Eagle Hills Project design

ዋዜማ ራዲዮ- በቅርቡ በአዲስ አበባ በይፋና ይፋዊ ባልሆነ መንገድ እየተጀመሩ ያሉ ፕሮጀክቶችና የመሬት ዕደላ በመስተዳድሩ ውስጥ ከፍ ያለ ግራ መጋባትና ድንግርግር ማስከተላቸውን ከከተማው አስተዳደር የተለያዩ ሀላፊዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የከተማዋን ገጽታና የህዝቡንም ኑሮ ይለውጣሉ ተብለው በቢሊየን ብሮች የተተመኑ ፕሮጀክቶች ብዙዎቹም ውስጥ ለውጥ የብዙ ውዝግብ መነሻ እየሆኑ ሲሆን ; እንደ ፕሮጀክቶቹ ብዛት ለተቋራጮች ሲተላለፉም ጨረታ የማውያውቃቸው በመሆኑ የፍትሀዊነት ችግር ከማስነሳታቸው ባሻገር ; አሁን ላይ ደግሞ ፕሮጀክቶቹስ ይሳካሉ ወይ? የሚል ጥያቄንም የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላት ሳይቀር እያነሱ መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ተረድታለች።


በለገሀር የንግድ መርከብ ህንጻና ታሪካዊው ቡፌ ዴላጋር ፈርሶለት ፤ ሌሎች በርካታ የመኖርያ ቤቶችም ይነሱለታል ተብሎ የሚጠበቀውና ብዙ የተባለለት የአቡዳቢው ኤግል ሂልስ ኩባንያ ከሰሞኑ ይፋ ያደረገውን የሽያጭ ማስታወቂያ ን ስለኩባን ያው ከዚህ ቀደም በሌሎች ሀገራት የተፈጠረው ውንብድና ወደእኛ ሀገር ስላለመምጣቱ መተማመኛ የሚስጥ አይደለም ሲሉ የመስተዳድሩ ሀላፊዎች ስጋታቸውን ይናገራሉ።

ይህ ኩባንያ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዋጽኦም ከፍ ያለ ነው። በሌሎች ሀገራት በሰራቸው ስራዎች ቅሬታ ሲሰማበት የቆየው ኤግል ሂልስ በለገሀር 36 ሄክታር መሬት እንደሚቀርብለትና ፣ የኢትዮጵያ መንግስት 20 በመቶ አካባቢ ድርሻውን በሚያዋጣበት በጥቅሉ በ50 ቢሊየን ብር ኢንቨስትመንት ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎችን እና ቅንጡ መኖርያ ቤቶችን እንደሚሰራ ይፋ መሆኑ ይታወሳል።

ታድያ ኤግል ሂልስ የተባለው የአቡዳቢ ኩባንያ ገና ግንባታ የሚያከናውንበትን ስፍራ እንኳ ተጠርጎ ሳይሰጠው “One La Gare Sales Launch” በሚል የንግድ መቀስቀሻ ከባለ አንድ እስከ አራት መኝታ ቤት ቅንጡ መኖርያ ቤቶችን ሽያጭ እንደጀመረ ማስታወቂያ ለቋል። ይህን ማስታወቂያ በሬድዮኖች አስለቅቆም የከተማው ነዋሪዎች መነጋገርያ ሆኗል። ኤግል ሂልስ በዌብሳይቱ ላይ ለ31 ሰከንድ በለቀቀው የቤት ሽያጭ ማስታወቂያ ላይም ቤቶቹ የሚሰሩት ለገሀር ባቡር ጣብያ እንደሆነ የሚጠቁሙ ምስሎችም አሉበት።

የአቡዳቢው ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታዩት የሪልስቴት ኩባንያዎች ቤት ሳይሰራ መጀመርያ ገንዘብ የሚሰበስብ ከሆነ ለምን ያለ ጨረታ በመንግስት የተለየ ስፍራ አግኝቶ በመሀል ከተማ ለማግኘት የሚከብድ 36 ሄክታር መሬት እንዲያገኝ ተወሰነለት ? የሚለው ነው። በተመሳሳይ መንገድ ወደ ስራ ለመግባትስ ለሌሎች አለማቀፍም ሆነ ሀገር አቀፍ ኩባንያዎችስ ለምን ክፍት አልሆነም ? ይላሉ ስማቸውን የሸሸጉ የመስተዳድሩ የስራ ሀላፊ።

“እንዲህ ከሆነ ዜጎች በተደጋጋሚ ውዝግብ ውስጥ ከሚገቡባቸው አይነት የቤት ገንቢዎች መለየቱስ በምን ታወቀ? አወጣለው ያለውን ገንዘብስ በርግጥ የሚያፈስ ነው ወይ የሚሉትም አልተመለሱም” ሀላፊው ይጠይቃሉ።

ኤግል ሂልስ በለገሀር ላይ ሊሰራ ላሰበው ፕሮጀክት ያቀረበው ዲዛይንም ቢሆን የከተማዋን ማስተር ፕላንና ታሪካዊ ቅርሶችን አደጋ ውስጥ የጣለ ነው በሚል ማስተካከያ እንዲያደርግ ተመክሮ ነበር። አሁንም ቢሆን በቀረቡለት ምክረ ሀሳቦች መሰረት እየሰራ መሆኑን ጥያቄ ውስጥ የሚጨምሩ የቡፌ ደላጋር መፍረስን ጨምሮ ሌሎች ፍንጮች አሉ።

በሀገሪቱ የታወቁ የምህንድስናና የስነ ህንፃ ባለሙያዎች ኤግል ሂልስም ሆኑ ሌሎች በከተማዋ ለህዝብ አገልግሎት በተከለሉ ቦታዎች ላይ የሚያደርጉት ግንባታ እጅጉን ካልታሰበበት የከፋ የከተማ ፕላን መፋለስ ያጋጥማል እያሉ ሲያስጠነቅቁ ስንብተዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዘጋጃ ቤት እድሳትም ሌላው በጨረታ ያልተሰጠ ፕሮጀክትና ከወዲሁም ችግሮች ይታዩበት የነበረ እንደሆነም ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። የመዘጋጃ ቤቱ እድሳት ሁለት ቢሊየን ብር የተመደበለትና ይሄን ዘገባ እስከሰራንበት ጊዜ ድረስ እድሳቱን የሚያከናውነው ተቋራጭ ስራውን ከጀመረ በሁዋላ ከፍቃድ ፣ ከቫትና ክፍያ ጋር በተያያዘ ችግሮች አጋጥመውት ስራው ተቋርጦ እንደነበር ማረጋገጥ ችለናል። አሁን ላይ የእድሳት ስራው ይቀጥል አይቀጥልም ግልጽ አይደለም።

በ30 ሺህ 300 ካሬ ላይ የአድዋ ፓርክን እንዲሰራ የ4.6 ቢሊየን ብር ውል የወሰደው የቻይናው ጂያንግሱም ያለ ጨረታና ያለ ግልጽነት ያገኘው ውል ነው።


ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ በ19 ሺህ ካሬ ላይ ቤተ መጻህፍት እንዲገነባ ውል የወሰደው የጣልያኑ ቫርኔሮ ያለ ጨረታ ነው ፕሮጀክቱን የወሰደው። የአዲስ አበባ የወንዞች ልማትም ፕሮጀክትም ተመሳሳይ ትችቶች ያሉበት ነው። ጎተራ በተለያየ ባለቤቶች ይሰራሉ የተባሉ የቤት ልማት ፕሮጀክቶችም የፕሮጀክቶቹ ግንባታ አሰጣጥ ከግልጽነት የራቀ ነው ተብሏል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣንም በአዲስ አበባ ከተማ አሁን ላይ ያለጨረታ እየተሰጡ ያሉ ፕሮጀክቶችም ጨረታ ለምን እንዳይወጣባቸው እንደተፈለገ ግልጽ ያልሆነና ሀገሪቱን ለከፍተኛ የሀብት ብክነት ከዳረጉት የቀድሞ የፕሮጀክት ውል አሰጣጦች ትምህርት ያልተወሰደበት አካሄድ ሲሉ ለዋዜማ ራዲዮ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]