ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞው “የኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት” በአዲስ መልክ ሊዋቀር ነው። አዲሱ አወቃቀር የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ መቀየሩን ተከትሎ ሀገራዊ አንድነትን የሚፈታተኑ ተግዳሮቾችን ለመቀልበስ ያለመ ነው ተብሏል።
በአዲሱ አደረጃጀት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሚለው ስያሜ “የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን” ወደሚለው የቀድሞ ስያሜው ይመለሳል።
ምክንያቱ ደግሞ ተቋሙን ብዙ ሰው የሚያውቀው በዚህ ስያሜ ስለሆነ የሚል ነው።
የራዲዮና የቴሌቭዥን ዘርፉ እንዲለያዩ የሚደረግ ሲሆን የጋዜጠኞችና የአስተዳደር ሰራተኞች ምደባና ቅጥር ይደረጋል። የሚሰናበቱ ሰራተኞችም ይኖራሉ።

አሁን በአንድ ሥራ አስኪያጅ የሚመሩት ሁለቱ ተቋማት የየራሳቸው አስተዳደር ይኖራቸዋል።
የራዲዮና የቴሌቭዥን ዘርፉ እንዲዋሀዱ የተደረገው 2001 ዓም ነበር።
በአዲሱ መዋቅር የቴሌቭዥኑ አንደኛ ጣቢያ ዜና፣ ሁለተኛው መዝናኛ ሶስተኛው ደግሞ የተለያዩ ቋንቋዎች እንዲሰራጩበት እንደሚደረግ እቅድ ወጥቷል።

የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ባለፉት አስራ ሁለት አመታት ከገዥው ፓርቲ በተመለመሉ ካድሬዎች በመሞላቱ ከፍ ያለ የፓርቲዎች መቆራቆሻ መድረክ ሆኖ ቆይቷል።
በቅርብ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የተከሰተውን መከፋፈል ተከትሎ በኢቢሲ ውስጥ እየታየ ያለው የፖለቲካ ሽኩቻ ስራ መስራት ከማይቸልበት ደረጃ ደርሷል ይላሉ አስተያየታቸውን ለዋዜማ የሰጡ ሰራተኞች። [ተጨማሪ መረጃና ዝርዝሩን ከግርጌ የድምፅ ዘገባውን ይመልከቱት]

https://youtu.be/qjB6noZi2Fk