ዋዜማ ራዲዮ- ሶስት አመታትን በእስር ያሳለፈው ጋዜጠኛ ተመሰገን ደሳለኝ የእስር ፍርድን አጠናቆ ተፈታ
ተመሰገን ደሳለኝ በጥቅምት 3 ቀን 2009 ዓ. ም የመፈታት እደሉን በዝዋይ ፌደራል ማረሚያ ቤት ተነፍጓ ተጨማሪ አንድ ዓመት በእስር እንዲያሳልፍ ተገዷል።ባለፈው አርብ የእስር ጊዜውን ቢያጠናቅቅም ዛሬ እሁድ ጥቅምት 5 ቀን 2010 ከዝዋይ ማረሚያ ቤት ወጥቷል።
የፌደራል ዝዋይ ማረሚያ ቤት ተመስገንን በአመክሮ ላለመፍታት የዛሬ ዓመት እንደ ምክንያት ያቀረበው በጊዜው በአገሪቱ ተስተውሎ ለነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተመስገን ፁሁፎች አስተዋፆ አላቸው፤ በአመክሮ ለመገምገም እምቢተኛ ሆኗል እንዲሁም በማረሚያ ቤቱ አድማና አመፅ ለማስቀስቀስ እስረኞችን አደራጅቶ መብታችሁን ጠይቁ ብሏል የሚሉ ምክንያቶች ናቸው።
በአዲስ አበባ የሚገኙትን የቅሊንጦ ማረሚያ ቤት እና የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ቃሊቲን ተመስገን ለጥቂት ግዜያት አሳልፎባቸዋል። በተለይ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጥበቃዎች በደረሰበት ድብደባ በእስር ያሳለፈባቸውን ጊዚያቶች ሙሉ ለሙሉ የወገብ ህመምተኛ ሆኖ ያለ በቂ ህክምና ነው የጨረሰው።
በተደጋጋሚ ከቤተሰብ ምግብ ውሃ እና መሰረታዊ የፅዳት ቁሳቁሶች ከቤተሰቦቹ እንዳይቀበል የተከለከለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ፤የቤተሰብ እና የወዳጅ ዘመድ ጥየቃም እንዳያገኝ በማረሚያ ቤቱ እግድ ተጥሎበት ነበር።
በታህሳስ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ለስድሰት ተከታታይ ቀናት ተመሰገን ደሳለኝ ዝዋይ ፌደራል ማረሚያ ቤት “የለም” በሚል የዝዋይ ማረሚያ ቤት ቤተሰቦቹን በተደጋጋሚ የመለሰ ሲሆን ፣የተመስገን ቤተሰቦች ተመሰገንን ለማግኘት እና የት እንዳለ ለማወቅ ሸዋሮቢት፣ ቃሊቲ፣ ቅሊንጦ ፣ ማዕከላዊ እና ሌሎች ፖሊስ ጣቢያዎች ቢያስሱም ተመሰገንን ማግኛት አልቻሉም ነበር። በመጨረሻም ከቀናት በኋላ የዝዋይ እስር ቤት ተመሰገን እዛው በማረሚያ ቤቱ እንደሚገኝ ገልፆ ከቤተሰቦቹ ጋር አገናኝቷል።
ተመሰገን በእስር ባሳለፈባቸው ከአንድ ሺህ በላይ ቀናት መፅሐፍ ፅፎ የጨረሰ ሲሆን “ጊዜ ለኩሉ” ብሎ የሰየመው ይኸው መፅሀፉ ከመፈታቱ ቀናት አሰቀድሞ በጥቅምት 2 ቀን 2010ዓ.ም ለገበያ በቅቷል ።
በነሃሴ 2008 ተመሰገን ደሳለኝ ቀደም ብሎ ለህትመት ያበቃው “የፈራ ይመለስ” የሚለው መፀሃፉን እና ሌሎች የፖለቲካ ይዘት ያላቸውን መፀሃፍቶችን እየሸጡ ሳለ አንዳንድ የአዲስ አበባ አዝዋሪዎች በአዲስ አበባ ደንብ አስከባሪዎች ለእስር እና ለእንግልት እንደተዳረጉ ተናግረው ነበር።
በፍትህ፣በአዲስ ታየምስ፣በልዕልና እንዲሁም በፋክት መፅሄት በማኔጂንግ ኤዲተር እና በፀሃፊነት የሰራው ተመስገን፣ከመታሰሩ ቀደም ብሎ በጋዜጣና በመፅሄቶች ላይ የፃፋቸውን ፁሁፎች ስብስብ “የመለስ አምልኮ” በሚል በመፀሃፍ መልክ ለንባብ አቅርቧል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወጣቶች በሃገሪቷ መንግስት እና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ላይ እንዲያምፁ በመገፋፋት ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር በመፈፀም፤የመንግስትን ስም በማጥፋት እና በሃሰት ውንጀላ እንዲሁም የሃሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝብን በማነሳሳት ወይም አሰተሳሰባቸውን በማናወጥ በሚል በ1996 ተሻሽሎ የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል መቅጫ ህግ አንቀፅ 257ን በመተላለፍ ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትጥፋተኛ ተብሏል።
ገዥው መንግስት ካሰራቸው በርካታ ጋዜጠኞች እና ጦማሪዎች በተለየ መንግስት ተመሰገንን በፃፋቸው ፅሁፎች ብቻ ሰለመክሰሱ ፣ ሌሎቹ ግን በተጓዳኝ ሰለሰሩት የሽብር ሴራ እንደሆነ በተደጋጋሚ የገለፀ ሲሆን ተመሰገን በፃፋቸው ፁሁፎቹ በጥቅምት 17 ቀን 2007ዓ.ም የሶስት ዓመት እስራት በፍርድ ቤት ተፈርዶበታል።
ተመስገን የሶስት አመት እስራትን እንዲፈረድበት እንደ ምክንያት አቃቤ ህግ ያቀረባቸው የፁሁፍ ስራዎቹ “የፈራ ይመለስ” ፣ “ሞት የማይፈሩ ወጣቶች” ፣ “መጅሊሱ እና ሲኖዶሱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማጥመቂያዎች” ፣ “የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መጨፈር” እና “የሁለተኛ ዜግነት ህይወት በኢትዮጵያ እስከመቼ ” የሚሉት በፍትህ ጋዜጣ የታተሙ ፁሁፎቹ ናቸው።
ተመስገን ደሳለኝ የሁለት ልጆች አባት ሲሆን ሁለቱንም ልጆቹን በአባትነት ሃላፊነት ወስዶ በማደጎ የሚያሳድጋቸው ናቸው።