ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያና ኤርትራ ስላም አውርደው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ተጀምሯል። መሪዎችም ጉብኝት አድርገዋል። የንግድ ልዑካንም መነጋገር ጀምሯል። የዓስብ ወደብን ለመጠቀም ዝግጅት ተጀምሯል። በዚህ ሁሉ መሀል ግን የድንበሩ ጉዳይ እንዴት እልባት ሊበጅለት እንደታሰበ በይፋ አልተነገርም። ድንበር ማካለል ውስብስብ ጉዳዮችን ያካትታል። ተግባራዊ ማድረግም የራሱ ፈተና አለው። መሪዎቹ እንዳሉት የድንበር ጉዳይ ኢምንት ነውን? አንዳንድ ፈተና ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን እናነሳለን።  [ዝርዝር ዘገባ በድምፅ ከታች ይመልከቱ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

ድንበር ማካለል ኢምንት ጉዳይ ነውን?

Er Et leaders

አሁን በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መካከል የሚታየው ጫጉላ ሽርሽር የድንበር ማካለሉን ጉዳይ በጣም ተራ ጉዳይ አስመስሎታል፡፡ ከኤርትራ በኩልም ግዛቶቼ ይመለሱልኝ የሚለው ግፊት ጠንክሮ አይሰማም፡፡ በጠቅላላው ሁለቱ መሪዎች ስምምነት ከፈረሙ ወዲህ ባደረጓቸው ንግግሮች ትኩረታቸውን አልጣሉበትም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይም አሥመራ ላይ ባደረጉት ንግግር የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲውን እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ማቀላጠፍ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ካሰመሩበት በኋላ “ሌሎችን ትናንሽ ጉዳዮች ቀስ ብለን እንፈታቸዋለን” ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ ድንበር ማካለሉን “ትናንሽ ጉዳዮች” በተባለው ምድብ ውስጥ እንዳካተቱት ነው የሚያሳየን፡፡ “ለ20 ዐመታት ተዘግቶ የኖረው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንብ በፍቅር ፈርሷል፤ ከእንግዲህ ድንበር አያስፈልገንም” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ተወደደም ተጠላ ሁለቱ ሉዓላዊ ሀገሮች መሬት ላይ የተካለለ ዐለም ዐቀፍ ድንበር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕዝቦች ምንም ያህል ቢፋቀሩ፣ ምንም ያህል በኢኮኖሚ፣ በታሪክ እና ባሕል የተሳሰሩ ቢሆኑም ድንበር መጀመሪያ በሕግ ቢታሰር ነው የሚጠቅመው፡፡ ሁለቱ ሀገሮች ዛሬ ፍቅር በፍቅር ሆነው ስለታዩ ብቻ ድንበር የማካለሉን ነገር ወደ ጎን መግፋት አደጋ ሊጋብዝ ይችላል፡፡

ሀገሮቹ ወደፊት ወደ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ውህደት መምጣታቸው አይቀርም የሚለው እሳቤም ድንበር ማካለልን ገሸሽ ለማድረግ አሳማኝ አይመስልም፡፡ የድንበሩ መካለል ነገ ከነገ ወዲያ ሁለቱ ሕዝቦች በድንበር በኩል በሚያደርጓቸው የንግድ እና ባሕል ግንኙነቶች ላይ አንዳችም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ አይችልም፡፡ ይልቁንስ ግንኙነታቸውን በእኩልነት፣ በመከባበር እና በጋራ ጥቅም ላይ እንዲመሰርቱት ያስችላቸዋል፤ ግንኑነታቸውን ፍትሃዊ በሆነ የሕግ የበላይነት እንዲመሩት ያደርጋቸዋል፤ ለንግዳቸውም ሆነ ለሰዎች ዝውውር አስተማማኝ የደህንነት ዋስትና ያጎናጽፋቸዋል እንጅ ጉዳት የለውም፡፡ ድንበር ካልተካለለ በሚሊሻዎች አና አራሽ ገበሬዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ሁለቱን ሀገሮች እንደገና ወደ ግጭት ሊከቷቸውም ይችላሉ፡፡

ምንም እንኳ ዋነኛ መግፍዔ ባይሆንም በድንበር ውዝግብ ሳቢያ  አስከፊ ጦርነት ተካሂዷል፡፡ ሁለቱም ለከባድ ውድመት ተዳርገዋል፡፡ ውድ የሰው ሕይወትም ከፍለውበታል፡፡ የአልጀርሱ ሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላም ቢሆን ለ20 ዐመታት ግንኙነቱ ተቋርጦ የቆየው “ፍርድ ቤት የፈረደልኝን ግዛቴን ስጠኝ፤ የለም፣ ቁጭ ብለን ካልተደራደርን ቁራሽ መሬት አልሰጥህም” በሚል አተካሮ መሆኑም መረሳት የለበትም፡፡ አሁን ለጊዜው የሁለቱ መሪዎች የፖለቲካ ጫጉላ ሽርሽር ያዳፈነው ይምሰል እንጅ የድንበር እና ግዛት ጉዳይ የሚያንገበግባቸው በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከሁለቱም ወገን መኖራቸው ዐሊ የሚባል አይደለም፡፡ ኤርትራም ብትሆን አዲስ ሀገር እንደመሆኗ እና ግዛቶቹንም ያገኘችው በጦርነት ስለሆነ ዐለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ድንበር እንዲኖራት ትፈልጋለች፡፡

መደመርና ድንበር ማካለል አይጣረሱም?

በርግጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባላቸው ሀገሮች ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና ሕዝቦች ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርርቦሽ ድንበርን ዋጋ እንደሚያሳጣው ይታወቃል፡፡ ችግሩ የአፍሪካ ሀገሮች የጋራ ድንበር ከቅኝ ግዛት የተወረሰ ወለፈንድ ድንበር መሆኑ እና የይገባኛል እና ባለቤትነት ጥያቄ በብዙ ሀገሮች ለጦርነት እና ግጭት መንስዔ ሲሆን መታየቱ ነው፡፡ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ደሞ ድንበር በመንግስታቱ እንጅ በሕዝቦች ፍላጎት እና በተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታዎች አማካኝነት የሚመራበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም፡፡

እናም መሬት ላይ ያልተካለለ ድንበር መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር አዲስ የውዝግብ እና ግጭት መንስዔ እንዳይሆን የጋራ ጥቅምን መሠረት አድርጎ፣ በዐለም ዐቀፍ ሕግጋት አማካኝነት ማካለል ጠቃሚ እንደሆነ ነው የሚታመነው፡፡

ይህንንም መሠረት በማድረግ ነው አፍሪካ ሕብረት የየሀገራቱን ዐለም ዐቀፍ ድንበር የማካለልን ጉዳይ እንደ ትልቅ መርሃ ግብር ይዞ እየሰራበት ያለው፡፡ ቢሳካለትም ባይሳካለትም ሕብረቱ እኤአ እስከ 2050 ድረስም ሁሉም ሀገሮች ዐለም ዐቀፍ ድንበሮቻቸውን አካለው እንዲጨርሱ ዕቅድ ይዟል፡፡

የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን የማካለል ስልጣን የተሰጠው ኮሚሽን የሁለቱን ሀገሮች ቀና ትብብር በማጣቱ መሬት ላይ የማካለል ሥራውን ገና በቅጡ ሳይጀምረው ነበር ያቆመው፡፡ እናም ኮሚሽኑ ጥቂት ዐመታት ቆይቶ ተበትኗል፡፡ በዋናነት ያከናወነው ሥራ የካርታ ማካለሉን ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም አሁን የትኛው ገለልተኛ አካል ነው የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መሬት ላይ የሚተገብረው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ግድ ነው፡፡

አንዱ አማራጭ ሊሆን የሚችለው ሁለቱ መንግሥታት በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ የድሮው ኮሚሽን መልሶ እንዲቋቋም መጠየቅ ነው፡፡ ድሮ ሁለቱ ሀገሮች የመረጧቸው ሁለት ሁለት ዐለም ዐቀፍ ባለሙያዎችን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ግን አንደኛው ባለሙያ ከአስር ዐመታት በፊት በሞት ተለይተዋል፡፡ ሌሎቹም ቢሆኑ ለቀጣዩ ሃላፊነት ዝግጁ ስለመሆናቸው ገና ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡

ድንበሩ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ከ1000 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ስላለው ሥራው መሬት ላይ ችካል መትከል በጣም ውስብስብ ነው የሚሆነው፡፡ ዘለግ ያለ ጊዜም መውሰዱ አይቀርም፡፡ በተለይ ያለምንም ፖለቲካዊ ድርድር እንደወረደ የሚተገበር ከሆነ ደሞ በመኻሉ ንትርክ መፍጠሩ ስለማይቀር ሥራው ሊጓተት የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም፡፡ ነባሩ ኮሚሽንም ይሁን አዲስ ኮሚሽን ቢቋቋም ሁለቱ ሀገሮች ግን ለዐለም ዐቀፍ ለባለሙያዎች የሚከፍሉት ከፍተኛ የገንዘብ ወጭ ይጠብቃቸዋል፡፡ ምናልባትም ወጭውን ለመሸፈን ከዐለም ዐቀፉ ሕብረተሰብ የገንዘብ ድጋፍ ለመጠየቅ ሊገደዱ ይችሉ ይሆናል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ ኢትዮጵያ እና ሱዳን እንደሚያደርጉት የሁለትዮሽ ድንበር ኮሚሽን አቋቁመው በተራዘመ ፖለቲካዊ ድርድር ድንበሩን ማካለል ነው የሚሆነው፡፡ ዳሩ ጦርነት የተካሄደበት እና በዐለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት የተወሰነ ድንበር በመሆኑ ይሄ የመሆን ዕድሉ እጅግ አናሳ ይመስላል፡፡

አጠቃላይ ስምምነቱ ሦስተኛ ወገኖች በመሃል ሳይገቡበት መከናወኑ ለአፍሪካዊ ችግር የአፍሪካዊያን መፍትሄ ለማለት ያመች ይሆናል፡፡ ውሎ አድሮ ግን መዘዝ እንዳያመጣ ስጋት ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡ ሁለቱ መንግስታት ይሄን አካሄድ ለምን የመረጡት አጣዳፊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ስለገጠሟቸው እንደሆነ ግን መናገር ይቻላል፡፡ አሁን ባለው አያያዝ ሁለቱ መንግስታት ከስምምነተ በሚያገኙት ፖለቲካዊ እና ጸጥታ ነክ ጥቅሞች ላይ ስላተኮሩ ድንበሩን መሬት ላይ የማካለሉ ነገር እንዲዘገይ የፈለጉ ነው የሚመስለው፡፡

ወታደሮች ማስወጣት፣ ከየት ወዴት?

ድንበሩ ከመሰመሩ በፊት አንገብጋቢ የሆነው ጉዳይ ግን ወታደሮችን ከድንበር አርቆ የማስፈሩ ነገር ነው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮ-ኤርትራ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ከኤርትራ መንግስት ቀና ትብብር አጣሁ ብሎ ወደ ኤርትራ ግዛት 25 ኪሎ ሜትር ዘልቆ ከሚገባው ነጻ ወታደራዊ ቀጠና ለቆ ከወጣ በርካታ ዐመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የሁለቱ ሀገሮች ወታደሮች ያለ ገላጋይ ፊት ለፊት ተፋጠው ነው የኖሩት፡፡ እንዲያውም በዚህ ሳቢያ “የኤርትራ መንግስት ሰላም አስከባሪዎቹን ገፋፍቶ ማስወጣቱ የአልጀርሱን ስምምነት የሚቃረን ስለሆነ ስምምነቱ ከዚህ በኋላ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም” ብለው የሚከራከሩ ወገኖችም ነበሩ፡፡

በምንም መለኪያ ድንበሩ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ እና ምሽግነት ነጻ ሳይሆን ድንበሩን የማካለሉን ሥራ አስቸጋሪ ነው የሚያደርገው፡፡ በተለይ ለሦስተኛ ወገኖች ድንበር አካላይ ከሆኑ ደሞ የደኅንነት ዋስትና ሊሰማቸው አይችልም፡፡ የንግድ እና ሕዝብ ሕዝብ ግንኙነትንም ማቀላጠፍ ያስቸግራል፡፡ ግንኙነቱ ለቀቅ ብሎ ሊሟሟቅ የሚችለው ሲቪል አስተዳደራዊ መዋቅሮች እና መደበኛ ፖሊስ በሰፈሩባቸው አካባቢዎች እንጂ መደበኛ ወታደሮች ምሽግ ሰርተው በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡

እዚህ ላይ ሁለቱ መሪዎች ስምምነቱን ከፈረሙ ወዲህ ወታደሮች ከድንበሩ አርቀው ገለልተኛ ሲቪል እና ወታደራዊ ታዛቢዎች ድንበሩ ላይ እንዲሰፍሩ ይፈቅዱ ይሆን? ወይንስ በሁለትዮሽ ስምምነት ብቻ አካባቢው ከወታደራዊ ቀጠና ነጻ ሆኖ ይቆያል? እንደዚያ ከሆነ ወታደሮቹ ከድንበሩ ምን ያህል ኪሎ ሜትሮች ይርቃሉ? የሚሉ ጥያቄዎች መታሰብ ያለባቸው ናቸው፡፡

ሰሞኑን ግን የኤርትራ መንግስት ወታደሮቹን ከድንበሩ አካባቢ ወደኋላ መሳብ መጀመሩ መዘገቡ አንድ ትልቅ ርምጃ ሆኗል፡፡ የዚህን ዜና እውነተኝነት ማረጋገጥ አልቻልንም። በርግጥ ኤርትራ የፍርድ ባለ መብት ስለሆነች የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ግዛቶቿን ለቆ እንዲወጣ ለማበረታታት ካልሆነ በስተቀር ወታደሮቿን ምንም ውዝግብ ከሌለባቸው ከራሷ ግዛቶች ወደ ኋላ መሳብ አይጠበቅባትም ነበር፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጰያ በኩል ከመንግስትም ሆነ ከጦር ሠራዊቱ ግዛቶቹን ለቆ ስለውጣት በይፋ የተነገረ ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ጦሯን ወደኋላ ሳበች የሚባለው ለኤርትራ ከተወሰኑት ግዛቶች ስታስወጣ ነው ወይንስ ከራሷ ግዛት ጭምር የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ስታርቅ? የሚለው ገና ስምምነት ያልተደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡

ሁለቱም ወታደሮች በሚለቋቸው ቦታዎች ሁለት አማራጮች ሊታሰቡ ይችላሉ፤ አንደኛው፣ ገለልተኛ ወታደራዊ ታዛቢዎችን ማስፈር ነው፡፡ ከድንበሩ ርቀው የሚቆዩትስ ድንበሩ እስኪካለል ነው ወይንስ እስከመቼ ነው? የሚለውም መታየት ይኖርበታል፡፡ ይሄ አማራጭ ስለመታሰቡ ግን አሁን ማወቅ አይቻልም፡፡ ምናልባት ወደፊት በሚደረስ ዝርዝር ስምምነት ግን ታሳቢ ሊደረግ ይችል ይሆናል፡፡ የድንበሩ ርዝመት ደሞ በርካታ ታዛቢዎችን እንደሚፈልግ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ መንግስታቱ በሁለትዮሽ አካላት ድንበሩ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆን መስማማት ነው፡፡ ይሄ የሚሆን ከሆነ እንግዲህ በቅንጅት የሚሰሩ ሲቪል አስተዳደሮች እና ፖሊስ ብቻ ይቀራሉ ማለት ነው፡፡ በርግጥ ይሄን ማድረግ መቻል ቀላል ነገር አይሆንም፡፡

ስለ ድንበር ማካለል ከተነሳ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮችም አሉ፡፡ ትናንሽ ከተሞች ወደ ኤርትራ ሲጠቃለሉ የኢትዮጵያ መንግስት ንብረት የሆኑ የአስተዳደር እና እንደ ጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት ያሉ ማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት ጉዳይ እንዴት ይፈታል? በምንስ ማካካስ ይቻላል? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ምንም እንኳ ከባድ ባይሆንም፡፡

ሌላው ጉዳይ ባድመ ወይም ኢሮብ የመሳሰሉ አካባቢዎች ነዋሪዎች ወደ ኤርትራ መጠቃለሉን ባይፈልጉት እና ወደ ሌላ የትግራይ ክልል ክፍል ለመስፈር ቢጠይቁ መንግስት መብታቸውን ይጠበቅላቸዋል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ማንሳት ግድ ይላል፡፡

በተለይ ድንበሩ እንደወረደ መካለሉ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን የኢሮብ ብሄረሰብ ሕልውና እንደሚያጠፋው ነው የብሄረሰቡ መብት ተሟጋቾቹ ደጋግመው የሚናገሩት፡፡ ዋናው ስጋታቸው “የኢሮብ ሕዝብ ለሁለት ስለሚከፈል እንደ ብሄረሰብ ሕልውናው ይጠፋል” የሚል ነው፡፡ የኢሮብ ሕዝብ ደሞ ከሕወሃትም ሆነ ከኤርትራው መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት በጥርጣሬ የተሞላ ነው፡፡

እዚህ ላይ እንግዲህ በድንበር ማካለል ጊዜ ሁለቱ ሀገሮች ምን አማራጮች አሏቸው? ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ አንዱ አማራጫቸው አንዳንድ ግዛቶችን መለዋወጥ ነው፡፡ በዐለም ዐቀፉ ፍርድ ቤት ውሳኔ ግዛቴን አጣሁ የምትለው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በተወሰነ ደረጃ ኤርትራም ጭምር ናት፡፡ እናም ምናልባት ባድመን ባይጨምር ሌሎች ቦታዎችን ግን በድርድር የመለዋወጥ ዕድል አላቸው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መንግስት አንዳንድ ግዛቶችን በድርድር ለኢትዮጵያ ቢተውለት ወይም አከላለሉን ከነባራዊ ሁኔታው ጋር በሚስማማ መልኩ ቢያደርገው የኢትዮጵያ መንግስት ከሀገር ውስጥ በተለይም በትግራይ ክልል ከሚደርስበት ፖለቲካዊ ኪሳራ ይድናልና፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ስለ አካባቢው ጥርሳቸውን የነቀሉት አንጋፋ ፖለቲከኞች ከመንግስትም ፓርቲም ስልጣን ለቀዋል፡፡ በኤርትራ በኩል ግን ለእስር ከተዳረጉት ፖለቲከኞች በሰተቀር ከሞላ ጎደል እንዳሉ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ይሄ ሁሉ የሚሆነው ትግራይ ክልላዊ መንግስት እና ሕወሃት ከሂደቱ በተገለሉበት ሁኔታ ከሆነ ችግሩ ይወሳሰባል፡፡ በርግጥም እንደ ኢሮብ ያሉ ሕዝቦች የሚያነሱትን ተቃውሞ ሕወሃት ወይም ስምምነቱን ለጊዜው የሚቃወመው ቡድን ሊጠቀምበት ይችል ይሆናል፡፡ እንዲህ ዐይነት ችግሮችን ለመፍታት ነው እንገዲህ ፖለቲካዊ ድርድር የሚያስፈልገው፡፡ ችግሩ የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካዊ ድርድር መሳሪያውን ቀድሞ ከእጁ ጥሏል፡፡

ሌላው ጉዳይ ውሳኔው እንደወረደ ቢፈጸም በተለይ ኢትዮጵያ ከወታደራዊ እና ጅኦፖለቲካ አንጻር ምን ዐይነት ቁልፍ ቦታዎችን ልታጣ ትችላለች? የሚለው ጥያቄ መታሰብ ያለበት ነው፡፡ አሁን ያለው መንፈስ ግን እውነተኛ ዕርቀ ሰላም ከወረደ ኢትዮጵያ የምታጣቸው ወታደራዊ ስትራቴጂካዊ ቦታዎች እምብዛም አሳሳቢ ላይሆኑ ይችላሉ ፡፡

ባጠቃላይ ሲታይ በ1993 ዓ.ም ሕወሃትን ከሁለት የከፈሉት ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኘነት የሚመለከቱት ጉዳዮች ዛሬም አልተፈቱም፡፡ ድንበር ውዝግቡ በሕጉ መሠረት ቢፈታ እንኳ ፍትሃዊ ንግድ እና የቀረጥ ሁኔታስ ምን ይወሰናል? ድርብ ዜግነት ያያዙ ሰዎች በተለይ ኤርትራዊያን በኢትዮጵያ ሕግ እንዴት ይስተናገዱ? የሚሉት አሁንም ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እንደ ድሮው እንደ ዜጋ የሚስተናገዱ ከሆነ ግን ውሳኔው በርግጥም ለአፍሪካ ቀንድ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ይሄ አሰራር ግን በተለይ በትግራይ ሊሂቃን ዘንድ የድሮውን ልዩነት ላለመድገሙ ማረጋገጫ የለም፡፡

ድንበር ማካለሉን በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግስ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ምኞትና መብት ለመጨረሻ ጊዜ መዝጋትስ አይሆንም?  [ዝርዝር ዘገባ በድምፅ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/cjCUF-UkvqA