ዋዜማ ራዲዮ- ቅዳሜ ዕለት ከፍተኛ የቃጠሎ አደጋ በደረሰበት ቂሊንጦ እስር ቤት 23 እስረኞች መሞታቸውን መንግስት አመነ፡፡ ከእስር ቤቱ ሃምሳ በመቶ ከአገልግሎት ውጭ መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ገለጹ፡፡ የተወሰኑ አስረኞች አሁንም ድረስ በአንድ ዞን ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
ለገዢው ፓርቲ ቅርብ የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤትን ጠቅሶ ማምሻውን እንዳስታወቀው በእሳት ቃጠሎው ምክንያት ህይወታቸው ካለፉ ሰዎች መካከል ሃያ አንዱ የሞቱት በመረጋገጥ፣ በጭስ በመታፈን እና በቃጠሎ ነው፡፡ ሁለት ታራሚዎች ደግሞ ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ ህይወታቸው አልፏል ሲል ፋና ዘግቧል፡፡
ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ አክቲቪስቶች ግን ቢያንስ ከ50 በላይ ሰዎች በአደጋው ሞሞታቸውን የሚያሳይ መረጃ አለን እያሉ ነው።
መንግስት ይህን ይበል እንጂ አደጋውን ተከትሎ ከውስጥ ምንጮች ለዋዜማ የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፖሊሶች ከእሳቱ ይሸሹ በነበሩ እስረኞች ላይ ይተኩሱ እንደነበር ነው፡፡ በአደጋው ወቅት በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞችም እስር ቤቱን ከብበው ከነበሩ ፖሊሶች ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ ይሰማ እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል፡፡ መንግስት ቅዳሜ ምሽቱን በመንግስት ብዙሃን መገናኛዎች በተላለፉ ዜናዎች የእሳት አደጋውን መነሻ ከእስረኞች ጋር አያይዞት የነበረ ቢሆንም በዛሬው ዕለት መግለጫው መንስኤው ገና በመጣራት ላይ እንደሆነ ገልጿል፡፡
በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር የሚገኘው እና በኦፊሴል የአዲስ አበባ የቀጠሮ እስረኞች ማቆያ በመባል የሚታወቀው የቂሊንጦ እስር ቤት በአራት ዞኖች የተከፈለ እና ወደ ሶስት ሺህ ገደማ እስረኞችን በውስጡ የያዘ ነበር፡፡ ቅዳሜ ጠዋቱን በግቢው በተነሳው እና ለማጥፋት ሰባት ሰዓታትን በወሰደው እሳት ምክንያት ዞን ሁለት እና ዞን ሶስት ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን ምንጮች ለዋዜማ አስረድተዋል፡፡
ዞን ሁለት እና ዞን ሶስት እያንዳንዳቸው 24ሜትር በ12 ሜትር ስፋት ያላቸው ስምንት ክፍሎች በውስጣቸው ያቀፉ ነበሩ፡፡ በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ከ90 እስከ 130 እስረኞች በተጨናነቀ ሁኔታ እንዲቆዩበት ይደረጋል፡፡ የማደሪያ ክፍሎቹ በብሎኬት የተሰሩ ሲሆን ጣራቸው ቆርቆሮ ነው፡፡
“በዞን ሁለት እና ሶስት የቀረው ግድግዳው ብቻ ነው” ይላል ከቃጠሎው በኋላ ቦታውን የተመለከተ የዋዜማ ምንጭ፡፡ “ጣሪያ እና ፍራሾች ሌሎችም ተቀጣጣይ ነገሮች በሙሉ ወድመዋል” ሲል ያክላል፡፡
በዞን ሁለት እና ሶስት ከመቆያ ከፍሎቹ ሌላ በቆርቆሮ የተሰሩ የኦርቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንት እና እስልምና ተከታዮች ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓት የሚያከናወኑባቸው አነስተኛ ክፍሎች አሉ፡፡ የልብስ ማጠቢያ ቦታ፣ ሱቅ፣ ጸጉር ቤት፣ ካፌ እና ላይብረሪም በውስጣቸው ይዘዋል፡፡
ምርጫ 2007 ዓ.ም ሲቃረብ በቆርቆሮ የተገነባው እና ከሌሎቹ ዞኖች ጋር ሲነጻጸር በአሰራርም በስፋትም አናሳ የሆነው ዞን አራት ላይ የደረሰው ጉዳት ምን እንደሆነ ግን ማወቅ አልቻልንም፡፡ ዞን አራት ከዞን ሁለት ጎን የሚገኝ እና በቁጥር አነስተኛ የሆኑ እስረኞች የሚታሰሩበት ነው፡፡ በእስር ቤቱ አስተዳዳር የቅጣት ትዕዛዝ የሚተላለፍባቸው እና የፖለቲካ እስረኞች በዚህ ቦታ እንደሚታሰሩ ይነገራል፡፡
“ዞን ሁለት እና ሶስት በመቃጠላቸው እስረኞቹ ወደ ዝዋይ እና ሸዋ ሮቢት ተቀላቅለው እንዲሄዱ ተደርጓል” ይላል የዋዜማ ምንጭ፡፡ “በዞን አንድ የሚገኙ እስረኞች ግን እዚያው ናቸው”
ከቂሊንጦ የተጫኑት እስረኞች ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 160 ኪሎ ሜትር ርቆ ዝዋይ ከተማ መግቢያ ላይ ወደሚገኘው ሌላኛው የፌደራል ማረሚያ ቤት የተወሰዱት ትላንት እሁድ ነበር፡፡ እስረኞቹ 30 ገደማ በሚሆኑ በተለምዶ ቢሾፍቱ ተብለው በሚጠሩት አውቶብሶች ተጭነው ዝዋይ የደረሱት ከቀኑ አምስት ሰዓት ገደማ እንደነበር በቦታው የነበረ ጠያቂ ለዋዜማ አስረድቷል፡፡
የታሳሪ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ደህንነት እና ሁኔታ ለማጣራት ትናንት እና ዛሬ ወደ ቂሊንጦ ያመሩ ቤተሰቦች እንግልት እና ወከባ ደርሶባቸዋል። ትናንት የእስረኞችን ሁኔታ ማክሰኞ በዝርዝር እናሳውቃለን ተብሎ ለቤተሰቦች የተነገረ ቢሆንም ዛሬ ደግሞ ቀኑን ወደ አርብ መግፋታቸው ተነግሯል፡፡