ዋዜማ ራዲዮ- አቶ በረከት ስምዖን የስልጣን መልቀቂያ ከማቅረባቸው ባሻገር ስለ ኢህአዴግ “መሰንጠቅና”  ስለ “ርዕዮት አለም መስመር አለመታመን” በአደባባይ እየተናገሩ ነው።

አቶ በረከት የፓርቲያቸውን ከፍተኛ ካድሬዎች ማጥመቂያ በሆነው ስልጠና ላይ እየሰጡ የነበረው አስተያየት መደናገርና ጥያቄ አጭሯል። በውስጣዊ ቀውስ የሚታመሰው ኢህአዴግ በአቶ በረከት የስልጣን መልቀቂያ ሳቢያ ወደ አዲስ ትርምስ መግባቱ እየተነገረ ነው።
ላለፉት ወራት በዙር ሲሰጥ የነበረውን  የፖለቲካ ትምህርት ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮቹን የጠራ ርዕዮተ ዓለም ለማስታጠቅ የሚጠቀምበት ነው፡፡ ኾኖም ከመለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ ባለፉት አራት ዓመታት ስልጠናው በሙሉ አቅም መሰጠቱን አቁሞ ነበር፡፡ ዘንድሮም ቢሆን አገሪቱ በወቅታዊው ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ውስጥ ተዘፍቃ ባለችበት ወቅት ይህ ፖለቲካዊ ስልጠናው መሰጠቱ ስልጣኞቹ ከትምህርቱ ይልቅ በአመዛኙ ኔትዎርካቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት እያዋሉት ነው ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ ዕለታዊ የሻይ እረፍቶች ቡድናዊነትን የሚያጎሉ፣ የግለሰቦች አሰላለፍ የሚጠቁሙ ሆነዋል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

‹‹አዲስ አበባ ከተማን ማስተዳደር ታክቷቸዋል፣ በዘንድሮ የከተማው ምርጫም ሥልጣናቸውን ያስረክባሉ›› የሚባሉት ከንቲባ ድሪባ ኩማ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ለከፍተኛ ፖለቲካዊ ሥልጠና ወደዚሁ ጉርድሾላ የሚገኘው ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ገብተዋል፡፡ አቶ አባተ ሥጦታው አዲስ አበባን ለ45 ቀናት ያስተዳድራሉ፡፡
እያንዳንዱ ሚኒስትርና ሚኒስትር ዲኤታ በዚህ ስልጠና ውስጥ ለ45 ቀናት መጠመቅ የሚኖርበት ሲሆን በስልጠናው መጨረሻም ከመቶ የሚታረም ‹‹ምርጫ››፣ ‹‹ተንትነህ ጻፍ››፣ እና ‹‹እውነት ወይም ሐሰት በማለት መልስ›› የሚሉ የፖሊሲና የርዕዮተ ዓለም ጥያቄዎች ያሉበት ማጠቃለ ፈተና ይሰጣል፡፡ ኾኖም ፈተናው ታርሞ ለሰልጣኞች አይመለስም፡፡
ይህ ባለፈው ሳምንት የተጀመረው ስልጠና የ4ኛ ዙር ሲሆን ከንቲባ ድሪባን ዓይነት ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራሮችን፣ የክልል ባለሥልጣናትን እንዲሁም ጥቂት የመካከለኛ አመራር አባላትን ያካተተ ነው፡፡ የመካከለኛ ሰልጣኞች ይህን ስልጠና ለማግኘት ከድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ደብዳቤ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡
ያለፉትን ዙሮች በአውራነት ሲያሰለጥኑ የከረሙት አቶ በረከት ስምኦን ሲሆኑ በስልጠናው ላይ ከኢህአዴግ ባህል ባፈነገጠ መልኩ ‹‹ኢህአዴግ ለሁለት የመሰንጠቁ ነገር አይቀርለትም››፣ ‹‹ኢህአዴግ ለተነሳበት ርዕዮት ዓለሙ አልታመነም›› የሚሉ አወዛጋቢ ሐሳቦችን ማንሳታቸው በሰልጣኞች ዘንድ ብዥታን ፈጥሮ ነበር፡፡
ይህ ንግግራቸው በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ ዶክተር አርከበ እቁባይና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር የነበራቸው ቁርሾ ዘለግ ያለ ጊዜን ያስቆጠረ ሲሆን ከኢንደስትሪ ፓርክ መጀመር ጋር ተያይዞ የዘለቀ እንደሆነም ይታመናል፡፡
ሌላው አውራ አሰልጣኝ የሕወሓቱ አቶ አባይ ፀሐዮም ቢሆን በዚህ ዙር ስልጠና ላይ በአጥማቂነት ለመካፈል ፍላጎት እንዳላሳዩ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ አቶ አባይ የአቶ ኃይለማርያም አመራር የመስጠትና አዳዲስ ሐሳብ የማፍለቅ አቅም ተሸመድምዷል፣ ይህም አገሪቱን ወደ ቀውስ እየመራት ነው ብለው ከሚያምኑ ቱባ ባለሥልጣናት አንዱ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ በሕወሓቶች መንደር የአቶ ኃይለማርያም በጠቅላይ ሚኒስትርነት መቀጠል ክፍተት እየፈጠረ እንደሆነ እየታመነ መጥቷል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

አቶ በረከት ስልጣል መልቀቂያ መጠየቃቸውን መንግስት በይፋ ያረጋገጠ ሲሆን ለስልጣን መልቀቅ ስበብ ስለሆናቸው ምክንያት አልተናገረም።
በፖሊሲና በርዕዮተ ዓለም ስልጠና ጥርሳቸውን ነቅለዋል የሚባሉ የኢህአዴግ አመራሮች ራሳቸውን ከመድረክ ገሸሽ ማድረጋቸውን ተከትሎ ሌሎች አሰልጣኞች እየተፈለጉ ሲሆን ምናልባትም በአምባሳደርነት ሹመት ክፉኛ አኩርፈዋል ተብለው በሚታሙት አቶ ካሳ ተክለብርሃንና ከቁልፍ ፖለቲካ ጨዋታ ለጊዜው ገሸሽ በተደረጉት አቶ ጌታቸው ረዳ ስልጠናው ሊሰጥ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ያም ካልሆነ አቶ ሬድዋን ሁሴን ከአየርላንድ ተጠርተው አቶ በረከትንና አቶ አባይ ጸሐዬ የፈጠሩትን ክፍተት ሊሸፍኑ የሚችሉበት እድል ይኖራል፡፡
ይህ ሁሉ ካልተሳካ ግን ስልጠናው በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀደም ብለው የተቀዱ የፕላዝማ ትንተናዎች ታግዞ ሊካሄድ እንደሚችል ለፓርቲው ቅርብ ከሆኑ የመንግሥት ቤት ጋዜጠኞች ያገኘናቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡