Fire on Kilinto prison/PHOTO Reporter
Fire on Kilinto prison/PHOTO Reporter
  • የታጠቁ ጠባቂዎች የእስር ቤቱ ሕንጻዎቹ ወደሚገኙባቸው አቅጣጫዎች ሲተኩሱ ታይተዋል
  • ቢያንስ ሀያ ሰዎች መሞታቸውንና በርካታ መቁሰላቸው ታውቋል

ዋዜማ ራዲዮ- ጎብኚዎች ታሳሪ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ በእስር ቤቱ ደጃፍ መድረስ የጀመሩት ከንጋቱ 1 :30 ሰዓት ጀምሮ ነበር። በእስር ቤቱ ደጃፍ ላይ ከውሃና ከቆሎ በስተቀር ምግብን ጨምሮ ለታሳሪዎች ይዞ መግባት እንደማይቻል የሚገልጽ ማስታወቂያ ተለጥፎ እንዳገኙ ጎብኚዎቹ ለዋዜማ ገልጸዋል። ወደ 3: 00 ሰዓት ግድም ጠያቂዎች መታወቂያቸውን እያሳዩ መመዝገብ ቢጀምሩም ባልተለመደ መልኩ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ጎብኚዎችን ለማስገባት አልፈቀዱም ነበር። አንድ በቦታው የነበሩ ጠያቂ ጠባቂዎቹ ከወትሮ የተለየ ማቅማማት ይታይባቸው እንደነበር መታዘባቸውን ተናገረዋል። ብዙም ሳይቆይ የእስር ቤቱ ዋና በር ከሚገኝበት አቅጣጫ የአውቶማቲክ መሳሪያ ተኩስ መጀመሩንና ወዲያውኑ በሌሎችም የእስር ቤቱ አካባቢዎች ተመሳሳይ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።

በአደጋው ዙሪያ ቀደም ሲል ያዘጋጀነውን ዘገባ እዚህ ያገኙታል- http://wazemaradio.com/?p=2764

በመጠበቂያ ማማ ላይ የነበሩ የታጠቁ ጠባቂዎች የእስር ቤቱ ሕንጻዎቹ ወደሚገኙባቸው አቅጣጫዎች ሲተኩሱ መመልከታቸውን ለጥየቃ ሔደው የነበሩ እማኞች ገልጽዋል። ይህን ተከትሎ ወረፋ ሲጠብቁ የነበሩ ጠያቂዎች መሬት ላይ እንዲተኙ በአካባቢው ከነበሩት ጠባቂዎቹ በአንዱ መታዘዛቸውን ጨምረው አስታውሰዋል። ከአፍታ ቆይታ በኋላ እስር ቤቱን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት ጠያቂዎች ለታሳሪ ዘመዶቻቸው ያመጡዋቸውን ነገሮች ሁሉ እየጣሉ መሸሽ ጀመረዋል። ሆኖም እነዚህ ጠያቂዎችንና በአካባቢው የተገኙ ሌሎችም ሰዎች ወዲያኑ በጸጥታ ኀይሎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው፣ የፋሉ ሮጠው እንዳመለጡ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በእስር ቤቱ የተነሳው እሳት፣ ዞን አንድ እና ሁለት የሚባሉትን አካባቢዎች አጥቅቷል ተብሏል። እሳቱ በተነሳበት ወቅት እስረኞች ከየክፍሎቻቸው ወጥተው በየግቢያቸው ውስጥ እንደነበሩ አንድ ሌላ ምንጭ ለዋዜማ አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት በርከት ያሉ ታሳሪዎች በተኩሱ ሊጎዱና ሊገደሉ እንደሚችሉ ተገምቷል።

በመንግስት በኩል ስለ አደጋው መነሻም ሆነ ስለደረሰው ጉዳት የተሰጠው መግለጫ አንድ ሰው ሞቷል፣ ሶስት የእሳት አደጋ ስራተኞች ተጎድተዋል የሚል ነው።

ፎርቹን ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው ቢያንስ ሀያ ሰዎች መሞታቸውንና በርካታ መቁሰላቸው ታውቋል።

የመንግስት የኮምንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አደጋው የተከሰተው እስረኞች በቀሰቀሱት ግርግር ነው ብሏል።
የኦሮሞ አክቲቪስቶች በበኩላቸው መንግስት በወህኒ ቤቱ ያሉ የፖለቲካ እስረኞችን ደህንነት በቀጣዩ ሀያ አራት ሰዓታት ለህዝብ ካላሳወቀ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።