ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተመካካሪዎች ያቀረቡት የምክረ ሀሳብ ሰነድ በርካታ አስተያየቶችን ማስተናገዱን የገለጡልን ምንጮች፤ “ቀጣዩ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ምን ይሁን? መሪውስ በምን አይነት መንገድ ይመረጥ?”፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አወቃቀር፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ምርጫ እንዲሁም የሕገ መንግስት ተርጓሚ ፍርድ ቤት ጉዳይ ስምምነት ላይ አልተደረሰባቸውም በሚል መቅረባቸውን ጠቁመዋል።

ቀጣዩ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ፓርላመንታዊ ሆኖ ፕሬዝዳንቱ ከፓርላማው ይመረጥ የሚል ምክረ ሀሳብ በብልጽግና ፓርቲ አባላት እየተቀነቀነ የሚገኝ ምክረ ሀሳብ መሆኑን የገለጡ ምንጮች፤ ፕሬዝዳንቱ በቀጥታ በሕዝብ መመረጥ አለበት የሚል ሀሳብ የሚያነሱ ተመካካሪዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። በሁለቱ ምክረ ሀሳቦች መካከል ያለው ልዩነት፤ ስምምነት ላይ ያልተደረሰበትና ቀጣይ ምክክር የሚደረግበት መሆኑንም ሰምተናል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አወቃቀር ጉዳይ ሌላኛው ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት ጉዳይ መሆኑን የገለጡልን ምንጮች፤ “ሁሉም ብሔሮች በምክር ቤቱ ዕኩል ውክልና ያግኙ” የሚል እና “ብሔሮች በአንድ ሚሊዮን ሕዝብ ተጨማሪ ወንበር ያግኙ” የሚሉ ሀሳቦች በአማራጭነት መቅረባቸውን ጠቁመዋል። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የሚመረጡበት ሁኔታ ደግሞ ሌላኛው ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት ጉዳይ ነው። የምክር ቤቱ አባላት በቀጥታ በሕዝብ ይመረጡ የሚል እና አሁን ባለው አሠራር የክልል ምክር ቤቶች የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላትን የሚመርጡበት ሂደት ይቀጥል የሚል አማራጭ መቅረቡን ሰምተናል።

የሕገ መንግስት ተርጓሚ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም የሚጠይቅ ምክረ ሀሳብ በአጀንዳው መካተቱን የገለጡልን ምንጮች፤ የፍርድ ቤቱ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኃላፊነት ድርሻ ክፍፍል ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት አራተኛ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል። ፍርድ ቤቱ ያለ ፌደሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ ገብነት “ሙሉ’ ስልጣን ይሰጠው የሚሉና፤ “በጉልህ” ጉዳዮች ዙሪያ ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ይሰጥ የሚሉ ተመካካሪዎች መኖራቸውን አውቀናል። ሁለቱ ምክረ ሀሳቦች በአማራጭነት መቅረባቸውን የጠቆሙ ምንጮች፤  በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ምክክር ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጠዋል።

አጠናቃሪዎች በሌሎቹ ጉዳዮች ስምምነት ላይ መደረሱን “በራሳቸው” በይነዋል የሚል ቅሬታ መኖሩንም የሰማን ሲሆን፤ ነሐሴ 05 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የሥራ ቡድኑ ምክክር እንደሚቀጥል ምንጮች ነግረውናል።

በሥራ ቡድን ሰነድ ላይ አንፈርምም ያሉ ተመካካሪዎች

የሥራ ቡድናቸው አጀንዳ ላይ የሚያደርጉትን ምክክር እያጠናቀቁ የሚገኙ የሌሎች ሥራ ቡድኖች ተመካካሪዎች፤ በፌደራል ከተሞች ጉዳይ ላይ እየተመካከረ የሚገኘው የሥራ ቡድን ውጤት ሳይታወቅ፤ በሥራ ቡድናቸው የምክረ ሀሳብ ሰነድ ላይ እንደማይፈርሙ መግለጣቸውን ሰምተናል። በሥራ ቡድን ደረጃ እየተደረገ የሚገኘውን ምክክር አስቀድመው የጀመሩ ቡድኖች፤ ምክረ ሀሳባቸውን አጠናቅረው ሲያጠናቅቁ፤ የአዲስ አበባን ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ በምክረ ሀሳቡ ላይ ከመፈረም ለመቆጠብ የወሰኑ ተመካካሪዎች መኖራቸውን ምንጮች ነግረውናል። [ዋዜማ]