ዋዜማ- ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ25ኛ ቀን ውሎው በሥራ ቡድን ደረጃ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ላይ መመካከር ጀምሯል። ሀሙስ ሐምሌ 30 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ለሥራ ቡድን ጉባኤዎች የቀረቡ የስልታዊ ቡድን ምክረ ሀሳቦችን እንዲያደራጁ ኃላፊነት የተሰጣቸው አጠናቃሪ ቡድኖች፤ በሰባት የሥራ ቡድኖች ያጠናቀሩትን ምክረ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ የፌደራል ከተሞች ጉዳይን በአጀንዳነት በያዘው ቡድን ግን የተጠናቀረ ምክረ ሀሳብ ለተመካካሪዎች ሳይቀርብ ቀርቷል።
የአዲስ አበባ ጉዳይ
በአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ አቋም ዙሪያ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች በተመካካሪዎች ላይ ልዩነት የፈጠሩ ሆነው ቆይተዋል። “አዲስ አበባ የፌደራል ከተማ ትሁን” በሚለው ምክረ ሀሳብ ዙሪያ ስምምነት ላይ ቢደረስም፤ “ከተማዋ በተጨማሪነት የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እና መቀመጫ ትሁን” በሚል የተነሳው ምክረ ሀሳብ ግን በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እና ከአዳራሽ ውጭ ውጥረት እንዲሰፍን ማድረጉን ምንጮች ነግረውናል። ይህ ምክረ ሀሳብ፤ አዲስ አበባን በተዘዋዋሪ የኦሮሚያ ክልል “ይዞታ” የሚያደርግ ነው የሚል ሀሳብ የሚያነሱ ተመካካሪዎች፤ ምክረ ሀሳቡን ለድርድር የማያቀርቡት መሆናቸውን ከሚገልጡ ተመካካሪዎች ጋር “እየተሟገቱ” መሆናቸውን ሰምተናል።
በሁለቱ ስልታዊ ቡድኖች የተዘጋጁ ምክረ ሀሳቦችን አደራጅተው እንዲያቀርቡ ኃላፊነት የተሰጣቸው 30 ተመካካሪዎችም፤ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እና መቀመጫ ትሁን በሚለው ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ምክንያት፤ የአጀንዳውን ምክረ ሀሳብ አጠናቅረው ለሥራ ቡድኑ ጉባኤ ማቅረብ አለመቻላቸውን ምንጮች ነግረውናል። ሌሎች የሥራ ቡድኖች ቅዳሜ ነሐሴ 02 ቀን፣ ተጠናቅረው በቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ዙሪያ ምክክር ቢያደርጉም፤ የፌደራል ከተሞች ጉዳይን እየመከረበት የሚገኘው የሥራ ቡድን 7 ግን ምክክር ሳያደርግ ለሰኞ ነሐሴ 04 ቀን ቀጠሮ በመያዝ ተበትኗል። የቡድኑን ምክረ ሀሳብ እንዲያጠናቅሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው 30ዎቹ የአጠናቃሪ ቡድን አባላት ደግሞ የሚያደርጉትን ምክክር እንዲቅጥሉ መወሰኑን ምንጮች ነግረውናል።
ለሁለት የተከፈለው ብልጽግና ፓርቲ
የብልጽግና ፓርቲ አባላት በአጀንዳው ዙሪያ ለሁለት የተከፈለ አቋም ማራመዳቸውን ቀጥለዋል። የፓርቲው አመራሮች “አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ትሁን” የሚለውን አማራጭ ደግፈው ሀሳብ ሲሰነዝሩ የነበሩ አባላቱን ማስጠንቀቁን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ፊቱን ከተማዋ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ትሁን የሚለውን ምክረ ሀሳብ ወደተቃወሙ አባላቱ አዙሯል። በማዕከል ደረጃ ያሉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እና መቀመጫ መሆኗ በሕገ መንግስቱ ይካተት” የሚለው ምክረ ሀሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ግፊት ማድረግ መጀመራቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። ይህንን ምክረ ሀሳብ ለሚቃወሙ የፓርቲው አባላት፤ “ከፓርቲው አቋም ውጭ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው” የሚል የማስጠንቀቂያ መልዕክት እንደደረሳቸው የገለጡልን ምንጮች፤ በከፍተኛ አመራሮች ጫና የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነግረውናል።
በተለይም በአማራ ክልል መንግስት ውስጥ የኃላፊነት ሚና ያላቸውና ከምክክር ጉባኤው ጅማሮ አንስቶ አዲስ አበባ የፌደራል ከተማ ትሁን የሚለውን አማራጭ ደግፈው እየሞገቱ የሚገኙ ተመካካሪዎች ጫና እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ሰምተናል።
“አዲስ አበባ የፌደራል ከተማ ትሁን” በሚለው ምክረ ሀሳብ ዙሪያ ስምምነት ላይ የተደረሰው አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ትሁን የሚለውን አቋም ባንጸባረቁ የፓርቲው አባላት ላይ በተደረገው ጫና ምክንያት መሆኑን የሚያነሱ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፤ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ መሆኗን ዕውቅና መስጠት እንደ “ማካካሻ” የሚታይ ሊሆን ይገባል የሚል አቋም እንዳላቸውም ምንጮች ጠቁመዋል።
ከምክክር አዳራሾች ውጭ እየተካሄደ ያለው ድርድር
በምክክር አዳራሾች ከሚደረገው የምክክር ሂደት ውጭ፤ ትይዩ የሆኑ ድርድሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን ዋዜማ ሰምታለች። የማንነት እውቅና፣ የአስተዳደር መዋቅርና ሌሎች ጥያቄዎች ያሏቸው ፓርቲዎች፤ “ከብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ እንድታገኙ በአዲስ አበባ ጉዳይ አግዙን” የሚል መደራደሪያ እየቀረበላቸው መሆኑን ዋዜማ ጥያቄው ከቀረበላቸው የፓርቲ አመራሮች ሰምታለች። የተለያዩ ክልሎችን ወክለው በምክክሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ አባላትም፤ መደራደሪያ ቀርቦላቸው አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ትሁን የሚለውን ምክረ ሀሳብ እንዲደግፉ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። በዚህም በጉዳዩ ዙሪያ “የተለሳለሰ” አቋም እያራመዱ የሚገኙ ተመካካሪዎች መኖራቸው ታውቋል።
ግፊት የሚያደርጉ ኮሚሽነሮች
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የምክክር ሂደቱን በአግባቡ መምራት አልቻለም የሚሉ ድምጾች መበራከታቸውን የጠቆሙ ምንጮች፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጡ የተመደቡ የምሁራን ፓናል አባላት እና አወያዮች በብልጽግና ፓርቲ በኩል እንደ አቋም የተያዙ ሀሳቦችን በተመካካሪዎች ላይ “ለመጫን” ሞክረዋል የሚል ቅሬታ መቅረቡን ነግረውናል። ኮሚሽኑ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡና በቂ ሙያዊ ክህሎት ሳይኖራቸው በምሁራን ፓናል ውስጥ የተካተቱ ግለሰቦች ላይ እርምጃ አለመውሰዱም ጥያቄ አስነስቶበታል።
ከዚህ ቅሬታ ባሻገር ተመካካሪዎች “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ትሁን” የሚለውን ምክረ ሀሳብ እንዲቀበሉ ግፊት እያደረጉ የሚገኙ ኮሚሽነሮች መኖራቸውን ሰምተናል። ይህ የኮሚሽነሮች ተግባር ቅሬታ የፈጠረባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ኮሚሽነሮች “ገለልተኛ” ሆነው እንዲሠሩ በተናጠል ባደረጉት ስብሰባ መጠየቃቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።
“ወርቃማአማካይ” ያጣውአጀንዳ
በምክክሩ እንደ አማራጭ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች በድምጽ ብልጫ ውሳኔ ቢያገኙ እንኳን ዘላቂ መፍትሄ መሆን የሚችሉ አይደሉም የሚሉ አስተያየቶች መበራከታቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ የአዲስ አበባ ጉዳይ ሁለቱን የሀሳብ ቡድኖች የሚያስማማ “ወርቃማ አማካይ” ማጣቱን ጠቁመዋል። አዲስ አበባ የፌደራል ከተማ ብቻ ትሁን የሚለው ምክረ ሀሳብ በምክክሩ የሚጸድቅ ከሆነ፤ በኦሮሚያ ክልል “ተቃውሞ” ሊያስነሳ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ሰምተናል። ብልጽግና ፓርቲም በኦሮሚያ ክልል አለኝ የሚለውን ተቀባይነት ላለማጣት አዲስ አበባ የፌደራል እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ትሁን የሚለውን ምክረ ሀሳብ አጠንክሮ ቢይዝም፤ ከዚህ ምክረ ሀሳብ በተቃራኒ የቆሙ ወገኖች መበራከት ፓርቲውን አጣብቂኝ ውስጥ የጣለ ጉዳይ ሆኗል። ይህ እውነታ በምክክሩ ከቀረቡ ምክረ ሀሳቦች መካከል አንዱ በድምጽ ብልጫ ቢጽድቅ፤ አንድን ወገን አሸናፊ፣ ሌላኛውን ደግሞ ተሸናፊ የሚያደርግ ይሆናል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
በአጀንዳው ዙሪያ እየተደረገ የሚገኘው ምክክር ሁለቱን ወገኖች ሊያቀራርብ የሚችል ”ወርቃማ አማካይ” ማግኘት እንደተሳነው ያሰመሩበት የዋዜማ ምንጮችም፤ ከአጀንዳው ውጭ የሆነ ድርድር እንዲካሄድ ለማስቻል እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ነግረውናል። የምክረ ሀሳብ አጠናቃሪ ቡድኑ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር፤ በትይዩ የሚካሄደው ድርድር የአጀንዳውን እጣ ፈንታ የመወሰን ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑንም ሰምተናል።
ምክክሩን “ለማሳደር” የቀረበው ሀሳብ
የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች እንዲሁም በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ድርሻ ያላቸው አካላት፤ እየተካሄደ የሚገኘው የምክክር ሂደት በሁሉም ጉዳዮች ዙሪያ “መግባባት” እና “መፍትሄ” ላያመጣ ይችላል የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ ሲሰነዝሩ ተሰምተዋል። በአጀንዳው ዙሪያ እየተነሱ የሚገኙ ሀሳቦች በሌሎች አጀንዳዎች ላይ እየተካሄደ ያለውን ምክክር ተጽዕኖ ውስጥ መክተታቸውን ያነሱ ወገኖች፤ የአዲስ አበባን ጉዳይ “ለጊዜው በማቆየት” በሌሎች አጀንዳዎች ላይ እየተካሄዱ ያሉ ምክክሮችን ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ለኮሚሽኑ ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸውንም ሰምተናል። [ዋዜማ]
