Dilla University
Dilla University

ዋዜማ ራዲዮ-  የዲላ ዮኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ በትምሕርት ስርዓቱ ውስጥ በሚንፀባረቀው ብሄርን መሰረት ያደረገ ማጥላላትና በዜጎች ላይ የሚደረሰውን መፈናቀል በመቃወም ስራቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ።

በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመምህርነትና በሀላፊነት ያገለገሉት ዶ/ር ቃልኪዳን ለዋዜማ እንደተናገሩት ያለፈውን አንድ ዓመት ተኩል ያህል በፕሬዝዳንትነት በመሩት የዲላ ዩንቨርሲቲ ከተፈጠረው የከረረ ብሄርን ያማከለ ሽኩቻ በተጨማሪ ሰኔ ሁለት ቀን በዩኒቨርሲቲው የደረሰው የቦንብ ጥቃት ለደህንነቴ የሚያሰጋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብለዋል።

በዚህ እንቆቅልሽ በሆነ የቦንብ ጥቃት ዙሪያ መረጃዎች እንዲድበሰበሱና ተገቢ ምርመራ እንዳይካሄድ መደረጉ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብኛል ብለዋል።
“ለብሄረሰቦች እኩልነት መረጋገጥ በቅን ልቦና ድጋፍ ሳደርግ ቆይቻለሁ አሁን ግን በብሄር ስም የሚደረጉ ሙስናና የስልጣን መባለግ የሚያስከትሉትን አደጋ በመመልከት እንዲሁም በአካባቢው ሰሚ ያጣው የዜጎች መፈናቀል ትኩረት እንዲያገኝ ስል ከሀላፊነቴ ለመልቀቅ ወስኛለሁ”  ይላሉ ዶር ቃልኪዳን።

ለትምህርት ሚንስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በፃፉት ደብዳቤም ችግሩ አሁን ካለበት ደረጃ ተባብሶ የከፋ ቀውስ ከመከተሉ በፊት እርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው በጌዳኦ ዞን ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ጋር ይጎራበታል።
በቅርቡም በአካባቢው ስባት መቶ ሺህ የጌድኦ ብሄር አባላት ከሚኖሩበት የኦሮምያ ክልል ተፈናቅለዋል።
በአካባቢው ያለው የብሄር ግጭት እኔንም እንደአካባቢው ማህበረሰብ የሚመለከተኝ በመሆኑና መንግስት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ ያሳስበኛል ያሉት ዶ/ር ቃልኪዳን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ይህን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ትኩረትእንዲስጡት ተማፅነዋል።