PM Hailemariam Desalegn
PM Hailemariam Desalegn
  • የአቶ አባዱላ መልቀቂያ ጉዳይ እልባት እንዳላገኘ እየተነገረ ነው
  • የኮምኒኬሽን ሚንስትሩ ዶር ነገሪ ሌንጮ ስንብት አይቀሬ ነው
  • የሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ በዚህ ሳምንት ይጠናቀቃል

ዋዜማ ራዲዮለመንግሥት ቅርብ የሆኑ የመረጃ ምንጭ ላለፉት ቀናት ሲካሄድ በነበረው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ዝግ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ከረር ያሉ ሂሶች የተሰነዘረበት እንደነበር እንደሚያውቁ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት አቶ ኃይለማርያም በመሪነት የመቀጠል እድላቸው የመነመነ እንደሆነም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

በኢህአዴግ ውስጥ ሐይለማርያምን ማሰናበት ከዋና ዋና የመፍትሄ እርምጃዎች አንዱ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ የጠቅላይ ሚንስትሩ እናት ፓርቲ ደኢህዴግም ጭምር እስካሁን የተቃውሞ አዝማሚያ ያሳየ የለም።

በዚህ ሳምንት ህወሓት ባቀረበው የመወያያ ሰነድ ላይ የተካረረ ውይይት እየተካሄደ ስለመሆኑ የገለጹት እኚህ የኦህዴድ አባል ኾኖም ግን የትኛው ቡድን ከማን ጋር እንደተሰለፈ ለመረዳት  አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ አብዛኛው የውይይት መንፈስ ግን በመግባባት ላይ የተመሠረተ እንደነበር በከፍተኛ የስልጣን እርከን ካሉ ጓዶቻቸው መስማታቸውን አልሸሸጉም፡፡ የሕወሓት ሰዎችና ኦህዴዶች እንደሚወራው በልዩነት መስመር ላይ አይደሉም ብለዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ ሰኞና ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝግ ለፓርላማ ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ አቶ ለማና ዶክተር ደብረጽዮን በትብብር መንፈስ ተጋግዘው ጥያቄዎችን ሲመልሱ ነበር፡፡

ከወራት በፊት የሥራ መልቀቂያ አቅርበው ምላሽ በመጠባቅ ላይ የሚገኙት የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ በድርጅቻተቸውም ሆነ በራሳቸው ላይ ገሸሽ የመደረግ ዝንባሌ እንደነበረና ሁሉን አቀፍ ጫና እየደረሰባቸው ስለመሆኑ ለሥራ አስፈጻሚው ሐሳብ አንስተው እንደነበረ፣ ኾኖም ከአንዳንድ ተሰብሳቢዎችና ከራሳቸው ድርጅት ሰዎች ሳይቀር ላነሱት ሐሳብ ድጋፍ ሳያገኙ መቅረታቸውን ሰምቻለሁ ብለዋል እኒሁ ምንጭ፡፡ ኾኖም ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የአቶ አባዱላ የመልቀቂያ ጥያቄ በሥራ አስፈጻሚው ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል ተብሎ መዘገቡ እንዳስገረማቸውና እሳቸው እስከሚያውቁት ድረስ ግን ኦህዴድ እንጂ ሥራ አስፈጻሚው የግለሰብ ጉዳይ አለማንሳቱን እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡ 

Abadula Gemeda, Speaker of the House and OPDO CC member
Abadula Gemeda, Speaker of the House and OPDO CC member

ከአንድ ሳምንት በላይ በቆየው ስብሰባ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የአመራር ብቃት ማነስ ዙርያ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል ያልዋቸውን አመራሮች በስም የጠቀሱ ሲሆን የኦህዴዱ አቶ ለማ መገርሳና የብአዴኑ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዘለግ ያለ ጊዜ ወስደው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ባልተለመደ መልኩ እንደነቀፏቸው ሰምቻለሁ ብለዋል፡፡

አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ፣ ጓድ አዲሱ ለገሰ፣ ዶክተር ካሱ ኢላላና አቶ ስዩም መስፍን  በታዛቢነት የተገኙበት በዚህ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በቀጣይ ወር ለሚደረገው 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ የሚቀርቡ ቁልፍ ዉሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስንብት እውን ከሆነም በዚሁ 11ኛው ጉባኤ ይፋ ሊደረግ ይችላል ይላሉ እኚህ ምንጭ፡፡

የተለየ አጀንዳ ካልተጨመረ በስተቀር በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ እንደሚጠናቀቅ የተናገሩት እኚህ የኦህዴድ ከፍተኛ ባለሥልጣን አመራሩ አገሪቱ ውስጥ ለተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብንም ለዚህ ምስቅልቅል ይቅርታ እንደሚጠይቅ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ቀጣይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ለኦህዴድ የመሰጠቱ ጉዳይ ውስጥ ውስጡን እየተብላላ እንደሆነ የሚናገሩት እኒህ ምንጭ የኦሮሞ ሕዝብን ተገቢ የሥልጣን ውክልና ጥያቄን ለመመለስና አልበርድ ያለውን ተቃውሞ ለማርገብ ወንበሩን ለኦህዴድ የመስጠቱ ነገር እውን የሚሆንበት እድል እንዳለ እንደሚገምቱ ተናግረዋል፡፡ ኾኖም ለዚህ ወንበር የሚታጩ ሰዎች በስም ለመለየት ጊዜው ገና ነው ባይ ናቸው፡፡ ‹‹ዞሮ ዞሮ ኃይለማርያምም ሆነ አቶ ደመቀ በሥልጣን የሚቆዩበት እድል ግን አይታየኝም›› ይላሉ፡፡ ለዚህም በአስረጂነት ያቀረቡት ‹‹የማዕከላዊ አመራር መሽመድመድ›› ለተፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮች በዋና ምክንያትነት ተነስቶ መተማመን ላይ መደረሱን ነው፡፡ ‹‹በኢህአዴግ ባህል አጀንዳዎች ተከትለን ከሄድን ከፖለቲካው ገለል የሚደረጉ አመራሮችን መለየት ያስችለናል›› የሚሉት እኚህ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራር በሰሞኑ የፓርላማ ዝግ ስብሰባም አቶ ኃይለማርያም ተኮንነዋል ይላሉ፡፡

ቀጣዩ ተግባር የሚሆነው ሥራ አስፈጻሚው ወደ ድርጅቱ ተመልሶ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ግምገማውን መቀጠልና 11ኛው ጉባኤ መዘጋጀት ይሆናል፡፡ በተለምዶ 3 ቀናት በላይ የማይወስደው የሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ 4ኪሎ ቤተመንግሥት ዘወትር ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ሲካሄድ የቆዩ ሲሆን ባለፈው እሁድ ብቻ እረፍት አድርጓል፡፡ በሁሉም ቀናት የስብሰባ ወቅት 10 አባላትን የያዘ አንድ የፌዴራል ፖሊስ ፓትሮልና 05436 መለያ ሰሌዳን የለጠፈ አንድ የመከላከያ ልዩ ኃይልን የጫነ ተሸከርካሪ ለተሰብሳቢዎቹ ጥበቃን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የባለሥልጣናት ሾፌሮች ወደ ቅጥር ግቢ መግባት ያልተፈቀደላቸው ሲሆን በላይኛው የቤተመንግሥቱ በር አጸድ ላይ ሰብሰብ ብለው እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡ ባለሥልጣናት መኪና ውስጥ ሆነው ስለ ስብሰባው የስልክ ንግግር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ተነግሯቸዋል ተብሏል፡፡ ስብሰባውን በምስል የሚያስቀሩት የደኅንነት መሥሪያ ቤት የኦዲዮ ቪዙዋል ባለሞያዎች እንደሆኑም ይነገራል፡፡

የሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ ታኅሳስ 2 የተጀመረ ቢኾንም የኦህዴድ አመራሮች በመጀመርያዎቹ ሁለት ቀናት ‹‹ክልላችንን ማረጋጋት መቅደም አለበት›› በሚል ስብሰባዎቹን ሲያስተጓጉሉ ነበር፡፡

በተያያዘ ዜና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በሥልጣን የመቆየታቸው ነገር አብቅቶለታል ሲሉ የኦህዴድ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ በሚሰጧቸው ቃለ መጠይቆች የብቃት ማነስና ግጭቶች በሚነሱበት ወቅት ጥንቃቄ የጎደለው መግለጫ መስጠታቸው ከፍተኛውን የኢህአዴግ አመራርን አላስደሰተም ተብሏል፡፡ የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀጣዮቹ አራት ሳምንታት ውስጥ ዶክተር ነገሪ በወንበራቸው ይቆያሉ ብለው እንደማያምኑ የኦህዴድ ባልደረባቸው ነግረውናል፡፡