ዋዜማ- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ሲኖዶስ መንግሥት ለቤተክርስቲያኗ ሕግ የማያስከብርላት ከሆነ፣ “ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ” የቤተክርስቲያኗ መብት እስኪረጋገጥ እንደሚታገል ዛሬ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ሲኖዶሱ፣ የቤተክርስቲያኗ መብት እስኪረጋገጥ ከፓትርያርኩ ጀምሮ ሁሉም አባቶች “የሕይወት መስዕዋትነት ጭምር በመክፈል” ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጧል።
ሲኖዶሱ መግለጫውን የሰጠው ጠቅላይ ሚንስትሩ ለካቢኔ አባላቶቻቸው የሰጡት ማብራሪያ በመንግስት መገናኛ ብዙሀን ትናንት ምሽት መተላለፉን ተከትሎ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ስለተፈጠረው ችግር ውስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናት በጉዳዩ እጃቸውን እንዳያስገቡ ለሚንስትሮች በሰጡት ማብራሪያ ላይ አስጠንቅቀዋል።
ሲኖዶሱ ለገጠመው ችግር መፍትሄው “ድርድር ነው” ያሉት ዐቢይ፣ ሲኖዶሱ “መንግሥት የላካቸውን አደራዳሪዎች ውድቅ አድርጓል” ብለዋል። ዐቢይ መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ላይ ከኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች የሚነሱ ጥያቄዎችን በቸልታ እንደማያይ በመግለጽ፣ በቋንቋ የመገልገል መብትን ሳይጋፉ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል። መንግሥት ከሁለቱ ወገኖች ለይቶ የሚደግፈው ወይም የሚቃወመው እንደሌለም ዐቢይ ተናግረዋል።
ሲኖዶሱዛሬ ምሽት በሰጠው መግለጫ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በሲኖዶሱ ላይ የተፈጸመውን “መፈንቅለ ሲኖዶስ” “ቀላልና በንግግር የሚፈታ” አንደሆነ መግለጻቸው፣ “በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ጣልቃ መግባት” ነው በማለት ተቃውሞውን ገልጧል።
ዐቢይ ሲኖዶሱ ያባረራቸውን የቀድሞ ጳጳሳት ከሲኖዶሱ ጋር በአቻ ማየታቸው፣ “ሕገወጥነትን የሚያበረታታ”፣ “ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት በሕገወጥ ቡድኖች እንዲታመሱ ይሁንታ የሚሰጥ” እና “ሊታረም የሚገባው” መሆኑን ሲኖዶሱ አስታውቋል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት በጉዳዩ እጃቸውን እንዳያስገቡ ዐቢይ የሰጡትን መመሪያም፣ የመንግሥት ኃላፊዎች “ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ የሚያደርግ” እና “ሥርዓት አልበኝነትን የሚያበረታታ” ነው- ብሎታል ሲኖዶሱ።
ሲኖዶሱ፣ ከቤተክርስቲያኗ የኦሮምኛ ቋንቋ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡት ማብራሪያ፣ “ከእውነት የራቀ” እና “እርምት ሊሰጥባት የሚገባው ነው” በማለትም ተችቷል።
ሲኖዶሱ በዚሁ መግለጫው፣ የትግራይ ክልል ኦርቶዶክስ ጳጳሳት በሲኖዶሱ ላይ አምና ባወጡት መግለጫ ላይ “አንድም ተቃውሞ አልቀረበም” በማለት ጠቅላይ ሚንስትሩ መናገራቸው፣ የአሁኑ ችግር “ሕጋዊ ሽፋን እንዲኖረው የሚያስመስል” ነው ብሏል።
ሲኖዶሱ ያገዳቸው አካላት “ወዳልተፈቀደላቸው የአገልግሎት ቦታዎች በመግባት በካህናትና ምዕመናን ላይ ሁከት እየተፈጠረ” እንደሚገኝ የጠቀሰው መግለጫው፣ መንግሥት በቤተክርስቲያኗ ጥያቄ መሠረት በሕገወጦች ላይ ርምጃ አልወሰደም በማለት ወቅሷል።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ለሕገወጡ ቡድን “የፓትሮል እጀባ” እየሰጠና የቤተክርስቲያኗ ሕጋዊ ተቋማት “ተሰብረው በሕገወጥ ቡድኖች እንዲወረሩ መደረጉን” ጭምር የጠቀሰው ሲኖዶሱ፣ “በመንግሥት ይሁንታ መፈንቅለ ሲኖዶስ እየተከናወነ” እንደሆነ እምነት ያሳድራል ብሏል። [ዋዜማ]