Amb. Samantha Power, FILE
Amb. Samantha Power, FILE

ዋዜማ ራዲዮ-በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሳማንታ ፓወር ለአጭር የስራ ጉብኝት ትናንት በአዲስ አበባ ቆይታ ቢያደርጉም በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ ጉዳይ ላይ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ሳይነጋገሩ መመለሳቸውን ምንጮች ገለጹ ፡፡

አምባሳደር ፓወር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ላይ ከአፍሪካ ህብረት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ለመምከር ነበር፡፡ የደቡብ ሱዳን ቀውስን ለመፍታት በጸጥታው ምክር ቤት አማካኝነት በተዋቀረው ልዑክ አባል የሆኑት ፓወር ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ትላንት በጽህፈት ቤታቸው አግኘተዋቸው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዑካኑን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ሊቀመንበርነቷ የደቡብ ሱዳንን ችግር ለመፍታት ያደረገችውን አስተዋጽኦ አብራርተዋል፡፡ በሶማሊያ አለ ያሉትን ሰላም እና መረጋጋት እንደዚሁም በሀገሪቱ ብሔራዊ ጦር ለመመስረት ስለሚደረገው ጥረት ገለጻ ማድረጋቸውን የመንግስት ብዙሃን መገናኛዘግበዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ላይ ከረር ያለ አስተያየታቸውን የሰጡት አምባሳደር ፓወር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አሊያም ከሌሎች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የጎንዮሽ ውይይት ይኖራቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም ዲፕሎማቷ ማንንም ሳያነጋግሩ ትላንት ምሽቱን አዲስ አበባን መልቀቃቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡

ለጸጥታው ምክር ቤት ልዑክ ሽፋን የሰጡት የመንግስት ብዙሃን መገናኛዎች የአምባሳደር ፓወርን በስብሰባው መገኘት ሳይጠቅሱ አልፈዋል፡፡ አምባሳደሯም በኦፊሲሊያዊ ትዊተር ገጻቸው በአዲስ አበባ ከአፍሪካ ህብረት ሰዎች ጋር መገናኘታቸውን በፎቶ አስደግፈው የገለጹ ቢሆንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር መገናኘታቸውን ሳይጠቅሱት ቀርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጉዳይ ክፉኛ ያሳሰባቸው የሚመስሉት አምባሳደር ፓወር ወደ አዲስ አበባ ከመጓዛቸው አንድ ቀን አስቀድሞ በደቡብ ሱዳን ጁባ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄዱ ስላሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲጠየቁ ጠንከር ያሉ ቃላት ተጠቅመው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሁኔታ “በጣሙኑ አሳሳቢ”ሲሉ የጠሩት አምባሳደር ፓወር ሀገራቸው የኢትዮጵያ መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያሻሽል ጥሪ ማቅረቧን ይናገራሉ፡፡ ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ቅርብ ናቸው የሚባሉት እና በአንድ ወቅት ጋዜጠኛ የነበሩት አምባሳደር ፓወር በሰብዓዊ መብት እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች ላይ ጠንካራ አቋሞችን በማንጸባረቅ ይታወቃሉ፡፡

“የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡ የመቃወም መብቱን በሰላማዊ መንገድ እንዲያካሂድ፣ በነጻነት መሰብሰብን እና ሀሳብን በነጻ መግለጽን እንዲፈቅድ ጥሪ አቅርበናል” በማለት የመንግስታቸውን ጥረት የገለጹት አምባሳደሯ “በተቃዋሚዎች ላይ የሚወሰዱ ያልተመጣጠኑ የኃይል እርምጃዎች ላይ ያለንን ጥልቅ ቅሬታ አንስተናል” ሲሉ አሜሪካ የመንግስትን የተቃውሞ አያያዝ እንዴት እንደምትመዝነው በዚያው ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡

መንግስታቸው በተቃውሞዎቹ ላይ ለጠፋው ህይወት ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ እንደሚያምኑ ለጋዜጠኞች የተናገሩት አምባሳደሯ ግልጽ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡ አሜሪካ በወቅቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ በዲፕሎማት ደረጃ ጠንከር ያለ አቋሟን ስትገልጽ የመጀመሪያው አይደለም፡፡

ባለፈው ሳምንት የስራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት አምባሳደር ፓትርሺያ ሀስላክ በመሰናበቻ ንግግራቸው ከአምባሳደር ፓወር ጋር የሚመሳሰል አቋማቸውን አስተጋብተዋል፡፡ “እንድታውቁት የምፈልገው ነገር መልዕክታችን ግልጽ መሆኑን ነው… ህግን ያልተከተለ እስር እና ጥቃት ሊቆም ይገባል” ሲሉ መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ አሜሪካ ደስተኛ እንዳልሆነች ጠቆም አድርገዋል፡፡

“ኢትዮጵያ እንድታድግና ስኬታማ እንድትሆን የሚፈልግ ሁሉ መረዳት ያለበት ኢትዮጵያ ጠንካራ የምትሆነው የሁሉም ድምጾች ሲሰሙባት እና መንግስት ለሁሉም ተጠያቂ ሲሆን ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኦባማ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ቶም ማልኖውስኪ ከሁለት ሳምንት በፊት ከሁለቱ ዲፕሎማቶች ጋር የሚስማማ ይዘት ያለው አስተያየት በኦል አፍሪካ ድረ-ገጽ ላይ አውጥተው ነበር፡፡ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ማልኖውስኪ በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞችን “ፈታኝ ተግዳሮቶች” ሲሉ ጠርተዋቸው ነበር፡፡

“እነዚህ ተቃውሞዎች ኢትዮጵያውያን በሕገ-መንግስቱ በሰፈረው መሰረት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ የሚሰጥና የፖለቲካ ብዘሃነትን የሚያሰፍን መንግስት እንዲኖር መፈለጋቸውን የሚያመለክቱ ናቸው” ሲሉም ሁሉን ነገር በራሴ እፈታለሁ ከሚለው መንግስት የተቃረነ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

“የደህንነት ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ኢትዮጵያውያን በሰለማዊ መንገድ እንዳይሰበሰቡ መከልከል፣ በርካቶችን መግደልና ማቁሰል እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማሰራቸውን ቀጥለዋል” ሲሉ በጽሁፋቸው ያሰፈሩት ማልኖውስኪ “በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ተገኝተዋል በሚል መሰረተ ቢስ ክስ በእስር እንደሚገኙ፣ አብዛኛዎቹም ለሕግ ያልቀረቡ፣ የሕግ አማካሪ የተከለከሉ ወይም በአግባቡ የወንጀል ክስ ያልተመሰረተባቸው እንደሆኑ እናምናለን” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለተቃውሞቹ በሚሰጠው ምላሽ እየተከተለ የሚገኘው “ራስን የመጻረር ስልት” እንደሆነም አስምረውበታል፡፡

እነዚህ ጠንካራ አስተያየቶች እና አቋሞች “አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የአቋም ለውጥ እንዳደረገች ማመላከቻዎች ናቸው?” የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ በዋሽንግተን በሚገኘው “ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ኤንተርናሽናል ስተዲስ” የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሪቻርድ ዶውኒ በኢትዮጵያ ላይ ከአሜሪካም ጭምር “እውነተኛ ጫና” እንደሚመጣ ተስፋ ያደረጋሉ፡፡ ነገር ግን ጫናው አሁኑኑ ይከሰታል በሚል “ትንፋሻቸውን ሰብስበው” እንደማይጠብቁ ይናገራሉ፡፡

“የአሜሪካ መንግስት ስለ ኢትዮጵያ በአንድ ድምጽ አይናገርም” ይላሉ ምክትል ዳይሬክተሩ ለኢንስቲትዩት ኦፍ ሲኪዩሪቲ ስተዲስ በሰጡት አስተያየት፡፡ የቶም ማልኖውስኪ ቢሮ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫና እንዲደረግ ሲጎተጉት እንደ ዩ.ኤስ. ኤይድ ያሉ ሌሎች የአሜሪካ መንግስት ተቋማት ግን “ዝምታን በመምረጥ ላይ ከፍ ያለ ፍላጎት አላቸው” ይላሉ፡፡

“ይህም በኢትዮጵያ ለልማት የሚያፈሱትን ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለመጠበቅ ያለመ ነው” ሲሉ ያብራራሉ፡፡ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ እና ሁለቱ ሱዳኖች ባሉ ሀገራት የአከባቢያውን ጸጥታ ለማስጠበቅ ለምትጫወተው ሚና ቦታ ይሰጣል ባይ ናቸው፡፡

“በውስጥ ያሉ እንደዚህ አይነት የአመለካከት ልዩነቶች የሚነግሩን አሜሪካ አሁን ያለው ሁኔታ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተባባሰ ካልመጣ በስተቀር በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ የመሆን ዕድሏ የመነመነ መሆኑን ነው” ይላሉ ሪቻርድ ዶውኒ፡፡