ከሶስት አመት በፊት ሁለት የቻይና ባለሀብቶች በ3 ቢሊየን ብር የሲሚንቶ ፋብሪካ ይገነባሉ፣ ስራ በጀመረ በአጭር ጊዜ ባለሀብቶቹ ተሰወሩ። ይህን ፋብሪካ በ26 ሚሊየን ብር ከወጋገን ባንክ ላይ የገዙት ኢትዮጵያዊ ባለሀብት እንደገና 335 ሚሊየን ብር ከልማት ባንክ ተበድረውበታል። አሁን ፋብሪካው በመዘጋት አፋፍ ላይ ነው። ሂደቱ ይህን ይመስላል።


ዋዜማ ራዲዮ- ሲ ኤች ከሊኒካል ማኑፋክቸሪንግ አ.ማ በሁለት ቻይናውያን ባለሃብቶች የተቋቋመ የሲሚንቶ ፋብሪካ ነው፡፡
የሲሚንቶ ፋብሪካው በ2008 ዓ.ም ላይ በኦሮሚያ ክልል ገብረጉራቻ አቅራቢያ አቅራቢያ ሲቋቋም ብዙ የሚጠቀሱለት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና አቅምም ነበረው፡፡ ሌላው ቀርቶ የሀገሪቱን የሀይል መቆራረጥ ችግር ቀደሞ በጥናቱም ለምርቱ እንደስጋት የለየው ችግር ነበርና በፋብሪካው ቅጥር ግቢ የተተከለው 10 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ጄኔርትር የዚህ ምስክር መሆን ይችላል፡፡


ቻይናውያኑ ባለ ሀብቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ሲመጡ ከውጭ ሀገራት ከሚመጡ ኢንቨስተሮች በተሸለ ሁኔታ የራሳቸውን ፋይናንስ ይዘው መጥተዋል። የቻይናው ኤክዚም ባንክ የተመረጡ የሀገሩን ባለሀብቶች ብድር እየሰጠ ወደ ተለያየ ሀገራት እንደሚያሰማራ ይታወቃል። እነዚህ ባለሀብቶች ገንዘቡን ከዚሁ ባንክ ያግኙ ወይም ከሌላ አበዳሪ ያገኘነው መረጃ የለም፡፡ ፋብሪካው በ3 ቢሊየን ብር መነሻ ካፒታል በዘመናዊ መንገድ መቋቋሙም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነው፡፡


በዚህ መልኩ በሙሉ አቅም ወደ ተደራጀ ማምረት የገባው የሲሚንቶ ፋብሪካ ግን ብዙም ሳይቆይ በ2008 ዓ ም ያልታሰበ ችግር ያጋጥመዋል፡፡ ከማቀጣጠያው ማሽን ጋር በተያያዘ ባጋጠመ የቴክኒክ ችግር ምክንያት የማሽኑ አካል ላይ የፍንዳታ አደጋ ያጋጥመዋል፡፡ በዚህም በአደጋው ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰራተኞች ነበሩ፡፡ በሁኔታው ድንጋጤ ውስጥ የገቡት ቻይናውያን ኢንቨስትመንታቸውን ባለበት ትተው ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ፡፡ እዚህ ላይ ግን ባለሃብቶቹ በዚህ አደጋ ድንጋጤ ውስጥ ገብተው ንብረታቸውን ትተው ሀገር ጥለው መጥፋታቸው ብዙ ጥያቄ የሚያጭርም የሚያስገርምም ነው፡፡ ቻይናውያን ባለሃብቶች ከሀገራቸው ለኢንቨስትመንት ሲመጡ ከሀገራቸው ባንኮች በሚያገኙት ብድር መነሻ ካፒታላቸውን አደራጀተው እንደሚመጡ ቢታወቅም በዛው ልክ ያገኙትን ብድር ኢንቨስትመንቱ ላይ ሙሉ በሙሉ መጠቀም ላይ ግን ጥያቄ ይነሳል፡፡
ይህ የቻይና የሲሚንቶ ፋብሪካም በወቅቱ የስራ እንቅስቃሴ ከጀመረ በኃላ ለስራ ማስኬጃ ከወጋገን ባንክ 82 ሚሊየን ብር ተጨማሪ ብድር ወስዶ ነበር፡፡ የባለሃብቶቹ ን መሰወር የተመለከተው ወጋገን ባንክ ያበደረው 82 ሚሊየን ብር የመመለሻ ግዜው እንዳለፈበት ተረዳ። አስከትሎም በተለመደው አሰራር መሰረት በብድር መያዣነት ይዞት የነበረውን ፋብሪካ ላይ ጨረታ አወጣ፡፡


ይህ ግዜ ነው እንግዲህ የአሁኑ መንግስተ አብ መሀሪ ኢንደስትሪያላይዝሽን እና ኮምርሺያል አ ማ ፋብሪካ ጨረታውን አሸነፈ ተብሎ ፋብሪካውን እንዲጠቀልል የተደረገው፡፡ ይህ አክሲዮን ማህበር በአቶ መንግስተ አብ መሀሪ እና በባለቤታው ወይዘሮ ገነት ኪዳኔ ሙሉ ለሙሉ ድርሻው የተያዘ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ወጋገን ባንክ በ82 ሚሊየን ብር ያወጣወን ጨረታ 30 በመቶ ክፍያ ማለትም ወደ 26 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ብቻ ቅድሚያ የከፈለ ሲሆን 70 በመቶ 55 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር አካባቢውን በሂደት የሚከፈል ሆኖ ፋብሪካውን ይረከባል፡፡


ምንጮቻችን እንደሚሉት ወጋገን ባንክ እራሱ በ3 ቢሊየን ብር የመቋቋሚያ ካፒታል ለተቋቋመ ሲሚኒቶ ፋብሪካ ባበደረው 82 ሚሊየን ብር ብቻ ፋብሪካውን ለመሸጥ መወሰኑም አነጋጋሪም አስገራሚም ያደርገዋል ይላሉ፡፡ በርግጥም የዋዜማ ምንጮቻችን እንደሚሉት በወቅቱ ፋብሪካው አደጋ ካስተናገደ በኋላ አጠቃላይ የፋብሪካውን ግምት ለመስራት የተላኩ የልማት ባንክ ሰራተኞች ፋብሪካው በነበረበት ቁመና 319 ሚሊየን ብር እንደሚያወጣና የደረሰበትም ጉዳት በመጠነኛ ጥገና የሚስተካከል መሆኑን አጥንተው ለልማት ባንክ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ይህ ንብረት ነው እንግዲህ ወጋገን ባንክ የመጀመሪውን ክፍያ 26 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ብቻ በመቀበል ለግለሰቡ እንዲተላለፍ ያደረገው፡፡ የ319 ሚሊየን ብርን ንብረት በ26 ሚሊየን ብር እንደማለት፡፡

ደሞ ወደ ልማት ባንክ ሄደን እንበደር…
ፋብሪካውን የተረከበው መንግስተ አብ መሀሪ ኢንደስትሪያላይዜሽን እና ኮሜርሺያል ወደ ልማት ባንክ በመምጣት ፋብሪካውን ከወጋገን ባንክ ለመግዛት ያልተከፈለውን 70 በመቶ ቀሪ እዳ ለመክፈልና ለፋብሪካው ማስፋፊያ እንዲሆን 405 ሚሊየን ብር ብድር ከልማት ባንክ ይጠይቃል፡፡ ልማት ባንክ አሰራሩን ከተከተለ የተጠየቀውን ብድር የማይፈቅድበት ሁለት መሰረታዊ የመመሪያ ክልከላዎች ነበሩ፡፡
የመጀመሪያው በዚህ ወቅት ባንኩ ለሲሚኒቶ ፋብሪካዎች ብድር ላለመስጠት ወስኖ በመመሪያ የከለከለበት ግዜ ነበር፡፡ ሁለተኛው ቀሪውን 70 በመቶ የወጋገን ባንክ መሸፈኛ ብድር የማይፈቅድበት ምክንያት ባንኩ ሌላ ብድርን መግዛትንም በመመሪያው በመከልከሉ ነው፡፡
አቶ መንግስተአብ መሀሪ በዚህ መልኩ ከባንኩ የፈለጉት ብድር እንደማይፈቀድ ሲያውቁ ወደ ብሄራዊ ባንክ በመሄድ ልማት ባንክ ብድሩን እንዲያመቻችላቸው ይጠይቃሉ፡


የሀይለማርያም ደሳለኝ ትዕዛዝ
ብሄራዊ ባንክም የልማት ባንክ አሰራር ይህንን እንደማይፈቅድ ስለሚገነዘብም ይህንን ብድር እንዲፈቀድ ጫና ማሳደር እንደሚቸገር ለባለሃብቱ በመግለጹ አቶ መንስተአብ መሀሪ ፊታቸውን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር (ሀይለማርያም ደሳለኝ) ጽህፈት ቤት ያዞራሉ፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በተሰጠ ትእዛዝም ብሄራዊ ባንክ የኢንቨስትመንቱ አስፈላጊነት ከግምት ውስጥ ገብቶ እና የልማት ባንክ የቦርድ ማኔጀመንት በተለይ ሲሚኒቶ ፋብሪካው ያለበትን የወጋገን ባንክ እዳን ለመግዛት ሃላፊነት የሚወስድ ከሆነ ቢፈቀድላቸው ችግር አይኖረውም የሚል ደብዳቤ ብሄራዊ ባንክ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በዚህ ደብዳቤ ያሳውቃል፡፡
ይህ ደብዳቤ በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በወቅቱ የልማት ባንክ የማኔጅመንት ቦርድ አባል ለነበሩትና ለኢንደስትሪ ሚኒስትሩ ለአቶ አህመድ አብተው እንደተጻፈም ዋዜማ አረጋግጣለች፡፡


55 ሚሊያን ብር አልፈቅድም ባይሆን 335 ሚሊያን ውሰዱ
ደብዳቤው የደረሰው የልማት ባንክ የቦርዱ ማኔጅመንትም ስብሰባ ይቀመጥና በደብዳቤው ላይ ይወስናል፡፡ የመጀመሪው በቦርዱ ሃላፊነት ሊወሰን ይችላል የተባለውን የወጋገንን ባንክ እዳ የመግዛት ህገ ወጥ አሰራር አልቀበልም ሃላፊነት አልወስድም ሲል ከቀሪው 55 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የወጋገን ባንክ እዳ እራሱን ነጻ ያወጣል፡፡ ይሁንና ለሲሚኒቶው ፋብሪካ ተጨማሪ ስራ ማስኬጃ በሁለት ዙር በጠቅላላው የ335.86 ሚሊየን ብር ብድር ይፈቅዳል፡፡ ይህ ማለት ባለሃብቱ ከብንኩ ለማግኘት ከጠየቁት የ405 ሚሊየን ብር ብድር ውስጥ ከ335 ሚሊየን ብር በላይ ብድርም ተፈቀደላቸው ፡፡


የባንኩ የቦርድ ማኔጅመንት አነስተኛውን የ55 ሚሊየን ብር አካባቢ እዳን ወደ ጎን ቢተውም አሁንም ሁለት መሰረታዊ የባንኩ መመሪያዎች መጣሳቸውን ከባንኩ ያገኘናቸው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው ባንኩ በወቅቱ ለሲሚኒቶ ፋብሪካ እንደማያበደር ያወጣው መመሪያን የሚጣረስ ውሳኔ ማሳለፉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ባንኩ ለሌላ ባንክ ደንበኛ ብድር አይሠጥም የሚለውን መመሪያ የሚጥስ ነው፡፡
ሲሚኒቶ ፋብሪካው ገና ያልተከፈለ የወጋገን ባንክ 55 ሚሊየን ብር እዳ እንዳለበት ታወቀ ማለት ፋብሪካው የዚሁ ባንክ ደንበኛ መሆኑ ግልጽ ነው ይላሉ ምንጮቻችን፡፡ በዚህ መልኩ ይህንን ያህል ገንዘብ ብድር ያገኘው ፋብሪካ አሁን ላይ ስራ ላይ እንደሆነ ቢነገርም በቅርቡ ግን ለሰራተኞቹ ደሞዝ ለመክፈል እስከመቸገር መድረሱ ይነገራል፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባውን ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/P39yO4PTmlk