IMG_1480

 

[መስፍን ነጋሽ – ለዋዜማ ራዲዮ እንደከተበው]

ክብርት ሆይ!
ለጤናሽ እንደምን ከርመሻል?! በዐይነ ስጋ ከተያየን ብዙ ቅዳሜ ነጎደ፣ ብዙ ጥር አለፈ! ስንት መውሊድ ተከብሮ ስንት ልደት ተቆጠረ! ስንት ጾም ተይዞ ስንት ጾፍ ተፈታ! ስንት ሰው ተይዞ ስንት ሰው ተፈታ! ስንት ሰው ተወልዶ፣ ስንት ሰው አለፈ! ዝርዝሩ ብዙ ነው።
ስለእኔ የምትሰሚውን ባላውቅም፣ ስላቺ እሰማለሁ፣ ስላቺ እሳላለሁ። ስለእኔ ያልሽውን ባላውቅም፣ ስላቺ አነባለሁ፣ ስላቺ አነባለሁ።
ለሁሉም ሰው የበቀለበት ቀዬው እንደሚሆንለት ሁሉ፣ በእኔ የሕይወት ሰሌዳ ላይ የፈሰሰው ኅብረ ቀለም የተቀዳው ካንቺ ነው። ከንባታዎቹ እነማን እንደሆኑ ሳላውቅ፣ በከንባታ ሰፈር እድር ጡሩምባ ከእንቅልፌ ስቀሰቀስ አድጌ፤ በጋሽ ሁሴን አንደበት ተመርቄ፣ ከአባቦና ከፉንጌ እጅ ጎርሼ (ፉንጌ ተሰድጄም ሙልሙል ይልኩልኛል)፤ ከግደይ ጋራ ተምሬ፣ እትዬ ኢትዮጵያ ቤት ተልኬ፤ ከሐረሩ ሰለሞን እንግሊዝኛ፣ ከወለጋው ጋሽ ገለታ ትህትና ተምሬ፤ ከነኬኔዲ ጋራ ጥምቀት ሜዳ ካርታ ተጫውቼ፣ ከነተስፋዬ ጋራ ታቦት አጅቤ፤ ሚስማር ተራ፣ ካታንጋ፣ ግራ ጥላ ለመታደም ታትሬ፤ ካላጣነው ሜዳ ገርጂ አለያም ሾላ ድረስ ለኳስ አራራ ተንከራትቼ፤ አሜሪካ ለሚሄድ ሰው የቤት ውስጥ ፓርቲ ወጥቼ፤ ከ22 መርካቶ የስራፈት ጎረምሳ ወክ አድርጌ፤ የማይገባኝን ፊልም ለማየት ሲኒማ ኢትዮጵያ ተጋፍቼ፣ አቅሜ የማይችለውን መጽሐፍ ገዝቼ፤ እያለ… እያለ… የሰፈራችን ልጅ ጣሃ ሙስሊም አባቱን ለፋሲካ በግ እንዳስገዛ ሰምቼ ስቄ፣ አመንኩ ያልኩ ሰሞን በቴዲ ካሴት ላይ መዝሙር በመቅዳቴ ኋላ በራሴ ስቄ፤ የልጅነት ፍቅረኛዬ ሌላ ስትወድ አይቼ፣ ብሔሯን አላውቅ እንደነበር ካረጀሁ ታዝቤ፤ ሕጻን የነበረችው ለይላ ትልቅ ሰው ሆና ተገርሜ፣ መጎልመሴን ገርምሜ፤ የሆለታ ልጅ ጓደኛ፣ የባህር ዳራ ልጅ ሚዜ ሆኜ፤ ከአዲሳቤው አሉላ ጋራ በአማርኛ ስዋሰው ተጣልቼ፣ የዮሐንስ አድማሱን ግጥሞች በእጄ ገልብጬ ጨርሼ፤ ሰባኪ በነበረ ጊዜ የሚያውቃቸውን ሰዎች ሲያገኝ “ያን ጊዜ ያስተማርኳችሁ ስህተት እንደነበረ ገብቶኛል” ብሎ የሚናዘዘውን የሕሊና ሰው ተዋውቄ፤ አንድ ጊዜ ብቻ ያየኋቸው ሴት አያቴ እየናፈቁኝ፣ አንድ ጊዜ ብቻ ያየኋት የአባቴ ልጅ እየተረሳችኝ፤ እያለ… እያለ…በሕይወቴ እኩሌታ ከታሪክ ጎዳናዎች በአንዱ በድንገት ካገኘኋቸው መንገደኞች ጋራ አዲስ ጨዋታ ገብቼ፣ የሙከራው በረከት ወይም መርገም ካንቺ እስኪለኝ ያለውን ሁሉ የምታውቂው ነው። ከዚያ በኋላ የተኖረው፣ አዲስ ቀለም ባይጠፋበትም መደቡ ግን ያው አንቺ ነሽ፤ አዲስባ። እያለ… እያለ…
የሆነስ ሆነና፣ ሸገር እንደምን ነሽ!

አሁን ቅዳሜ ትልቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ለማስተናገድ አስበሻል መባልን ሰማሁ። ሰዉ ሁሉ ደስ ብሎታል አሉ። ሰዉ ደስ ሲለው አንቺንም ደስ እንደሚልሽ አውቃለሁ። ስትስቂም ስታለቅሺም አውቃሻለሁ። ስትፈሪ ስትጨነቂም እናውቅሻለን። እንኳንም ደስ ያለሽ። እንኳንም ተስፋ አደረግሽ።

ሰልፉ አዲሱን መሪ፣ ዐቢይ አህመድን ያዝልቅልህ ለማለት፤ ዴሞክራሲ ይሉትን ውቃቤ ለመለማመን መሆኑን ከልጆችሽ አንደበት ሰማሁ። ከእስራትሽ እየፈታሽ፣ ከስጋትሽ እያወጣሽ ስለሆነ እንዲበረታልሽ ብትመኚ እውነት አለሽ። ልጆችሽን ሲያጎሳቁሏቸው፣ ሲገሏቸው፣ ጣር ሲያበዙባቸው አይተሻልና “እፎይ!” ለማለት ብትቸኩዪ እውነት አለሽ። የግፍ እስረኛ ማጎሪያ አድርገውሽ ሰንብተው፣ ታሳሪዎችሽ ሲፈቱ ብትጨፍሪ፣ ብታለቅሺ እውነት አለሽ፤ ጎድለውብሽ ነበርና። ስደተኞችሽን በዕንባ ብትቀበዪ እውነት አለሽ፣ ጎድለውብሽ ነበርና። አሁንም ያ ቀን እንዳይመለስ ብትመኚ፣ የፍቅርና የይቅርታ እጣን ብታጨሺ፣ እውነት አለሽ።
ማዳመጥን የሚይዳመጥ፣ ልጆችሽ ወደመካ ዞረው የሚሰግዱለት፣ ኢየሩሳሌምን የሚሳለሙለት፣ ዋቃን የሚለምኑበት፣ የየነፍሱ አማልክት ምኞታቸውን እንዲሞሉላቸው ብትመኚ እውነት አለሽ። በጎ ሕሊና ያላቸው ሁሉ፣ አርምሞሽን ይጋራሉ፣ ምኞትሽን ያጸድቃሉ።

እንዲያም ሆኖ፣ ሰልፉ፣ አንዷን ልጅችሽን አስደስቶ ሌላኛዋን የሚያስከፋ እንዳይሆን የሚሰጉ ድምጾች ሰማሁ። ስጋታቸው እንድሚያሰጋሽ አውቃለሁ። ልጆችሽ እንዲህ ያለውን ነገር እንዲጸየፉት አስታውሻቸው። ንገሪያቸው፤ ዘክሪያቸው፤ ገስጻቸው። ያንቺ ልጅነት፣ በአጥንትና በደም ቆጠራ፣ በመወለድ፣ አለዚያም በቋንቋ ጥራት፣ ካልሆነም በሃብት ብዛት የሚገኝ ወይም የሚታጣ እንዳልሆነ አስታውሻቸው። እጅግ ያዘነ፣ የተቆጣ፣ የተቀየመ ወይም የተደሰት ሰው መልካሙን ቀን መርሳት ልማዱ ነውና፣ ደጋግመሽ አስታውሻቸው። ተማጸኛቸው። ይሰሙሻል። ማንም አይከፋ በያቸው።

እንዲያም ሆኖ፣ ግፋቸው ሳያንስ፣ ጉርብትናን ጭምር የሚመርዝ የጥላቻና የመለያየት ዘር ሲበትኑብሽ የሰነበቱ፣ ሰልፉን አስታከው የጠብና የደም አዝመራቸውን ሊሰበስቡ አሰፍስፈው እንደሚጠብቁ ሰማሁ። እውነት ነው? አዲስባ፣ በጉንተላቸው አትዘናጊ፣ በለከፋቸው አትበሳጪ፣ በወጥመዳቸው አትውደቂ። መለያየትና ጥላቻን እምቢ በያቸው። ይመስላቸዋል፤ ይገምታሉ፤ አንቺን በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከከተቱ፣ መላውን ኢትዮጵያ በተመሳሳይ እሳት እያነደዱ ሊጫወቱበት እንደሚችሉ ያስባሉ። አንቺን የጥላቻና የመለያየት ከተማ በማድረግ፣ ወይም እንዲዚያ ሆናለች የሚል ወሬ በማራባት፣ የኢትዮጵያ ልጆች መሰባሰቢያ መሆንሽን ሊያስቀሩ ይመኛሉ። አንቺን የግጭት መናኸሪያ በማድረግ፣ አብሮ መኖር አይቻልም እያሉ የመለያየት ነጋሪት ከምጎሰም አይመለሱም። በቂ ህመም፣ በቂ ጭንቀት፣ በቂ ሰቆቃ፣ በቂ እሪታ አለብኝ በያቸው። ሲሆን አግባቢያቸው፤ ካልሰሙ በፍቅርና በትዕግስት አሸንፊያቸው።
በቀረውስ አዲሳባ!

የፈረንሳይ ሌጋሲዎኗን ጓደኛዬን እሷ ከእስር ተፈታ፣ እኔ እስር ሸሽቼ ስቶክሆልም ላይ ሳገኛት፤ ከ12 የአዲሳባ ጽዋ ተጣጪዎቼ ስምንቱን አሜሪካ ሳገኛቸው ጭምር ኢትዮጵያን የሚያካልለው የጨዋታችን ባቡር የሚጓዘው ሸገር በሚባል ሐዲድ ላይ እንደነበር ስነግርሽ ምን እንደምትዪ አላውቅም። ያንቺና እኔ መዋደድ ወንጀል ቢሆን ኖሮ፤ ባለቤቴ የገዛችልኝ የስደት ቤታችን አድማቂ ስዕል ፒያሳ አራዳ ፊትለ ፊትን የሚያሳይ መሆኑ የጥፋታችን ማስረጃ ሆኖ በቀረበብን ነበር። የማንክደው ክስ፤ ፍቅራችን።

አውግተን የማንጨርሰው የልብ ጨዋታ አናጣምና ስንገናኝ እንቀጥላለን። ሕልማችንም የጋራ ነውና አብረን እናባዝታለን። አሰፋ ጫቦን፣ ገብሩ መርሻን እና ኢዮብ መኮንንን በመቃብራቸው፣ ምናልባት ካልሞቱ የቄስ ትምህርት ቤት መምህሬን ባሉበት፣ ጋሼ እትዬ እያልኩ የምጠራቸውን ብዙ ሰዎች በያሉበት፣ አንዳንዶቹን አድባራት፣ ብዙዎቹን ጎዳናዎች፣ የሚስቁ የሚያስቁ ጓደኞችን፣ ከአራት ኪሎ ስድስት ኪሎ፣ ስታዲየምንና ብሔራዊን፣ የልጅነት ጥርሶቼ የተበተኑበትን 22 ማዞሪያ፣ ካፌዎቹን እና ሌሎቹንም ታስጎበኚኝ ይሆናል። እስከዚያው ሰላም ሁኚ።

መስፍን ነጋሽ።