ዋዜማ- ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በተካሄደው አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ የምክክር ስብሰባ ላይ  አለመሳተፏን ዋዜማ ሰምታለች።

እ.ኤ.አ ህዳር ወር፤ 2026 በቱርክ አንታሊያ መዲና በሚደረገው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ እና በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለአፍሪካውያን የተሳካ ለማድረግ ሰፊ ምክክር በተደረገበት የአዲስ አበባው መድረክ ላይ፤ የኢትዮጵያ ተወካዮች ሳይሳተፉ መቅረታቸው ጥያቄ ፈጥሯል፡፡    

ኢትዮጵያ የአፍሪካን አህጉር በመወከል 32ኛውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ-32) እንድታዘጋጅ የተመረጠች ቢሆንም፤ በአዲስ አበባ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) አዘጋጅነት ከጳጉሜ 1 እስከ ጳጉሜ 3 ቀን 2018 ዓ.ም «ከቃል ወደ ተግባር» በሚል መሪ ቃል በተካሄደው 14ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረትና ልማት ጉባዔ መክፈቻ እና መዝጊያ ላይ የኮፕ-32 ብሔራዊ ኮሚቴ ከፍተኛ አመራሮች አለመገኘታቸው ጥያቄ አስነስቷል።

ይህ አህጉራዊ መድረክ አፍሪካ በመጪዎቹ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎች ላይ የምታቀርባቸውን የጋራ የድርድር አቋሞች ለመቅረጽ ያለመ ነው። አህጉሪቱ በተለይም ከአንድ ዓመት በፊት በብራዚሏ ቤሌም በተካሄደው ኮፕ-30 ያሳካቻቸውን ውጤቶች በመገምገም፤ ከሁለት ወራት በኋላ በቱርክ አንታሊያ በሚካሄደው 31ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ-31) እና በቀጣዩ ዓመት በአዲስ አበባ በሚካሄደው ኮፕ-32 ተከታታይ ጉባዔዎች ላይ የምትይዛቸውን ስልታዊ አቋሞች ለመወሰን ለ 3 ቀናት ሲመክር የቆየው ጉባኤው፤ ይህ ስብሰባ ጳጉሜ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ተጠናቅቋል።

በዚህ ጉባዔ የመክፈቻና የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ሆኑ በቀጣዩ አመት የሚካሄደው የኮፕ-32 ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጉባዔው ዕጩ ፕሬዚዳንት የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ሳይገኙ ቀርተዋል።

ይህም በጉባዔው ተሳታፊዎችና ዲፕሎማቶች ዘንድ ትልቅ ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን፤ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንጋፋ የአየር ንብረት ጉዳዮች ባለሙያና ተደራዳሪ፤ ኢትዮጵያ የጉዳዩ ባለቤት ሆና ቀዳሚውን ሚና ልትጫወት በሚገባት በዚህ አህጉራዊ መድረክ ላይ አለመገኘቷ እንዳሳዘናቸው ለዋዜማ ተናግረዋል። መድረኩ ተከታታይ የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔዎችን የሚመለከቱ ሳይንሳዊና ሙያዊ ትንታኔዎች የሚቀርቡበት እንዲሁም አህጉራዊ አቋሞች የሚያዙበት ሆኖ ሳለ፤ አፍሪካን ወክላ ቀጣዩን ዓለም አቀፍ ጉባዔ የምታዘጋጅ ሀገር አንድም ከፍተኛ ባለሥልጣን አለመላኳ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመክፈቻና መዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ስላልተገኙበት ምክንያት በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ሆኖም፤ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና በጉባኤው ተሳታፊ የሆኑ አንጋፋ ባለሞያ እንደሚሉት፤ ስብሰባው የኮፕ-32 አዘጋጅ ኮሚቴ ባለመሆኑ የከፍተኛ አመራሮች መገኘት ግዴታ እንዳልነበረና በአሁኑ ወቅት ያለው የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ሥራ ውጥረትም ለባለሥልጣናቱ አለመገኘት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሠዋል፡፡

‹‹ከፍተኛ አመራሮቹ በሥራ ተወጥረው እንጂ ከፍላጎት ማነሥ አይደለም ያልተገኙት፤ ሌላ ምንም ምክንያት የላቸውም›› ያሉት እኝሁ አንጋፋ ባለሞያ፤ እርሳቸውም በጉባኤው መገኘታቸውን በመጥቀስ የኢትዮጵያ የቴክኒክ ባለሞያዎችና የሲቪል ማህበራት ተወካዮች ግን በውይይቶቹ ላይ ተሳትፈዋል ሲሉ ተናግረዋል። ከየትኛውም የመንግሥት መስሪያ ቤት በላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ተወካዮቹን መላክ እንደነበረበት ገልጸው፤ የተቋሙ ተወካዮች ያልተገኙበትን ምክንያት እንደማያውቁ አክለዋል፡፡

የብሔራዊ ኮሚቴው አባል የሆኑ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላኛው ከፍተኛ ባለሙያ በበኩላቸው፤ በጉባዔው ላይ አለመሳተፋቸውን አረጋግጠው፤ ምክንያቱን ግን ከመናገር  ተቆጥበዋል። ዋዜማ የኮፕ-32 ጉባዔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ የሆነውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ፤ ኢትዮጵያ በጉባዔው ላይ ያልተሳተፈችበትን እንዲሁም ተቋሙ ተወካዮቹን ያልላከበትን ምክንያት ብትጠይቅም፤ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።

አፍሪካ በካርቦን ልቀት ላይ የጎላ ድርሻ ባይኖራትም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች እንደሆነ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ተገልጿል። ጉዳቱን ለመቋቋም እስከ እ.ኤ.አ. 2030 ከሚያስፈልገው 277 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ እስካሁን የተገኘው 11 በመቶ ብቻ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቋቋም፣ ለመከላከል እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመላመድ የሚረዱ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚመደብ የገንዘብ አቅርቦት (የማላመጃ ፈንድ) በሦስት እጥፍ እንዲያድግና ያደጉ ሀገራት የገቡትን የፋይናንስ ቃል እንዲፈጽሙ ተጠይቋል። በተጨማሪም ወደ ንጹሕ ኢነርጂ የሚደረገው ሽግግር አህጉሪቱን ለብዝበዛ የሚያጋልጥ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።

ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ-32) በቀጣዩ ዓመት ህዳር 2027 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደምታስተናግድ ይታወቃል። ሀገሪቱ ይህንን ታላቅ ጉባዔ በስኬት ለማስተናገድ ብሔራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ አዋቅራ ወደ ሥራ መግባቷን ቀደም ብላ ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ የዚሁ ኮሚቴ አባላት የልምድ ልውውጥ ለማድረግ በቅርቡ ወደ አዘርባጃን አቅንተው እንደነበር ይታወሳል። [ዋዜማ]