German Chancellor Angela Merkel /AP
German Chancellor Angela Merkel /AP

ዋዜማ ራዲዮ- በአውሮፓ ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው የጀርመን መራሔተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በፖለቲካዊ ቀውስ እየታመሰች ወደምትገኘው ኢትዮጵያ ሊጓዙ ነው፡፡

ቻንሰለሯ ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱት የመስከረም 30 (ኦክቶበር 10) ሲሆን በአዲስ አበባ ሰባት ሰዓት ብቻ የሚፈጅ አጭር ቆይታ እንደሚኖራቸው የጀርመን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምንጮች የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ አንጌላ ሜርክል በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ይነጋገራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ምንጮች ይናገራሉ፡፡

በሰብዓዊ መብት አያያዝ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አተገባበር ላይ ጠንከር ያለ ትችት በመሰንዘር የምትታወቀው ጀርመን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የፖለቲካ ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ ካሳሰባቸው ሀገራት ትመደባለች፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች የተከፉት ጀርመኖች ይህንኑ አቋማቸውን “ባልተለሳለሰ ሁኔታ” በመሪያቸው አማካኝነት ያሳያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡

የቻንስለሯ ጉብኝት በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ መካሄድ አሊያም መሰረዝ ሀገሪቱ ውስጥ ባለው የጸጥታ ሁኔታ እንደሚወሰን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ባለስልጣናት በኩል የቻንስለሯ ጉብኝት “በጥብቅ እንደሚፈለግ” ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት “ሀገሪቱ ባስመዘገበችው እድገት እና ስኬት መሰረት በታላላቅ የውጭ መሪዎች እየተጎበኘች ነው፤ በታላላቅ መድረኮችም እየተጋበዘች ነው” የሚል የገጽታ ግንባታ መልዕክትን በተደጋጋሚ ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያለፈው ዓመት ሁለት የጀርመን ጉዞዎችም ከዚህ አንጻር በተደጋጋሚ ሲነሱ ቆይተዋል፡፡

ሜርክልም ቢሆኑ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሶስት አገራትን ያካተተ የመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ሲያደርጉ ቅድሚያ የሰጡት ለኢትዮጵያ ነበር፡፡ በሐምሌ 2003 ዓ.ም ቻንስለሯ ጎረቤት ሀገር ኬንያን፣ አንጎላን እና ናይጄሪያን ጎብኝተዋል፡፡

የመስከረም የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውም ቢሆን በዋናነት ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር ልታጠናክረው የምትፈልገው ግንኙነት ውጤት ነው፡፡ ከሜርክል የአዲስ አበባ ቆይታ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የሚወስደውም በሀገራቸው እርዳታ በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባው የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ህንጻ ምረቃ እንደሚሆን ምንጮች ይናገራሉ፡፡

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አምሳያ እንደተቀረጸ የሚነገርለት የአፍሪካ ህብረት ሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በህብረቱ ውስጥ ካሉ ውሳኔ ሰጭ አካላት አንዱ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በየጊዜው በሚደረግ ምርጫ አባል የሚሆኑ እና ከአምስት የአህጉሪቱ ቀጠናዎች የተውጣጡ አስራ አምስት ሀገራትን ያቅፋል፡፡

የህብረቱ የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት የአህጉሪቱ ትልቅ ራስ ምታት የሆኑትን እና በተደጋጋሚ አህጉሪቱን የሚያውኩትን ግጭቶች የመከላከል፣ የመቆጣጠር እና የመፍትሄ ሀሳብ የማፍለቅ ስልጣን የተሰጠው ነው፡፡ ምክር ቤቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ ህብረት ኮሚሽንነት ከተቀየረ በኋላ ከመሰረታቸው ተቋማት ውስጥ በተቺዎች ሳይቀር በውጤታማነቱ ጥሩ ቦታ ሲሰጠው ቆይቷል፡፡

ግጭቶች ከፈነዱ በኋላ ተከትለው የሚመጡ ችግሮችን በገንዘብ ለመፍታት ከመሯሯጥ ይልቅ በእንጭጩ የመቅጨት አላማ ለሰነቀው ለዚህ ምክር ቤት ህንጻ መገንቢያ ይሆን ዘንድ የጀርመን መንግስት 26.5 ሚሊዮን ዮሮ የመደበው ከአምስት አመት በፊት ነበር፡፡ በቻይናዎች ከተገነባው ግዙፉ የአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እና ህንጻ አጠገብ የሚገኘው የምክር ቤቱ ህንጻ ስራው ቢጠናቀቅም እስካሁን ስራ አልጀመረም፡፡