ዋዜማ – በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የሚኖሩ አርሶ አደሮች እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በጸጥታ ቀውስ እና በአስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ስጋት (አፈሳ) ውስጥ እንደሚገኙ ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ለመረዳት ችላለች። 

በተለይም በአካባቢው ሰፊ ምርት የሚገኝበት የበቆሎ እርሻ ወቅት ቢሆንም፣ ነዋሪዎች ፤ በተለይም አርሶአደሮች እስር እና የግዳጅ ወታደራዊ ስልጠናን በመስጋት እርሻቸውን ጥለው ወደ ሌላ አካባቢ ያሉ ዘመዶቻቸው ጋር እንደሚደበቁ ነግረውናል፡፡
 
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና በአካባቢው ሚሊሻዎች እየተፈጸመ ያለው የጅምላ አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ነው። 

ሰዎች በቤት ለቤት ፍተሻ ፣ከገበያ፣ ከሃይማኖት ስፍራዎች እና ከደስታና ከሐዘን ስነ-ስርዓቶች ላይ ጭምር ታፍሰው የሚወሰዱበት ሁኔታ እንዳለ በመጥቀስ፤ ሁኔታው በገጠሩ አካባቢ እየበረታ መምጣቱን ተከትሎ አንዳንድ ነዋሪዎች ወደ ከተማ ገብተው ለመደበቅ ቢሞክሩም፤ በከተማዎችም ውስጥ ተመሳሳይ ተግባር እየተፈጸመ በመሆኑ ‹‹መሸሸጊያ›› እንዳጡ ተናግረዋል።


ምልመላውም ሆነ ከዚያ በኋላ የሚሰጠው ስልጠና የጤና እክል ያለባቸውን ዜጎች እንኳ ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን አንድ ነዋሪ ሲገልጹ፤ ‹‹አንድ ከቤቱ የወሰዱት ጎረቤቴ የሚጥል በሽታ አለበት፤ ዘወትር መድኃኒት ይወስዳል። ታፍሶ ከተወሰደ በኋላ ለጸጥታ ኃይሎቹ ስለ ህመሙ ቢያስረዳም፣ የህክምና ማስረጃውን የሚያይለት ወይም አቤቱታውን የሚሰማው አካል አላገኘም”፤ ከብዙ የደብዳቤ ምልልስ እና እንግልት በኋላ ነው የተለቀቀው›› በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።


የግዳጅ ስልጠና እና የመብት ጥሰቶች


በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ዶንጎሮ ወረዳ፣ የጸጥታ ሁኔታው ይበልጥ አሳሳቢ መሆኑን የሚገልጹት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች፤ በወረዳው ‹‹አካባቢውን ከሸኔ መከላከል›› በሚል ምክንያት ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በኩል የሚደርስባቸው ጫና እንደበረታባቸው ነው ያስረዱት። 

በጉሎ እና ሀባቦ ጉዱሩ ወረዳዎች ያሉ በርካታ አርሶ አደሮች በግዳጅ ተይዘው ከሶስት እስከ አራት ቀናት የሚወስድ “የሚሊሻ ስልጠና” እንዲወስዱ እንደሚገደዱ ገልጸውልናል።

በተመሳሳይ መልኩ በዞኑ፤ በጃርደጋ ጃርቴ  ወረዳ፤ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሠ) ታጣቂዎች አርሶ አደሮችን እና ተማሪዎችን “ፋኖን መዋጋት አለባችሁ” በሚል በግዳጅ እያፈሱ ወደ ጫካ እንደሚወስዱ ተገልጿል። በዚህ መሰረትም ግጭት ውስጥ እንዲሳተፉ የተደረጉ 16 አርሶ አደሮች ህይወት ማለፉን ሰምተናል።


‹‹ጋቸናሲርና›› እና የሁለት ወገን ስጋት


በምስራቅ ወለጋ ዞን፤ በተለይም በጊዳ አያና እና ኪረሙ ወረዳዎች፤ ነዋሪዎች በተለይም አርሶ አደሩ ‹‹ጋቸና ሲርና››  (የስርዓት ጥበቃ) የተባለውን የሚሊሻ ስልጠና እንዲወስዱ በመንግስት እንደሚገደዱ ዋዜማ ከነዋሪዎች አንደበት ሰምታለች። ይህ ስልጠና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን ለመከላከል ያለመ መሆኑ ቢነገርም፤ አርሶ አደሩ ህብረተሰብ ግን በሁለት ጥይት መካከል መቆሙን ይገልጻል።


ነዋሪዎቹ ለዋዜማ እንደተናገሩት፤ በአንድ በኩል የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ‹‹ታጣቂዎችን ትደግፋላችሁ›› በሚል ያፍሷቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ታጣቂዎች ‹‹ለመንግስት መረጃ ታቀብላላችሁ›› በሚል ጥቃት ይሰነዝሩባቸዋል። ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ወረዳዎች በተጨማሪ፤ በአባይ ጮመን፣ ጂማ ራሬ፣ ጂማ ገነት፣ ሱሉለ ፊንጫ እና ኮምቦልቻ ወረዳዎች የሚኖሩ በተለይም አርሶ አደሮች ከሁለት ወራት በላይ ቤታቸውን ለቀው ጫካ ውስጥ ለመቆየት መገደዳቸውን ነው የተናገሩት።


ኢ-መደበኛ ቡድኖች 


ከመደበኛው የጸጥታ መዋቅር ውጭ፣ በመንግስት ደረጃ የሚታወቁ መሪዎች ያሏቸው ነገር ግን በህገ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ቡድኖች መኖራቸውን ነዋሪዎች ጠቁመዋል። 

ለኦሮሚያ ክልል መንግስትና  ለኦሮሚያ ብልፅግና ቃል አቀባይ ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ ብንጠይቅም መልስ ለመስጠት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። [ዋዜማ]