ዋዜማ- የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት አባሉ እና በቅርቡ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር የተዋሃደው የቀድሞው ተቃዋሚ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት ዮሐንስ ተሠማ አዲስ የፍትሐብሔር ክስ ቀረበባቸው፡፡
ዮሐንስ በአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ መምሪያ አዲስ የተመሰረተባቸው ክስ፣ ከዚህ ቀደም ጠፋተኛ በተባሉበት የከተማ መሬት ከሊዝ ሕግ አግባብ ውጪ ከመያዝ ጋር በተያየዘ ነው፡፡
የምክር ቤት አባሉ ከክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ ያለመከሰስ መብታቸውን ካጡ በኋላ፣ የከተማ መሬት ከሊዝ ሕግ አግባብ ውጩ በመያዝ ጥፋተኛ መባላቸው ይታወሳል፡፡ ዮሐንስ ጥፋተኛ በተባሉበት የከተማ መሬት ይዞታ መንግሥትን 996 ሺህ ብር አሳጥተዋል የሚል የፍትሐብሔር ክስ እንደቀረበባቸው ዋዜማ ተረድታለች፡፡
ዮሐንስ የቀረበባቸው አዲስ የፍትሐብሔር ክስ የካቲት 2፣ 2018 ዓ፣ም እንደደረሳቸው ቤተሰቦቻቸው ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው በሽብር ክሰ ቢሆንም፣ ከከተማ መሬት ሊዝ ይዞታ ጋር በተገናኘ በተቀሰቀሰባቸው የቆየ ክስ አምስት ዓመት ከ10 ወር እስር እንደተፈረደባቸው አይዘነጋም፡፡
ዮሐንስ ጠፋተኛ በተባሉበት የከተማ ሊዝ መሬት ጉዳይ ለክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ቅጣቱ ወደ አራት ዓመት ዝቅ እንደተደረገላቸው ቤተሰቦቻቸው የገለጡ ሲሆን፣ አሁንም ለፌደራል ከፍተኛ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቀዋል ፡፡
ዮሐንስ ጥፋተኛ ከተባሉበት የከተማ መሬት ጋር በተያያዘ አዲስ የፍትሐብሔር ክስ የቀረበባቸው፣ የክልሉ ዓቃቤ ሕገ ባቀረበባቸው የሽብር ወንጀል ነጻ ከተባሉ በኋላ ነው፡፡ የአሶሳ ከተማ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ጥር 25፣ 2018 ዓ፣ም ባዋለው ችሎት፣ ዮሐንስን ከቀረበባቸው ተደራራቢ የሽብር ክስ ነጻ ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ከሽብር ክሶች በነጻ ያሠናበታቸው፣ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ በቂ ማስረጃና ምስክሮች ማቅረብ አልቻለም በማለት ነው፡፡ ምስክር እና ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ መዝገቡ የተዘጋበት ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ወደፊት ምስክሮችን ሲያቀርብ ክሱን ማንቀሳቅስ እንዲችል ተፈቅዶለታል።
ዮሐንስ ላይ የቀረቡት ተደራራቢ ክሶች፣ “ለኦነግ-ሸኔ አባል መረጃ መስጠት፤ “የክልሉን ሕገመንግሥት ለመናድ መንቀሳቀስ”፤ “ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር” እና “የመተከል ዞንን ወደ አማራ ክልል ለማካለል ማሴር” የሚሉት ናቸው፡፡
ከታሰሩ 10 ወር ያስቆጠሩት ዮሐንስ ለእስር የተዳረጉት፣ በክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት ላይ ምክር ቤቱ “ኢ-ሕገመንግሥታዊ” በሆነ ሁኔታ ያደረገውን ማሻሻያ በመቃወም የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ የሕገመንግሥት ትርጉም እንዲሠጥበት ከሁለት ጓዶቻቸው ጋር አቤቱታ ባቀረቡ ማግስት ነበር። [ዋዜማ]
