Abiyዋዜማ ራዲዮ- አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ኢሕአዴግ በተለይም ሕወሃት ፊቱን ወደ አጋር ድርጅቶች የሚያዞርበት ጊዜ የመጣ ይመስላል፡፡ ኢሕአዴግ አጋሮቼ የሚላቸው ድርጅቶች እንግዲህ ጋምቤላ፣ የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር እና ሐረሬ የተባሉትን ክልሎች የሚያስተዳድሩት ብሄራዊ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከሽግግሩ ቻርተር ጀምሮ አምስቱም ክልሎች በአጋር ድርጅቶች ነው የሚተዳደሩት፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት ሕወሃት ወደ ኩርፊያ ማዘንበሉን ተከትሎ፣ ከአጋር ድርጅቶች ጋር የሚኖረው ግንኙነት ትኩረት ስቧል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በመንግስት እና ገዥው ፓርቲ ከተጋረጠባቸው ፈተና ሌሌ ከአጋር ድርጅቶች እና ታዳጊ ክልሎችም አዳዲስ የፖለቲካ እና ጸጥታ-ነክ አዲስ ፈተናዎች እያቆጠቆጡባቸው ይመስላል፡፡ 

እናም ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአጋር ድርጅቶች እና ታዳጊ ክልሎቻቸው ምን ፈተናዎች እና ዕድሎች ይጠብቋቸዋል? በሕወሃት/ኢሕአዴግ እና በአጋር ድርጅቶች መካከል ለዐመታት የቆየው መስተጋብር ምን ፖለቲካዊ እና ጸጥታ-ነክ ይዘት ነበረው? አሁን በገዥው ግንባር እና በሀገሪቱ ከሚታየው ጅምር ለውጥ አንጻር ወደፊትስ ግንኙነቱ ምን መልክ ሊኖረው ይችላል? በአኩራፊው የሕወሃት ወገን ወይም ባጠቃላይ በሕወሃት እና በአጋር ድርጅቶች መካከል ለጠቅላይ ሚንስትሩ ስጋት የሚሆን ምን አዲስ መስተጋብር ሊፈጠር ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ዛሬ ላይ መዳሰስ ጠቃሚ ነው የሚሆነው፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘጋባ ከታች ይመልከቱ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

ሕወሐት የታዳጊ ክልሎች ጠበቃ?

አጋር ድርጅቶች እና ታዳጊ ክልሎች በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ የሚመራውን ሀገራዊ ለውጡን በመደገፍ እና ባለመደገፍ ትግል እንደሚካሄድባቸው ካሁን ፍንጭ መታየት ጀምሯል፡፡ በሰሞኑ በቤንሻንጉል ክልል በበርታዎች እና ደገኞች በተቀሰቀሰው ግጭት እንኳ ከሕወሃት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎች እጅ እንዳለበት መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

ይሄ ጉዳይ ከሁለት ሳምንታት በፊት ሕወሃት ወዳወጣው መግለጫ ነው የሚወስደን፡፡ ሕወሃት ለአጋር ድርጅቶች ግንባር ቀደም ተቆረቋሪ ሆኖ የመቅረቡ ነገር ማለት ነው፡፡ ኢሕአዴግ የአልጀርሱን ስምምነት ለመፈጸም ቃል የገባው እና ቁልፍ የመንግሥት ልማት ተቋማትን ወደ ግል ባለሃብት ለማዛወር የወሰነው አጋር ድርጅቶችን እና ታዳጊ ክልሎቻቸውን ሳያማክር መሆኑ ትክክል እንዳልሆነ ነው የሚከሰው- የሕወሃት መግለጫ፡፡ እንግዲህ በሀገራዊ ጉዳይ ወይም በኢሕአዴግ ውሳኔ የአጋር ድርጅቶች አቋም አስፈላጊ መሆኑ ሲነገር የሕወሃት መግለጫ የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሕወሃት ጉዳዩን ወደ መድረክ ያወጣው በኢሕአዴግ ውስጥ ይዞት የኖረው ድርጅታዊ የበላይነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ባለፉት ሦስት ወራት በፍጥነት መሸርሸሩን ተከትሎ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሕወሃት አንጋፋ መሪዎች “በድርጅታችን እና ሕዝባችን ላይ የስነ ልቦና ጦርነት ተከፍቷል”፤ “ኢሕአዴግ አብዮታዊ ፈሩን ስቷል” የሚሉ ቅሬታዎችን በይፋ እያሰሙ ባሉበት ወቅት ጭምር መሆኑም መረሳት የለበትም፡፡

እናም ሕወሃት ከሌሎች እህት ድርጅቶች ተነጥሎ ለአጋር ድርጅቶች እንዴት ተቆርቋሪ ሊሆን ቻለ? ጉዳዩን ያነሳው ለመርህ ሲል ነው? ወይንስ ለስልታዊ አላማ ሊጠቀምበት ፈልጎ? የሚሉት ጥያቄዎች ማየት ያሻል፡፡

በዋናነት ሕወሃት አጋር ድርጅቶችን ለስልታዊ ግብ ሊጠቀምባቸው ፈልጓል የሚለው ግምት ለእውነታ ይቀርባል፡፡ ይህን መነሻ አድርገን እንግዲህ ሦስት መላ ምቶችን ታሳቢ ማድረግ እንችላለን፡፡

አንደኛው መላ ምት ሕወሃት በኢሕአዴግ ውስጥ እየጎለበተ በመጣው የኦሕዴድ እና ብአዴን ሃይል ሚዛን ላለመበለጥ ሲል የተወሰኑትን ወይንም ሁሉንም አጋር ድርጅቶች የግንባሩ ሙሉ አባል ለማስደረግ አስቧል የሚለው ነው፡፡ በመጭው ነሐሴ በሚደረገው የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔው፣ አንድ ሁለት አጋር ድርጅቶች ለግንባሩ የአባልነት ጥያቄ እንዲያቀርቡ ደሞ ሕወሃት ቀድሞ ማሳመን እና ማስተባበር አይሳነውም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በተለይ የሱማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ) ለሕወሃት ቡድናዊ ዕቅድ ምቹ ሊሆን ይችላል፡፡

ሁለተኛው መላ ምት ሕወሃት ኢሕአዴግ ውስጥ እያለ ከውስጥ የማዳከም ሥራ ሊሰራ ይችላል የሚለው ነው፡፡ በተለይ ደኢሕዴን እና ደቡብ ክልል ለዚህ የተመቹ ናቸው፡፡ ከሰሞኑ ደሞ አንጋፋ የደኢሕዴን ከሃላፊነት በመልቀቃቸው አዳዲስ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ወደ ፊተኛው መድረክ እንዲመጡ በር ይከፍታል፡፡ አሁን ካለው ሀገራዊ ፖለቲካ አንጻር ተተኪዎቹ በክልልነት ጥያቄው ሊገፉበት ይችላሉ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ ሲዳማ እና ጉራጌ ካሉ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ጀርባ የሕወሃት እጅ ይኖርበት ይሆን? የሚል ጥያቄ ማንሳት ለስህተት አይዳርግም፡፡ ለምሳሌ፣ ሲዳማ ክልል ቢሆን የሲዳማ ብሄርተኞች ከደኢሕዴን ወጥተው፣ አዲሱን ክልላቸውን የሚመራ የብሄረሰብ ድርጅት ያቋቁማሉ፡፡ አዲሱ ድርጅት የኢሕአዴግ አባል ለመሆን ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ወይም የኢሕአዴግ አጋር ድርጅት ይሆናል፡፡ አለበለዚያ በተቃዋሚ ድርጅትነት ይሰለፋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለ ሁኔታ ኢሕአዴግን ማዳከም ለሚፈልግ ሃይል ምቹ መሆኑ አይቀርም፡፡

ሦስተኛው መላ ምት ሕወሃት ከኢሕአዴግ አባልነቱ ለቅቆ፣ ከአጋር ድርጅቶች ጋር አዲስ የጋራ ግንባር ሊመሰርት ይችላል የሚለው ነው፡፡ ይህ ሊደረግ የሚችለው ሕወሃት ከግንባሩ ከወጣ ነው፡፡ መውጣት ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን የመሆን ዕድሉ አናሳ ይመስላል፡፡ ሕወሃት ወጥቶስ ኢሕአዴግ እንደ ግንባር መቀጠል ይቻላል ወይ? የሚለውም ለማሰብ የሚከብድ ነው፡፡

ሕወሃት ቢወጣም እንኳ አጋር ድርጅቶች ከኢሕአዴግ ጋር የተካረረ ቅራኔ ውስጥ እስካልገቡ ድረስ መላ ምቱ ብዙም አያስኬድም፡፡ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆችን ማፈናቀል እና ግድያን አጋር ድርጅቶቹ መቆጣጠር ካልቻሉ እና አንዳንድ ተቋሞቻቸው ተዋናይነታቸውን ካላቆሙ ግን ከኢሕአዴግ እና ፌደራሉ መንግሥት ጋር ውጥረት ውስጥ መግባታቸው አይቀርም፡፡ ይሄ ደሞ ለአኩራፊው የሕወሃት ቡድን ምቹ ዕድል ይፈጥራል፡፡

የሕወሐት አኩራፊ ቡድን ወይስ የዐብይ ፌደራል መንግስት?

በርግጥ አጋር ድርጅቶች ከኢሕአዴግ አፈንግጠው ለሕወሃት እንደ ድርጅት ወይም ለአኩራፊ ቡድን ጋር ሊወዳጁ ይችላሉ ወይ? የሚለውን ለመረዳት ለዐመታት ሕወሃት ከአጋር ድርጅቶች ጋር የነበረውን መስተጋብር መመርመር ያስፈልጋል፡፡

ሕወሃት/ኢሕአዴግ በተለይ ከጋምቤላ፣ አፋር እና ጋምቤላ ጋር ያለው ታሪካዊ ግንኙነት በውዝግብ እና ጥርጣሬ የተሞላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሕወሃት ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሲዘምት ሱዳን የነበረውን አንድ የአኝዋኮች ነጻ አውጭ ግንባር አስከትሎ ነበር የዘመተው፡፡ ድርጅቱ በሽግግሩ ዘመን ጋምቤላ ክልልን የመምራት ሃላፊነት ቢሰጠውም ወዲያው የሕወሃትን መመሪያዎች ባለመቀበሉ ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ ከስልጣኑ እንዲባረር ነበር የሆነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሕወሃት ሌላ ድርጅት እንዲመሰረት አድርጎ ነው ጋምቤላን ያስረከባት፡፡ ከ1994ቱ ጎሳ ግጭት በኋላ ግን አኝዋኮች ከመንግስት ጸጥታ ሃይል ጋር በከፍተኛ ደረጃ በመጋጨታቸው ሕወሃት/ኢሕአዴግ አጋርነቱን ከአኝዋኮች ወደ ኑዌሮች አዞረ፡፡ ያኔ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ያላቸው ነባሮቹ አኝዋኮች በሕወሃት/ኢሕአዴግ ለሁለተኛ ጊዜ ስር የሰደደ ቂም የቋጠሩት፡፡

ደቡብ ሱዳን ተረጋጋችም አልተረጋጋችም ኑዌሮች ግን ዛሬም ልባቸው ወደ ጁባ እንደሚያደላ የታወቀ ነው፡፡ በቅርቡ የጋምቤላ አኝዋኮች “በደቡብ ሱዳን ኑዌር ጎሳ ተዋጥን” የሚል ቅሬታ በይፋ ማሰማታቸውም ለመጭው የአጋር ክልል ጣጣ ማሳያ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሕወሃት መልሶ የአኝዋኮችን ቅሬታ ማራገብ ግድ የሚሆንበት ቢሆንም አኝዋኮች ካሁን በፊት የደረሰባቸውን ጠባሳ ይረሱታል ወይ? የሚለው ግን አጠራጣሪ ነው የሚሆነው፡፡

ወደ አፋር ስንመጣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ከአፋሩ ድርጅት ጋር የነበረው ግንኙነት በቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር ዐሊ ሴሮ ዘመን ሞቅ ደመቅ ያለ ነበር፡፡ የኤርትራን ወረራ ተከትሎ ግን አፋሮች አጣብቂኝ ውስጥ በመግባታቸው በሕወሃት/ኢሕአዴግ ፖሊሲ ደስተኛ አልሆኑም፡፡ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ጥገኛ ከሆነች ወደህ አፋሮች ከኢሳ ሱማሌዎች ጋር በወሰን እና ሃብት ይገባኛል ጥያቄ ሲጋጩ፣ ሕወሃት-መራሹ መንግሥት ሱማሌ ከልል እና ጅቡቲ ላሉ ኢሳዎች በተደጋጋሚ ወገንተኝነት እንዳሳየ ነው የኢትዮጵያ አፋር ተቃዋሚዎች እና መብት ተሟጋቾች አጥብቀው የሚከሱት፡፡

በርግጥ አፋር ከትግራይ ክልል ጋር ተጎራባች የሆነ ብቸኛው ታዳጊ ክልል መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ እናም የአፋር ሽምቅ ተወጊ ሃይል አሁንም ስላለ ለለውጥ አደናቃፊ ሃይሎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል፡፡ መንግስት ከኤርትራ ጋር ዕርቅ ካወረደ ግን አፋሮችን ተጠቃሚ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ዱር ቤቴ ያሉ አፋሮችም መፈናፈኛ አያገኙም፡፡

የሱማሌ ክልልን ደሞ እንየው፡፡ ሕወሃት/ኢሕአዴግ በሱማሌ ክልል መጥፎ ስም ይዞ ነው የኖረው፡፡ አብዴ ኢሌ ርዕሰ መስተዳድር ከሆኑ ወዲህ ነው ሶሕዴፓ ከሕወሃት ጋር ያለው ግንኙነት መልኩ የተቀየረው፡፡ ብዙ ክስ የሚቀርብባቸው አብዲ ኢሌ አይነኬ የሆኑት ከሕወሃት ጋራ ባላቸው ወዳጅነት እንደሆነ በሰፊው ይታመናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከድርጅታቸው እና ከሕዝቡ በይፋ ተቃውሞ በርትቶባቸዋል፡፡ ሰውዬው የሕወሃት ሎሌ ናቸው የሚለው አመለካከትም ስር ሰዷል፡፡

በያዝነው ዐመት መባቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከሱማሌ ክልል ከተፈናቀሉ በኋላ አብዲ ኢሌ በኦሕዴድ ጥርስ ቢነከሰባቸውም ሶሕዴፓም ሆነ እሳቸው በመልዕካ ምድር፣ ታሪክ እና ባህል የሚቀርቡትን ኦሮሞዎችን እና ኦሕዴድን ችላ ብለው፣ ከማይጎራበተው ሕወሃት መወዳጀቱ ጨርሶ ሊጠቅማቸው እንደማይችል ያውቁታል፡፡

እናም በተለይ አቶ አብዲ የሕወሃት ተጽዕኖ መሸርሸሩን ሲያዩ አሰላለፋቸውን ሊያስተካክሉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ከሕወሃት ጋር ያላቸው ትስስር እንደሆነ የስልጣን ጥመኝነት እና ሙስና ላያልፍ ይችላል፡፡ ከዚህ ካለፈ ምናልባት ኦጋዴንን ከማስገንጠል ሴራ ጋር የተቆራኘ ነው የሚሆነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሰሞኑን መንግስት ነዳጅ ማውጣት መጀመሩን ተከትሎ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ተቃውሞ ማሰማቱ ከክልሉ ጸጥታ አንጻር ፌደራል መንግስቱ እንደገና ውስብስብ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል አመላካች ነው፡፡ በዚያ ላይ ደሞ ነዳጅ ማምረት የተጀመረው የክልሉ ልዩ ሃይል ላይ የሚነሱት አሳሳቢ ስጋቶች ገና መፍትሄ ሳያገኙ ነው፡፡

ወደ ቤንሻንጉል ስንመጣ የክልሉ ወሰን ከአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ጋር እንጅ ከትግራይ ጋር አይደለም፡፡ የበርታዎች ጉዳይ ግን ትኩረት ይፈልጋል፡፡ በርታዎች በጸረ-መንግሥት ሽምቅ ተዋጊነትም ቆይተዋል፡፡ ቀደም ሲልም ከሱዳን እስላማዊ አክራሪዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት የነበራቸው ናቸው፡፡ እናም ከክልሉ የሚነሳው ችግር ለጠቅላይ ሚንስትሩ ሀገራዊ የለውጥ ሃሳብ ፈተና ሆኖ ሊቀጥል ይችላል፡፡

ኢሕአዴግ እንግዲህ የ97ቱ ምርጫ ጭንቅ ውስጥ ሲገባ ዐይኑን ወደ አጋር ድርጅቶች በማዞር ነባሩን አጋርነት የሚያጠብቅ ተጨማሪ ስምምነት ተፈራርሞ ነበር፡፡ “ማዕከላዊው መንግስት በሃይል ሲያዋህዳችሁ ታሪካዊ በደል ፈጽሞባችኋል፤ ኢሕአዴግ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳችሁን በራሳችሁ የማስተዳደር መብት የሰጣችሁ” የሚሉ ትርክቶችንም ተጠቅሟል፡፡ “ተቃዋሚዎች አራቱን ክልሎች ቢያሸንፉ እንኳ በታዳጊ ክልሎች ምንም ማህበራዊ መሠረት ስለሌላቸው ሕገ መንግስቱን ማሻሻል አይችሉም” የሚል ትርክትም ይሰብክ ነበር፡፡ ድርጅቶቹ ግን ከስምምነቱ ምንም አዲስ አወንታዊ ፍሬ ሳያገኙ ነው ተዳፍኖ የቀረው፡፡

ታዳጊ ክልሎች እና አጋር ድርጅቶቻቸው ዛሬም ፍትሃዊ የፌደራል ድጎማ ድልድል እና ከፍትሃዊ ልማት ተጠቃሚ የመሆን ጥያቄዎች እንዳሏቸው ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ክልላዊ ነጻነታቸውን ከገዥው ግንባር እና ፌደራል መንግሥቱ የመጠበቅ ፍላጎትም እንዲሁ፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ደሞ ባብዛኛው ፌደሬሽን ምክር ቤትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በያዝነው ዐመትም ምክር ቤቱ የፌደራሉን እና ክልል መንግስታትን ግንኙነት የሚወስን አዋጅ አጽድቋል፡፡ ይሄ ጉልህ ሕገ መንገስታዊ ክንውን ነው፡፡ ዝርዝር ይዘቱ ግን እስካሁን በሚስጢር ስለተያዘ ምን ያህል የታዳጊ ክልሎችን ነጻነት እንደሚጠብቅ እና ከመጽደቁ በፊት ምን ያህል የአጋር ድርጅቶችን ይሁንታ እንዳገኘ አልታወቀም፡፡

እዚህ ላይ አሁን ጠቅላይ ሚንስትሩ በሚከተሉት ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያ ወደፊት ፌደሬሽን ምክር ቤት የድርጅታዊ እና መንግሥታዊ ፍትጊያ ሜዳ እንደሚሆን መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህም ይመስላል ሕወሃት የሥራ አስፈጻሚ አባሉ የሆኑትን ወይዘሮ ኪሪያ መሐመድን ለአፈ ጉባዔነት ያስመረጠው፡፡

ባጠቃላይ እንግዲህ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የአንድነት እና የእንደመር ትርክታቸው ይዘቱም ሆነ ግቡ ምን እንደሆነ ግልጽ ካላደረጉ የሕወሃትን አኩራፊ ቡድን ይቅርና አጋር ድርጅቶችን እና በብሄረሰብ የተደራጁ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ጭምር ለጥርጣሬና ብዥታ ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ እናም ለአጋር ድርጅቶች ፈጥነው አለኝታነታቸውን ሊያሳዩ ግድ ነው የሚሆንባቸው፡፡

ኢሕአዴግ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ቢፈልግ አጋር ድርጅቶችን ካልያዘ ትልቅ መሰናክል ነው የሚገጥመው፡፡ እናም ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አጋር ድርጅቶች በኢሕአዴግ፣ በመንግስት እና ባጠቃላይ በሥርዓቱ የሚደረጉ ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች ከእስካሁኑ በበለጠ ምን ያህል እንደሚጠቅሟቸው ማስረዳት ግድ ነው የሚሆንባቸው፡፡ ከሐረሬ ክልል በስተቀር ሁሉም ታዳጊ ክልሎች ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተጎራባች ስለሆኑ እና ለፌደራል መንግስቱ እና ሀገሪቱ ብሄራዊ ደኅንነት ቀጥተኛ ተጽእኖ ስላላቸው ከፍተኛ ትኩረት የሚሹበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ እስካሁን ዋና ትኩረታቸውን በመንግስታዊ ስራ ላይ ማድረጋቨው ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በድርጅታቸው ውስጥ ግን ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ በተለይ ምን ያህል ድጋፍ እንዳላቸው ለማሳየት እህት ድርጅቶች ተከታታይ መግለጫዎች እንዲሰጡ ማድረግ መቻል አለባቸው፡፡ ይሄ የአጋር ድርጅቶችን ድጋፍ ለማግኘት ይረዳቸዋል፡፡ በመንግስትም ሆነ በድርጅቱ ውስጥ የጥቅም እና ጸረ-ለውጥ ሰንሰለቱንም በከፊል ለማዳከም ሊረዳቸው ይችላል፡፡

ሕወሐትም ይለወጣል

ሕወሃት በለውጡ ላይ ክፍፍል ውስጥ መግባቱ ቢነገርም ላሁኑ ግን የድርጅቱ ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጺዮን ገብረ ሚካዔል እንዲሁም አቶ አርከበ እቁባይ የጠቅላይ ሚንስትሩን የለውጥ አጀንዳ የደገፉ መስለው ይታያሉ፡፡ ደብረ ጺዮን ደሞ የድርጅቱን እና የክልሉን መንግስታዊ መዋቅር የሚቆጣጠሩ ናቸው፡፡ እናም ጦር ሠራዊቱ እና ደኅንነቱ ከፖለቲካ ገለልተኛ ከሆነ ለውጥ ደጋፊው ቡድን የበላይነቱን በመያዝ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይን ጉዞ አስተማማኝ የማድረግ ዕድል እንደሚኖረው መገመት አያዳግትም፡፡ ይሄ ለጠቅላይ ሚንስትሩ እና ለኢሕአዴግ አንድ ተስፋ ነው፡፡

አጋር ድርጅቶች እና ክልሎች በውስጣቸው ካለው በጎሰኝነት እና ጥቅማጥቅም መተሳሰር፣ መልካም አስተዳደር ብልሽት፣ የሕግ የበላይነት መጥፋት፣ አስተዳደራዊ ብቃት ማነስ እና ከገዥው ፓርቲ እና ፌደራል መንግስቱ ጋር ጠበቅ ያለ ተቋማዊ ትስስር የሌላቸው መሆኑ ሲታይ ግን በተለይ ለብሄር ግጭት እና መፈናቀል ተጋላጭ ሆነው መቀጠላቸው ባጭር ጊዜ መፍትሄ የሚያገኝ አይመስልም፡፡ እናም ኢሕአዴግ ከአጋር ድርጅቶች እና ክልሎቻቸው የሚመጣበትን አደጋ ለመቀነስ ሲል በመጭው ድርጅታዊ ጉባዔው ራሱ ለሙሉ አባልነት ይጋብዛቸው ይሆን? የሚለውን በቀጣዮቹ ወራት የምናየው ይሆናል፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘጋባ ከታች ይመልከቱ] 

https://youtu.be/w59SlbBSQVE