ዋዜማ- ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ37ኛ ቀን ውሎው ሊያካሂድ የነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ሳይካሄድ ቀርቷል። ኮሚሽኑ በተመካካሪዎች የቀረቡ 476 ምክር ሀሳቦች ነሐሴ 14 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በጠቅላላ ጉባኤ እንደሚጸድቁ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፤ ኦሮሚያ ክልልን የወከሉ ተመካካሪዎች ባቀረቡት ቅሬታ ምክንያት ጉባኤው ሳይካሄድ መቅረቱን ምንጮች ነግረውናል።
ነሐሴ 13 ቀን ምን ተፈጠረ
በስምንቱም አጀንዳዎች ዙሪያ የተጠናቀሩና የተመሳከሩ 476 ምክረ ሀሳቦች ነሐሴ 13 ቀን በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በሥራ ቡድን ደረጃ ለሁሉም ተመካካሪዎች ቀርበዋል። ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳቦች ውሳኔ የሚያገኙበትን አሠራር ቀደም ብሎ አሳውቆ የነበረ ቢሆንም፤ አሠራሩን ተግባራዊ ሳያደርገው ቀርቷል። በሰነድ ተዘጋጅቶ በቀረበው አሠራር ምትክም፤ ምክረ ሀሳቦች ከነ አማራጮቻቸው በሥራ ቡድን ደረጃ ጸድቀው በቀጥታ ወደ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲቀርቡና በጭብጨባ እንዲጸድቁ መወሰኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በተለያዩ ጊዜያት በሰጧቸው መግለጫዎችና፤ ለተመካካሪዎች ባቀረቧቸው ማብራሪያዎች ገልጠዋል። የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ ነሐሴ 13 ቀን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫም፤ በሥራ ቡድን ደረጃ የቀረቡት ምክረ ሀሳቦች ለጠቅላላ ጉባኤ ቀርበው እንደሚጸድቁ ገልጠው ነበር።
በሁሉም የሥራ ቡድኖች ሁሉም ምክረ ሀሳቦች ከተነበቡ በኋላ፤ ነሐሴ 14 ቀን በጠቅላላ ጉባኤ “በጭብጨባ” እንደሚጸድቁ በኮሚሽኑ ባለሙያዎች መነገሩን የገለጡት የዋዜማ ምንጮች፤ ከዚህ ሂደት በኋላ አብዛኞቹ ተመካካሪዎች ወደ ማረፊያቸው ማቅናታቸውን ነግረውናል።
ይሁንና 300 የሚደርሱ ኦሮሚያ ክልልን መወከላቸውን የገለጡ ተመካካሪዎች ቅሬታ አለን ሲሉ ኮሚሽነሮች እንዲያነጋግሯቸው መጠየቃቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ሦስት ኮሚሽነሮች የተመካካሪዎችን ቅሬታ መቀበላቸውን ነግረውናል። ተመካካሪዎቹ በአዲስ አበባ ጉዳይ በቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ዙሪያ ቅሬታ እንዳላቸው፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መሆኗን” የሚያረጋግጥ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ አማራጭ የሌለው ምክረ ሀሳብ ሆኖ ካልተካተተ ከምክክር ሂደቱ እንደሚወጡ ለኮሚሽነሮች መናገራቸውን ሰምተናል። ኮሚሽነሮችን ያነጋገሩት ተመካካሪዎች በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል እስከ ምሽት 3 ሰዓት ድረስ እርስ በእርስ ሲመካከሩ ማምሸታቸውን የገለጡል ምንጮች፤ ኮሚሽነሮች ደግሞ ስብሰባ ሳያካሂድ የቆየው የክልል ተወካዮች ጉባኤ ቀደም ብሎ ዕቅድ ባይያዝለትም ነሐሴ 14 ቀን እንዲሰበሰብ ለጉባኤው አባላት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ነግረውናል።
ነሐሴ 14 ቀን ጠዋት
ነሐሴ 13 ቀን ለተመካካሪዎች በተላለፈው መልዕክት መሠረት ተመካካሪዎች በጠቅላላ ጉባኤው ለመሳተፍ ወደ ምክክር አዳራሽ ቢያቀኑም፤ የክልል ተወካዮች ጉባኤ ስብሰባ ቀደም ብሎ እንዲካሄድ መወሰኑ ተነገራቸው ። በኮሚሽኑ ውሳኔ ግራ የተጋቡ ተመካካሪዎች፤ ኮሚሽኑ ከምክረ ሀሳብ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ጋር የተገናኙ አካሄዶችን ሳይከተል መቅረቱን በማንሳት የክልል ተወካዮች ጉባኤ እንዲካሄድ የተወሰነበትን ምክንያት ጠይቀዋል። የኮሚሽኑ ባለደረቦችም ጉባኤው እንዲሰበሰብ የተደረገው ከኦሮሚያ ክልል ተመካካሪዎች የቀረበውን ቅሬታ መሠረት በማድረግ ኮሚሽኑ ባስተላለፈው ውሳኔ ምክንያት መሆኑን የሚያመላክት ምላሽ መስጠታቸውን ሰምተናል።
የጉዳዩን አሳሳቢነት የተመለከቱ ተመካካሪዎች በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለው እርስ በእርስ ሲነጋገሩና ሲመካከሩ እንደነበር ያስተዋሉ ምንጮች ለዋዜማ እንደገለጡት፤ ቀጥዩን ሂደት የተመለከቱ መደበኛ ያልሆኑ ውይይቶች ተካሂደዋል። ለስብሰባ የተጠሩት የክልል ተወካዮች ጉባኤ አባላት ስብሰባ ከመጀመራቸው በፊትም ጉባኤው የተጠራበትን ምክንያት በተለያየ መንገድ መጠየቃቸውን ሰምተናል።
ሙሉ የጉባኤው አባላት ባልተገኙበትና ውጥረት በነገሰበት ስብሰባም፤ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች የኦሮሚያ ክልል ተወካይ ተመካካሪዎች ያቀረቡትን ቅሬታ ለጉባኤው አባላት ማቅረባቸውን ገልጠዋል። የጉባኤው አባል የሆኑት የሁሉም ክልሎች ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የሁለቱ ከተሞች ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት በተካሄደው ስብሰባ፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መሆኗን የሚያረጋግጥ ድንጋጌ በሕገ መንግስቱ እንዲካተት” የሚል አማራጭ የሌለው ምክረ ሀሳብ በመጨረሻው የምክረ ሀሳብ ሰነድ እንዲካተት መጠየቁን ሰምተናል።
በፌደራል ከተሞች ጉዳይ የተጠናቀረው የምክረ ሀሳብ ሰነድ
ኮሚሽኑ ተግባራዊ ባደረገው አሠራር መሠረት በሥራ ቡድን ደረጃ ጸድቆ የጠቅላላ ጉባኤውን መካሄድ እየተጠባበቀ የሚገኘው የምክረ ሀሳብ ሰነድ፤ በአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ጉዳይ ሁለት አማራጭ ምክረ ሀሳቦችን መያዙን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ምክረ ሀሳብ ክልሎች ርዕሰ ከተማቸውን ራሳቸው መምረጥ እንደሚችሉ የሚያስቀምጥ “የመርህ ድንጋጌ” በሕገ መንግስቱ እንዲካተት የሚጠይቅ ነው። ሁለተኛው ምክረ ሀሳብ ደግሞ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ከተማዋንና ክልሉን የሚመለከቱ ጉዳዮች በሕግ ይወሰናሉ” የሚል ድንጋጌ እንዲካተት የሚጠይቅ ነው።
ይህ ምክረ ሀሳብ ኮሚሽኑ ተግባራዊ ባደረገው አሠራር መሠረት በጋራ ማረጋገጫ ቡድን ተረጋግጦና በአጀንዳው ዙሪያ በተመካከረው የሥራ ቡድን የጸደቀ ሲሆን፤ ኦሮሚያ ክልልን መወከላችውን የገለጡት ተመካካሪዎች ያቀረቡት ቅሬታ ከምክክር ሂደቱ የወጣና፣ የምክክር ሂደቱን ወደ ኋላ የሚመልስ ነው የሚል ተቃውሞ ማስነሳቱን ሰምተናል።
የአማራ ክልል ተወካዮች ምን አሉ?
በክልል ተወካዮች ጉባኤ ስብሰባ ላይ የተገኙ የአማራ ክልል ተወካዮች፤ “ጉባኤው ለስብሰባ መጠራቱ የምክክር ሂደቱን ያልተከተለና ከአሠራር ውጭ የተደረገ ነው” ሲሉ መናገራቸውን ሰምተናል። የምክረ ሀሳብ ውሳኔ አሰጣጥ ተግባራዊ አለመደረጉን ተከትሎ የክልል ተወካዮች ጉባኤ እንዲሰበሰብ የሚያደርግ ምክንያት የለም፣ ጉባኤው ይጠራ ቢባል እንኳን የጋራ ማረጋገጫ ቡድን ሥራውን ከማከናወኑ በፊት እንጂ ቡድኑ ሥራውን ካጠናቀቀና ያደራጀውን ምክረ ሀሳብ ለሥራ ቡድኖች አቅርቦ እንዲጸድቅ ካደረገ በኋላ መሆን የለበትም በሚል የኮሚሽኑ ውሳኔ ላይ የመረረ ቅሬታ አሰምተዋል።
የክልል ተወካዮች ጉባኤ ጉዳይ
የተገቢነት ጥያቄ የተነሳበት የክልል ተወካዮች ጉባኤ ስብሰባ ኮሚቴ በማቋቋም ተጠናቅቋል። በጉባኤው የተገኙ የክልል ፕሬዝዳንቶችና ሌሎች ተመካካሪዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ከሰነዘሩ በኋላ፤ ጉዳዩን በጥልቀት የሚመለከትና መፍትሄ ያፈላልጋል የተባለለትን ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን፤ በኮሚቴው የ11ዱ ክልሎች ፕሬዝዳንቶች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ሶስት የትግራይ ክልል ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤው አባል የሆኑ አምስት የሃይማኖቶች ተወካዮች፣ 3 የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራሮች፣ ሁለት የወጣቶች ተወካዮች ተካትተዋል።
ኮሚቴው በከተሞች አጀንዳ ዙሪያ ከጥቃቅን ቡድን ጀምሮ የተካሄደውን የምክክር ሂደት ተመልክቶ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርብ መጠየቁን የነገሩን ምንጮች፤ ስለቀጣዩ ሂደት ግልጽ አቅጣጫ አለመቀመጡን ነግረውናል።
የአማራ ክልል ተወካዮች ያቀረቡት ቅሬታ
የአማራ ክልል ተወካዮች በተለያዩ ጊዜያት በምክክሩ ሂደት ተስተውለዋል ያሏቸውን ክፍተቶች በሚመለከት ለኮሚሽኑ ቅሬታ ማቅረባቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ለቀረቡ ቅሬታዎች ምላሽ አለመሰጠቱንና በአሁናዊ የምክክር ሂደቱ ዙሪያ ያላቸውን ቅሬታ አስመልክቶ የኮሚሽኑን ኮሚሽነሮች ማነጋገራቸውን ሰምተናል። ተወካዮቹ “የምክክር ሂደቱ ተጥሶ ወደ ኋላ እንዲመለስ መደረግ የለበትም፣ የክልል ተወካዮች ጉባኤ የሚጠራበት አሠራር የለም፣ ኮሚሽኑ በዘረጋው አሠራር መሰረት በሥራ ቡድን የጸደቀ ምክረ ሀሳብ ዳግም የሚታይበት ምክንያት የለም፣ ኮሚሽኑ ወደ መደበኛ የምክክር ሂደቱ ተመልሶ ጠቅላላ ጉባኤ የማያካሂድ ከሆነ ራሳችንን ከምክክሩ እናገላለን” የሚሉና ሌሎች የቅሬታ ሀሳቦችን ማቅረባቸውን ምንጮች ነግረውናል።
የኮሚሽነሮች ምላሽ
የአማራ ክልል ተወካዮችን ያነጋገሩት ኮሚሽነሮች፤ ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱን የጣሰ ተግባር አላደረገም የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ሰምተናል። ከኦሮሚያ ክልል ተወካዮች የቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲታይ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ለአማራ ተወካዮች እንደገለጡና የክልል ተወካዮች ጉባኤ እንዲጠራ የተደረገው ለዚሁ አላማ መሆኑን ማስረዳታቸውን ምንጮች ነግረውናል። በዚህም ከክልል ተወካዮች ጉባኤ ተውጣጥቶ የተቋቋመው ኮሚቴም ሁለቱ ወገኖች በጠቅላላ ጉባኤው ተሳትፈው የምክክር ሂደቱን በአግባቡ እንዲያጠናቅቁ የሚያደርግ ምክረ ሀሳብ እንዲያመነጩ መጠየቃቸውን፤ ከዚህ ባለፈ የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ያነሱትና የአዲስ አበባአ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫነት ጉዳይን የሚመለከተው ምክረ ሀሳብ ላይ በኮሚቴው አማካኝነት የሚደረግ ለውጥ አይኖርም ሲሉ ኮሚሽነሮች መናገራቸውን ምንጮች ነግረውናል። የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ፤ “በጠቅላላ ጉባኤ የሚነበብ ምክረ ሀሳብ ለሁሉም የሥራ ቡድኖች ቀደም ሲል የቀረበው እንጂ፣ አዲስ ምክረ ሀሳብ አይካተተም” በሚል ለአማራ ክልል ተወካዮች ንግግር ማድረጋቸውን ሰምተናል።
ከምክክር ሂደቱ ለመውጣት ያቆበቆቡ ተመካካሪዎች
ኮሚሽኑ ለተመካካሪዎች ባዘጋጃቸው የማረፊያ ቦታዎች ከሌሎች ጊዜያት የተለየ ድባብ መኖሩን ተረድተናል። ለሥራ ቡድኖች ከቀረቡት ከ476 ምክረ ሀሳቦች የሚጨመር አልያም የሚቀነስ ምክረ ሀሳብ ካለ ራሳቸውን ከምክክር ሂደቱ ለማግለል የወሰኑ ተመካካሪዎች ወደየመጡበት አካባቢ ለመመለስ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም ምንጮች ነግረውናል። እነዚህ ተመካካሪዎች ኮሚሽነሮች የአማራ ክልል ተወካዮችን ካነጋገሩ በኋላ፣ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሚቀርበውን ምክረ ሀሳብ ሰምተን ውሳኔያችንን እናሳልፋለን ብለው እየተጠባበቁ እንደሚገኙም ተረድተናል።
ለነሐሴ 15 ቀን የተቀጠረው ጠቅላላ ጉባኤ
ኮሚሽኑ ያቋቋመው ኮሚቴ የሚያቀርበውን ምክረ ሀሳብ መሰረት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚመለከት ስብሰባ ሰኔ 15 ጠዋት እንደሚደረግ የነገሩን ምንጮች፤ ጠቅላላ ጉባኤው ነሐሴ 15 ከሰዓት በኋላ ይደረጋል በሚል ለተመካካሪዎች እንደተነገራቸው ጠቁመዋል። ኮሚሽነሮች ለኦሮሚያ ክልል ተወካዮች፣ ለክልል ተወካዮች ጉባኤ አባላት እና ለአማራ ክልል ተወካዮች የሰጧቸው ማብራሪያዎችና ምላሾች የተለያየ ይዘት ያላቸው መሆናቸውን ተረድተናል ያሉት ምንጮቻችን፤ ሁለቱም ወገኖች በጠቅላላ ጉባኤ ተገኝተው የምክክር ሂደቱን እንዲያጠናቅቁ የማድረግ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ነግረውናል።[ዋዜማ]
