ዋዜማ ራዲዮ- የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መንግስት ባለፉት ወራት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የህዝባዊ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር ሲያካሂደው በነበረው ጦርነት “የሃገርን ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል” በሚል በአዋጅ ቁጥር 5/2014 በመላው ኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲሆን አውጆት የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማክሰኞ የካቲት 8 ቀን በሚያደርገው ልዩ ስብሰባ ያነሳዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ  ሕወሓት ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን በሃገሪቱ ህልውና እና ሉአላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑ እና ይህንኑን ጉዳይ በመደበኛው የህግ ማስከበር ስራ መከላከል የማይቻል መሆኑን በመጥቀስ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 ማወጁ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲወጣ አስገዳጅ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ እና ስጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ በመወያየትና በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ይታወሳል፡፡

መንግስት ከአንድ አመት በላይ በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት  የአገር መከላከያ ሰራዊት ከክልል የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የህወሓት ታጣቂዎችን ከአብዛኛው የአማራና የአፋር ማስወጣቱን በመግለጽ የመጀመሪያ ዙር የህግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁን የገለጸው ታህሳስ 2014 ዓ.ም ወር ላይ ነበር፡፡

የፌደራል መንግስት ምንም እንኳ የህወሓት ታጣቂዎችን ከሁለቱ ክልሎች በድል ማስወጣቱን ቢናገርም ከሰሞኑ በአፋር ክልል ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው በቀድሞ ስሙ ዞን ሁለት እየተባለ በሚጠራው ኪልበት ረሱ ዞን አምስት ወረዳዎች ከሕወሓት ታጣቂች ጋር አዲስ ከባድ ውጊያ መፋፋሙን ክልሉ ያስታወቀ ሲሆን በተመሳሳይ በአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎችም ትንኮሳ መኖራቸው የአማራ ክልል አስታውቋል፡፡

የሚንስተሮች ምክርቤት አዋጁ እንዲነሳ ተስማምቶ ካጸዳቀው ሶስት ሳምንታት የሞላው ሲሆን በፓርላማው ሳይጸድቅ መቆየቱ በብዘዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰነባብቷል፡፡

ምክርቤቱ ጥር 8 ቀን 2014 ዓ.ም በሚያካሂደው አንደኛ አመት አንደኛ ልዩ ስብሰባ የአዋጁ መነሳት አለመነሳት ላይ በአባላቱ ጠንካራ ክርክር ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፓርላማው በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ከበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች እና የጤና  ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በውይይት ላይ የነበሩትን የመንግስት ሰራተኞች ጡረታ ለመደንገግ በቀረበውን ረቂቅ አዋጅ እና የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ጡረታ ለመደንገግ የወጣ ረቂቅ  አዋጅ አስመልክቶ የሚቀርብለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን ያጸድል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]