ዋዜማ- በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት የመፍጠር ራዕይ የሰነቀው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አራት የጎሉ ፈተናዎች ገጥመውኛል ብሏል።
በተቋቋመበት አዋጅ የሦስት ዓመት ዕድሜ ተሰጥቶት የነበረው የምክክር ኮሚሽን፤ የተሰጠውን የአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ አጠናቆ ለኹለተኛ ጊዜ ማራዘሚያ ተሰጥቶታል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 11፣ 2018 ዓ፣ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ለኮሚሽኑ ተጨማሪ የስምንት ወራት ጊዜ ሰጥቷል።
ለኹለተኛ ጊዜ ዕድሜው የተራዘመለት የምክክር ኮሚሽን የአራት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና የቀጣይ ዕቅዱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት የገጠሙትን ከፍተኛ ችግሮች እና አሁንም እየፈተኑኝ ነው ያላቸውን አራት ጉዳዮችን ለይቶ ለምክር ቤቱ አቅርቧል።
ኮሚሽኑ ገጠሙኝ ያላቸውን ፈተናዎች በዋናነት ከሠላምና ጸጥታ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን፣ ዋዜማ የተመለከተችው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከ ሪፖርት ያመላክታል።
የምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት ተለዋዋጭ እና ፈታኝ ተግዳሮቶች እንደገጥሙት በሪፖርቱ ገልጧል። ሥራው በበርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች የተሞላ መሆኑን የገጠው ኮሚሽኑ፣ በተለይም የግጭት ተጽእኖ ቀዳሚው ነው ብሏል።
ኹለተኛው ኮሚሽኑ ገጥሞኛል ያለው ፈተና ከነጻነትና ገለልተኝነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው ብሏል። ከኮሚሽኑ ነጻነትና ገለልተኝነት ጋር በተያያዘ የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት ከፍተኛ ፈተና መሆኑን በሪፖርቱ ተገልጧል።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች “በራሳቸው ምክንያቶች” በምክክር ሂደቱ አለመሳተፋቸው ተግዳሮት እንደሆነበትም ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡
ከጅምሩ በምክክር ሂደቱ ካልተሳተፉ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች በተጨማሪ፣ በመሐል ራሳቸው ያገለሉ ፓርቲዎች መኖራቸው ይታወቃል። ከጅምሩ በኮሚሽኑ ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ በማንሳት ራሳቸው ከተሳትፎ ካገለሉት ፓርቲዎች መካከል፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የሚገኙበት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ እናት ፓርቲ የግጭት መቆሞና የፖለቲካ እስረኞች መፈታትን እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ራሳቸው ከሂደቱ ማግለላቸው ይታወሳል።
ኮሚሽኑ ከጅምሩ ራሳቸው ያገለሉ ፓርቲዎች ወደ ሂደቱ እንዲገቡ እና በመሐል የወጡት ፖለቲካ ፓርቲዎች ተመልሰው በምክረ እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን በሪፖርቱ ጠቁሟል።
በአራተኛነት የተቀመጠው የኮሚሽኑ ፈተና የታጠቁ ቡድኖች ተሳትፎ አለመኖር ነው። በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ወገኖችን ለማሳተፍ “ምቹ ሁኔታ” አለመኖሩ፣ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነበት ኮሚሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት አስታውቋል።
ኮሚሽኑ የታጠቁ ቡድኖች በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ለማስቻል ዝግጁነት እንዳለው የገለጠ ቢሆንም፣ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ግን ከመንግሥት እና ከታጣቂ ቡድኖች “ተጨማሪ ጥረቶች” ያስፈልጋሉ ብሏል።
በአራት ዓመቱ የምክክር ሂደት ኹለት የታጠቁ ቡድኖች አጀንዳዎቻቸውን እንዳቀረቡለት ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠቅሷል። የምክክር አጀንዳ አቅርቧል ተብሎ በሥም የተጠቀሰው አንዱ ታጣቂ ቡድን “ኦነን-ሸኔ” ሲሆን፣ ኹለተኛው ደግሞ ትጥቅ ፈትቶ ወደ ሠላም ተመልሷል የተባለው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ኃይል (አፋሕድ) ነው።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ሥራውን በተሰጠው የአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ እንዲያጠናቅቅ እንቅፋት የሆነበት የትግራይ ክልል ወደ ሂደቱ አለመግባት ነው ተብሏል። በ11 ክልሎች እና ኹለት ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ክፍል አጀንዳ መሰብሰቡን የገለጠው ኮሚሽኑ፣ በትግራይ በኩል ሁኔታዎች አልተመቻቹልኝም ብሏል።
በሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር ምቹ ሁኔታ አልፈጠረም” በማለት ኮሚሽኑ በሪፖርቱ የገጠመውን ተግዳሮት ገልጧል። ኮሚሽኑ ከታህሳስ 2015 ዓ፣ም ጀምሮ ከክልሉ አመራሮች ጋር በተደጋጋሚ ውይይቶች ያደረገ ቢሆንም፣ እስከአሁን ድረስ የምክክር ሂደቱን መጀመር አለመቻሉን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ታህሳስ 2018 ዓ፣ም ባደረገው ውይይት በአምስት ዞኖች የተሳታፊ ልየታ እና አጀንዳ ማሰባሰብ ለማድረግ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ አለመሳካቱን ጠቁሟል። በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳድር በኩል አስፈላጊው መመሪያ ለዞን እና ወረዳ አመራሮች ጥሪ ባለመተላለፉ ወደ ተግባር መግባት መግባት አለመቻሉን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
ኮሚሽኑ ለ2018 ዓ፣ም በጀት ዓመት ከመንግሥት ከተመደበለት 1 ቢሊዮን 880 ሺህ ብር መደበኛ በጀት፣ በግማሽ ዓመቱ ከገንዘብ ሚኒስቴር ከተለቀቀለት 300 ሚሊዮን 770 ሺህ ብር ውስጥ 57,76 ሚሊዮን ብር ብቻ ተጠቅሟል። በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ከተፈቀደው በጀት ጥቅም ላይ የዋለው 19.2 በመቶ ብቻ የሆነው፣ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ባለመጀመሩ ነው ተብሏል።
ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ለዋናው የምክክር ጉባኤ ማስፈጸሚያ የሚውል 253 ሚሊዮን 458 ሺህ ብር ማግኘቱን ዋዜማ የተመለከተችው ሪፖርት ያመላክታል። [ዋዜማ]
