የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እና መቀመጫ ትሁን የሚለውን ምክረ ሀሳብ ያቀረቡ ተመካካሪዎች ደግሞ፤ ምክረ ሀሳቡ በሥራ ቡድን ደረጃ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ጠይቀዋል።
ዋዜማ- በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ 23ኛ ቀን ውሎ በርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች (የሥራ ቡድኖች) ደረጃ የሚካሄደው ምክክር ተጀምሯል። በአንድ የሥራ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ሁለት ስልታዊ ቡድኖች የአጀንዳ ምክረ ሀሳባቸውን ለሥራ ቡድናቸው ጉባኤ ያቀረቡ ሲሆን፤ የሁለቱን ስልታዊ ቡድኖች ምክረ ሀሳቦች አደራጅተው ወጥ የምክረ ሀሳብ ሰነድ የሚያዘጋጁ 30 የአጠናቃሪ ቡድን አባል ተመካካሪዎች ሥራ ጀምረዋል። ይህ ምክረ ሀሳብ የማደራጀት ሂደት ነሐሴ 01 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል የሚል ዕቅድ ስለመያዙ የነገሩን ምንጮች፤ የተደራጀው ምክረ ሀሳብ ነሐሴ 02 ቀን ለሥራ ቡድኑ አባላት ቀርቦ ምክክር እንዲደረግበት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
ሰባቱ የሥራ ቡድኖች ሥራቸውን በተቀመጠላቸው ሰዓት መሰረት ስለመጀመራቸው የገለጡት የዋዜማ ምንጮች፤ በፌደራል ከተሞች ጉዳይ እየመከረ የሚገኘው የሥራ ቡድን ከኮሚሽነሮች ጋር ከተደረገ ውይይት በኋላ ዘግይቶ ወደ ምክክር ሂደቱ መግባቱን ነግረውናል።
በፌደራል ከተሞች ተመካካሪ ቡድን ውስጥ ምን ተፈጠረ?
በስልታዊ ቡድን ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ ቁመና ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው ምክክር በተመካካሪዎች ዘንድ የሀሳብ ልዩነት የተስተናገደበት መሆኑን የገለጡልን ምንጮች፤ ከጥቃቅን ቡድን ደረጃ ጀምሮ በተካሄዱ ምክክሮች ያልተነሱ ሀሳቦች በስልታዊ ቡድን ቃለ ጉባኤ ላይ እንዲካተቱ መጠየቁ ሰፊ ልዩነት የፈጠረ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል። ቀደም ባለው የምክክሩ ሂደት ለአዲስ አበባ ሕጋዊ ቁመና ከቀረቡ አማራጮች መካከል “አዲስ አበባ የፌደራል ከተማ ሆና ራሷን በራሷ ታስተዳደር” የሚልና “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል አካል ትሁን” የሚሉ አማራጮች በስፋት ይነሱ እንደነበር ምንጮች ነግረውናል። 250 አባላት ባሏቸው ሁለቱ የሥራ ቡድኖች በተካሄዱ ምክክሮች “አዲስ አበባ የፌደራል ከተማ ትሁን” የሚለው አማራጭ ሚዛን እየደፋ መምጣቱን ተከትሎም፤ ሁለተኛውን አማራጭ ደግፈው ሀሳብ ሲያቀርቡ የነበሩ ተመካካሪዎች፤ “አዲስ አበባ የፌደራል ከተማ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማና መቀመጫ” ትሁን የሚል ምክረ ሀሳብ በቃለ ጉባኤ እንዲመዘገብላቸው መጠየቃቸውን ሰምተናል። ይህ ምክረ ሀሳብ በጥቃቅን እና ንዑስ ቡድን ደረጃ ያልተነሳ ሀሳብ መሆኑን ያነሱ ተመካካሪዎች ደግሞ፤ በቃለ ጉባኤ ላይ መያዝ የለበትም የሚል መከራከሪያ በማንሳት የልዩነት ድምጽ አሰምተዋል።
ይህ ምክረ ሀሳብ በቃለ ጉባኤ እንዲያዝላቸው የጠየቁ ተመካካሪዎች፤ ጉዳዩ አዲስ አለመሆኑን በማንሳት “አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሕገ መንግስታዊ ማረጋጋጫ ይሰጠው” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ለቡድኖቹ አስረድተዋል። “አንድ ከተማ የፌደራልም የክልልም ከተማ መሆን አትችልም”፣ “የክልሎች መቀመጫን የተመለከተ ጉዳይ በፌደራል ሕገ መንግስት ላይ ሊካተት አይገባም፤ ክልሉ በራሱ ሕገ መንግስት ማካተት ይችላል”፣ “አዲስ አበባ ሕብረ ብሔራዊ ከተማ ናት እያልን ለአንድ ክልል ልዩ ጥቅም የሚያስገኝ ውሳኔ አናስተላልፍም” የሚሉና ሌሎች ሀሳቦችን በማንሳት ምክረ ሀሳቡ በቃለ ጉባኤ ላይ መካተት እንደሌለበት መከራከራቸውን ሰምተናል። ይህ የሀሳብ ልዩነት በተለያዩ ግዜያት የምክክሩ ሂደት እንዲቋረጥ አድርጎ መቆየቱም የተነገረ ሲሆን፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ምክረ ሀሳብ እንዲያጠናቅሩ የተመረጡ ተመካካሪዎችን በማነጋገር ምክረ ሀሳቡ እንደ አማራጭ ተቀምጦ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንዲሸጋገር መደረጉን የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ሕጋዊ ቁመና ጉዳይ
በስልታዊ ቡድኖች ደረጃ በተካሄዱ የምክክር ሂደቶች ጥቂት በማይባሉ ነጥቦች ዙሪያ “ስምምነት” ላይ ስለመደረሱ የነገሩን ምንጮች፤ አዲስ አበባ ራሷን በራሷ የምታስተዳድር የፌደራል ከተማ ትሁን የሚለው አማራጭ በበርካቶች ዘንድ ድጋፍ ያገኘ መሆኑን ጠቁመዋል። የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እና መቀመጫ ትሁን የሚለውን ምክረ ሀሳብ ያቀረቡ ተመካካሪዎች ደግሞ፤ ምክረ ሀሳቡ በሥራ ቡድን ደረጃ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ጠይቀዋል። ይህም በሥራ ቡድን ደረጃ ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚቀርበው ጉዳይ፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ትሁን? ወይስ አትሁን?” የሚለው መሆኑን የሚጠቁም ነው ሲሉ ምንጮች ነግረውናል።
ጉዳዩ ወደ ድምጽ አሰጣጥ ከማምራቱ በፊት ጊዜ ተወስዶ ንግግር እንዲደረግበት የጠየቁ ተመካካሪዎች፤ ድምጽ ወደ መስጠት ሂደት ከተገባ ከቁጥጥር ውጭ የሚሆኑ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ መናገራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። የተመካካሪዎች መታወቂያ የተሰጠበት መንገድ፣ በተመካካሪዎች ላይ የሚደርስ “ግፊት” እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች የምክክሩን ሂደት ሊረብሹ ይችላሉ የሚል ስጋት መኖሩንም ሰምተናል።
የብልጽግና ፓርቲ አባላት ያሳዩት የተለያ የአቋም
በአዲስ አበባ ሕጋዊ አቋም ዙሪያ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ያሳዩት የአቋም ልዩነት አሁንም መቀጠሉ ተስተውሏል። እስካሁን በተካሄዱ የምክክር ሂደቶች በስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ከፍተኛ የሀሳብ ልዩነትና ሙግት ያሳዩ የፓርቲው አባላት መኖራቸውን የገለጡልን ምንጫችን፤ ሁኔታው ለፓርቲው “የውስጥ ሰላም” የሚያሰጋ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህንን ያስተዋሉ ሌሎች የፓርቲው አባላት፤ በግልጽ የታየ የሀሳብ ልዩነት ላይ የፓርቲው አባላትን “እያሸማገሉ” መሆናቸውንም ሰምተናል። በተደረጉ የሽምግልና ጥረቶች “የተወሰነ” ለውጥ ታይቷል ያሉት ምንጫችን፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ትሁን” የሚለው ምክረ ሀሳብ በዚህ የሽምግልና ሂደት እንዲቀር መደረጉን ጠቁመዋል። በቀጠለው የሽምግልና ሂደት “የጋራ ተጠቃሚነትን” የሚያረጋግጥ ውሳኔ እንዲወሰን ግፊት እየተደረገ ቢሆንም፤ በስብሰባ አዳራሾች ያለው ውጥረት ግን መቀጠሉን ነግረውናል።
ፕሬዝዳንት የሚመራው ፓርላመንታዊ ሥርዓት
በመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ አጀንዳ ውስጥ ከቀረቡ ንዑስ አጀንዳዎች መካከል እንዱ በሆነው “የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት” ውስጥ ከቀረቡ ምክረ ሀሳቦች መካከል፤ “በፕሬዝዳንት የሚመራ ፓርላመንታዊ ሥርዓት” የሚለው አማራጭ በበርካቶች ድጋፍ ማግኘቱን ዋዜማ ሰምታለች። ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ በሚል የቀረበ ምክረ ሀሳብ መኖሩንም የገለጡልን ምንጮች፤ ቀዳሚው አማራጭ ሚዛን መድፋቱን ጠቁመዋል።
በፓርላማው የሚሾመው ፕሬዝዳንት የስድስት ዓመታት የስልጣን ዘመን እንዲኖረው የሚልና አንድ ግለሰብ ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ እንደማይችል የሚጠቁም ምክረ ሀሳብ መነሳቱንም የሰማን ሲሆን፤ ይህ ምክረ ሀሳብ ምርጫ በየስድስት ዓመቱ እንዲካሄድ ሊያደርግ የሚችል ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ፓርቲያቸው ብልጽግና፣ የመሪዎች የስልጣን ጊዜ በሕግ እንዲወሰን ለማድረግ ያስችላል ያለውን አጀንዳ ለኮሚሽኑ ማስመዝገቡን መናገራቸው ይታወሳል።
እንዲጠብቅ የተደረገው ቁጥጥር
በተለያዩ ምክረ ሀሳቦች ዙሪያ የሀሳብ ልዩነት በተስተዋለባቸው የሥራ ቡድኖች ላይ ያለው ቁጥጥር መጠናከሩን ምንጮች ነግረውናል። የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባልደረቦች በተለይም፤ በፌደራል ከተሞች ጉዳይ፣ በሀገር ግንባታ እንዲሁም በመንግስት አደረጃጀት አጀንዳዎች ላይ እየተመካከሩ በሚገኙ የሥራ ቡድኖች ላይ የሚያደርጉትን ቁጥጥር ማጠናከራቸውን ዋዜማ ሰምታለች። በሥራ ቡድኖቹ መሰብሰቢያ አዳራሾች መግቢያና መውጫ በሮች ላይ በርከት ያሉ የአገልግሎቱ ባልደረቦች እንደሚንቀሳቀሱ የገለጡት ምንጮች፤ ወደ አዳራሹ የሚገቡ ተመካካሪዎች መታወቂያቸው እየታየና እየተረጋገጠ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ለቁጥጥሩ መጥበቅ እንደ ምክንያት የቀረበው ጉዳይም፤ “በሌሎች አጀንዳዎች ላይ እንዲመካከሩ የተመደቡ ተመካካሪዎች ሳይፈቀድላቸው ወደ ቡድኖቹ መሰብሰቢያ አዳራሾች እየገቡ ነው” የሚል መሆኑን ሰምተናል።
ቅሬታ ያቀረቡ ፓርቲዎች
በምክክሩ ሂደት ላይ አስተውለናል ያሉትን ክፍተት አስመልክቶ ለኮሚሽኑ ቅሬታ ያቀረቡ ፓርቲዎች መኖራቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ አረጋግጣለች። የምክክሩ ሂደት ወደ ሦስተኛውና ውሳኔ ወደሚሰጥበት ምዕራፍ መሸጋገሩን ተከትሎ፤ በምክክሩ ሂደት ታይተዋል ያሏቸውን ክፍተቶች አስመልክተው ለኮሚሽኑ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሶስት ፓርቲዎች፤ ራሳቸውን ከምክክሩ እስከማግለል የደረሰ ውሳኔ ሊያሳልፉ እንደሚችሉ ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን ሰምተናል።
የብሔር ዕውቅና፣ የአስተዳደር መዋቅር እና የክልልነት ጥያቄ ያነሱ ፓርቲዎች፤ ጥያቄዎቻችን በዝርዝር እንዳይመዘገቡ፣ ይልቁንም በጥቅል “የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ ይገባል” በሚል አረፍተ ነገር ብቻ እንዲጠቃለሉ ተደርጓል የሚል ቅሬታ ያላቸው ሌሎች ፓርቲዎችም፤ ለኮሚሽኑ ቅሬታቸውን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ዋዜማ ሰምታለች። ለዋዜማ ቃላቸውን የሰጡ የአንድ ፓርቲ ሊቀ መንበር፤ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ካሏቸው ሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለኮሚሽኑ ቅሬታ ለማቅረብ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጠዋል። ጥያቄያቸው ተገቢውን ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ፓርቲያቸው አቋሙን በመግለጫ በማሳወቅ ራሱን ከምክክሩ እንደሚያገል ጠቁመዋል።
ሥራ ሊጀምሩ የተቃረቡት አደረጃጀቶች
የምክክር ሂደቱ ውሳኔ የሚሰጥበት ሶስተኛ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተከትሎ፤ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ ወሳኝ ሚና ያላቸው ሁለት አደረጃጀቶች ሥራ ሊጀምሩ ተቃርበዋል። በሥራ ቡድን ደረጃ የሀሳብ ልዩነት በፈጠሩ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ላይ እንዲደረስ የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠውና አስታራቂ ሽማግሌዎችን እና ምሁራንን እንዳቀፈ የተነገረለት “የስምምነት ግብረ ኃይል” አንዱ አደረጃጀት ሲሆን፤ በርካታ ጥያቄዎች ሲቀርቡበት የነበረውና የአባላቱን ቁጥር ከ211 ወደ 336 ያሳደገው “የክልል ተወካዮች ጉባኤ” ደግሞ ሌላኛው አደረጃጀት ነው።
ኮሚሽኑ የክልል ተወካዮች ጉባኤ አባላትን ሐምሌ 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ማስመረጡ የሚታወስ ሲሆን፤ የጉባኤው አባላት እስካሁን ስብሰባ አለማድረጋቸውን ምንጮች ነግረውናል። ኮሚሽኑ ሐምሌ 29 ቀን ለተመካካሪዎች በሰጠው ማብራሪያ፤ የጉባኤው አባላት በተጣለባቸው ኃላፊነት ዙሪያ “በቅርቡ” ማብራሪያ እንደሚሰጣቸው ማሳወቁን ሰምተናል። [ዋዜማ]
