ዋዜማ- በተጠናቀቀው አመት የክረምት ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የታየው የዝናብ መዘግየትና እጥረት በሰው፣ በእንስሳት እና በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያሰከተለ ይገኛል። አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ በርካታ ዞኖችና ወረዳዎች ድርቁ አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ህብረተሰቡ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት እና ተጓዳኝ ችግሮች መዳረጉን ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት ተረድታለች።
ድርቁ ከተባባሰባቸው ክልሎች መካከል አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና አፋር የሚገኙበት ሲሆን፤ የዋዜማ ባልደረቦችም ከእነዚሁ ክልሎች ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የተመለከተ መረጃ አሰባስበዋል፡፡
አማራ ክልል
በአማራ ክልል በተጠናቀቀው አመት ክረምት ሙሉ በሙሉ ዝናብ ያልዘነበባቸው እና መደበኛ ዝናብ ያላገኙ አካባቢዎች በርካታ ቢሆኑም፣ በተለይ በዋግኽምራ ብሔረሰብ እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች የሚገኙ ቆላማ ወረዳዎች የከፋ ጉዳት አስተናግደዋል።
በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን በዝቋላ፣ ሰሃላ ሰየምትና አበርገሌ ወረዳዎች ድርቅ መከሰቱን ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎችና የረድዔት ሠራተኞች ያረጋገጠች ሲሆን፤ በተለይም በዝቋላና ሳህላ ቆላማ ቀበሌዎች ድርቁ የከፋ መሆኑን ተከትሎ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንሰሳት ሞተዋል ተብሏል። በዝቋላ ወረዳ ብቻ ከ6 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት ሲሞቱ፤ ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ውሃና መኖ ፍለጋ ወደ አጎራባች ወረዳዎች ተወስደዋል፡፡
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው በሰሃላ-ሰየምት ወረዳ ያሉ አርሶ አደሮች ተስፋን ሰንቀው የዘሩት እህል ዝናብ ባለመዝነቡ፤ ሰብሉ መውደሙን እና እንስሳቱም የሚመገቡት ማጣታቸውን ገልጸውልናል፡፡
የድርቁ መባባስ ህብረተሰቡን ለመፈናቀል የዳረገ ሲሆን፤ተፈናቃዮች በዋናነት ወደ ተለያዩ የወሎ ከተሞች ፣ ባህር ዳር ፣ ደብረ ብርሃን እና አዲስ አበባ ከተሞች ለመጓዝ ተገድደዋል፡፡
በአዲስ አበባ መገናኛ ‹‹የካ ሚካኤል›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጎዳናዎች ላይም፥ በርካታ ህጻናትን የያዙ ከዋግኽምራ የተፈናቀሉ ቤተሰቦችን ዋዜማ ተመልክታለች።
በሌላ በኩል፤በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ ምሥራቅ እና ምእራብ ጠለምት፣ በየዳ እና ጃናሞራ ወረዳዎች ቆላማ አስከፊ የተባለ ድርቅ ተከስቷል።
ድርቁ በትምህርት አሠጣጥ ሂደት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን የገለጹት በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች በማገልገል ላይ ያሉ መምህራን፤ በተለይም በሦስቱ የጠለምት ወረዳዎች የተማሪዎች ምዝገባ መጠን በ50 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳይሆኑ፤ የተማሪዎች ምገባ ለማስጀመር እና የትምህርት ግብዓቶችን ለማቅረብ ጥረት ቢደረግም፤ እስከ መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ከዞን እስከ ክልል ባሉ መንግሥታዊ አካላት የቀረበ ድጋፍም ሆነ የተሰጠ ግብረ መልስ የለም ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን እንደ ጤፍ ባሉ ከፍተኛ እርጥበት በሚፈልጉ ሰብሎች ላይ የምርት መቀነስ ስጋት ደቅኗል።
‹‹የዓመታት ድርቅ ያደከመው አርሶ አደር››
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ባሉ ወረዳዎች በክረምት ዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ በሰዎች፣ በሰብል እና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ሠምተናል።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሃዊ ጉዲና፣ ቦኬ እና ቡርቃ ዲንቱ ወረዳዎች ድርቁ በስፋት የሚታይ ሲሆን፤ በተለይም ቆላማ የሆነው ሃዊ ጉዲና ወረዳ ላለፉት አራት ዓመታት በቂ ዝናብ አለማግኘቱ አርሶ አደሩን ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጎታል። በአካባቢዎቹ ካጋጠመው ውሃ እጥረት በተጨማሪ፤ በመኖ እጥረት ሳቢያ የሚሞቱት የቤት እንስሳትም ቁጥርም ቀላል እንዳልሆነ የሚገልጹት አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች፤ ‹‹ከአራት ዓመት ጀምሮ በቂ ዝናብ አላየንም፤ የዘራነው እህል ሙሉ በሙሉ ደርቆብናል። አሁን ላይ እህሉም፣ የምንጠጣው ውሃም አልቆብን እኛም ከብቶቻችንም አብረን እየተራብን ነው›› ሲሉ በምሬት ይናገራሉ።
መንግሥትም ሆነ አጋር ድርጅቶች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የማያቀርቡ ከሆነ፣ ያጋጠመው ቀውስ ከዚህ በላይ ሊከፋ እንደሚችል በመግለጽ፤ ነዋሪዎቹ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ የአካባቢው ግብርና ሙሉ በሙሉ በክረምት ዝናብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል፡
በወረዳውበስፋት የሚዘሩት የበቆሎ፣ ቦሎቄ እና የስንዴ ምርቶች ሙሉ በሙሉ መድረቃቸውን ለዋዜማ ያስረዱት አርሶ አደሮች፤ በ2014 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቶ በነበረ ድርቅ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን አውስተዋል፡፡ ዘንድሮም ተመሳሳይ ችግር ይከሰታል የሚል ስጋት ውስጥ መግባታቸውን ነግረውናል፡፡
‹‹ሰዎች ሞተዋል››
በትግራይ ክልል የምሥራቃዊ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ደቡባዊ እና ማዕከላዊ ዞኖች (በተለይም የጭላ፣ ጽራዕ ወምበርታ፣ ህንጣሎ፣ ሳህርቲ እና ራያ አዘቦ ወረዳዎች ላይ ያጋጠመው ድርቅ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ በቆላማ አካባቢዎች የተዘሩ ሰብሎች ሙሉ በሙሉ በመድረቃቸው፤ የታቀደውን ያህል እህል መሰብሰብ ካለመቻሉም ባሻገር፤ የመጠጥ ውሃና የመኖ እጥረትም በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት እንዲሞቱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በየጭላ ወረዳ በድርቁ ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ እንስሳት መሞታቸውን የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካል ባለመኖሩ ወደ አጎራባች ወረዳዎች እየተፈናቀሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ አዲሱ የትምህርት ዘመን በተጀመረበት በዚህ ወቅት፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ግን ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ መቀለ እና ሽሬ ከተሞች እንደሚያቀኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ፤ በኢሮብ ወረዳ በሚገኙ አብዛኞቹ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ 5 ነባር የውኃ ምንጮች ሙሉ በሙሉ መድረቃቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በተለይም በ«አርአ» ፣ ‹‹ወረአትለ›› እና ‹‹እንዳልጌይዳ›› ቀበሌዎች ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት ዝናብ ባለመዝነቡ እንስሳት መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከእንስሳቱ ባሻገር በወረዳው «አጋራሌ» ቀበሌ በርሃብ ሳቢያ የ 2 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ሠምተናል፡፡
አፋር ክልል
በአፋር ክልል ዞን 1 እና ዞን 2 እንደ ኤሊዳዓር፣ ኮሪ፣ ቢዱ፣ ተሩ እና እረብቲ ባሉ ወረዳዎች የተከሰተው ድርቅ፤ የበርካታ አርብቶ አደሮችን ህይወት አመሳቅሏል፡፡
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው በክልሉ ዞን 2 አብአላ ወረዳ በሚገኘው ኡርኩዲ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርብቶ አደር እንደተናገሩት፤ በርካታ እንስሳት በውኃ ጥምና በመኖ እጥረት ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ ‹‹ከብቶቻችን፣ በጎቻችን፣ ፍየሎች በሙሉ አለቁብን፤ የቀሩትም በየቤቱ ሞታቸውን እየተጠባበቁ ነው›› ያሉት አርብቶ አደሩ፤ ‹‹እንዲህ አይነት ድርቅ አይተን አናውቅም፤ መጪው ጊዜ ያስፈራል›› ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው በቦቴዎች የሚደረገው የመጠጥ ውሃን የማከፋፈል ስራ ከችግሩ ስፋት አንፃር እጅግ ውስን በመሆኑ፣ ማኅበረሰቡ ውሃ ለማግኘት ረጅም ርቀት በእግር እንደሚጓዝ አብራርተዋል፡፡
ታዳጊ ሴቶችን እንደ ሸቀጥ
የድርቅ ክስተት ባጋጠማቸው እና ችግሩ በተባባሰባቸው የኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሐረርጌ ዞን፣ ትግራይ ክልል ራያ ዓዘቦ እና የአፋር ወረዳዎች ውስጥ በድርቅ ምክንያት ብዙ እንስሳት የሞቱባቸው፣ ሰብል የወደመባቸው አሊያም ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተዳረጉ ቤተሰቦች፤ ለጋብቻ ያልደረሱ ሴት ልጆችን ፤ የተሻለ የኑሮ አቅም ላላቸው ቤተሰቦች ለጋብቻ እንደሚያቀርቡ ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች፡፡
ታዳጊ ሴት ልጆች እድሜያቸው ለጋብቻ ሳይደርስ ለአካባቢው የተሻለ ሀብት አላቸው ለሚባሉ ሰዎች ወይም ከተማ ለሚኖሩ ግለሰቦች በጥቅም መልክ የሚሰጡበት እና ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው አስገዳጅ ጋብቻ ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉበት ሁኔታም አለ፡፡
ተከታታይ ማስጠንቀቂያዎች
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከ 1 ወር በፊት፤ በኢትዮጵያ እና በጎረቤት ሀገራት የሚታየው የዝናብ እጥረት እና የድርቅ አደጋ በሚቀጥሉት ወራት ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቅቋል። ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ባወጣው መረጃ መሠረት፤ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ውስጥ በአጠቃላይ ከ48 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ ከ40 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት ቀውስ የተጋለጡ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ከኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ባወጣው የጋራ ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ በ2018 ዓ.ም የክረምት ወቅት የታየውን የዝናብ መዘግየትና እጥረት ተከትሎ፣ በአገሪቱ በሚገኙ 114 ወረዳዎች ውስጥ የከፋ የድርቅ ሥጋት መደቀኑን ጠቁሟል፡፡
ከእነዚህ አስቸኳይ የድርቅ ማስጠንቀቂያ የተሰጠባቸው 114 ወረዳዎች መካከል 84 የሚሆኑት በዋናነት በአማራ፣ በአፋር፣ በትግራይ እና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ አብዛኞቹም በአገራዊ መደብ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አጣዳፊ የሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ክልሎች ተብለው ተለይተዋል። ድርጅቱ እ.ኤ.አ. ከሰኔ 2026 እስከ መጋቢት 2027 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በእነዚህ ከፍተኛ የድርቅ ስጋት በተደቀነባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ 4 ነጥብ 66 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የሕይወት አድን ድጋፍ ለማድረስ የ50 ሚሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እየታየ ያለው የከፋ የዝናብ እጥረት እና የድርቅ ክስተት፤ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሁለት ሳምንታት በፊት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የአየር ንብረት ተመራማሪው ድሪባ ቆሪቻ (ዶ/ር) ከሰጡት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያ ጋር ጋር ተያያዥነት አለው። ፈውስ ኔት የአየር ንብረት ሥርዓቶችን፣ ያልተለመዱ የአየር ጠባይ ለውጦችን እና በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ተፅዕኖዎች በመተንተን፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን የሚሰጥና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትንና ተቋማትን የሚያማክር ተቋም ሲሆን፤ ከግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተቋሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአየር ንብረት ተመራማሪ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ድሪባ ቆሪቻ (ዶ/ር)፤ የኤልኒኖ የአየር ንብረት ለውጥ የደቀነውን ስጋትና ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት የተመለከተ፣ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ የዘንድሮው የኤል ኒኖ ክስተት ቀደም ሲል ካጋጠሙት የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ሱፐር ኤል ኒኖ ከሁለት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አጋጥሞ እንደነበር ያስታወሱት ተመራማሪው፥ በዚያም ምክንያት ከፍተኛ የወባና ሌሎች ወረርሽኞች በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል እና በሌሎችም ቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከስተው እንደነበር ገልጸዋል።
‹‹ጎርፍ ይከሰታል ፤ ጎርፉን ተከትሎ ከፍተኛ የኮሌራ ወረርሽኝ ሊቀሰቀስ ይችላል፤ ይህም የወባ በሽታን መስፋፋት የሚያስከትል እና በተለይም በአርብቶ አደሩ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ይሆናል›› በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡ ከጎርፍ መከሰት ጋር ተያይዞ፤ የሪፍት ቫሊ ትኩሳት በቫይረስ አማካኝነት ሊከሰት እንደሚችል የገለጹት ተመራማሪው፤ ሰዎችን እና እንስሳትን (ከብቶች፣ በጎች፣ ፍየሎችን እና ግመሎችን) የሚያጠቃ በሽታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ [ዋዜማ]
