ከኤርትራ ጋር የተጀመረው አዲስ ወዳጅነት ዘላቂ የሀገር ጥቅምን ታሳቢ ያደረገና ከመሪዎቹ መልካም ፈቃድ ይልቅ በህግና በተቋማት የታገዘ መሆን አለበት ብለው ያምናሉ። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ለአፍሪቃ ቀንድ የሚተርፍ አዲስ የለውጥ አጀንዳ ይዘው በመምጣታቸው እድናቆት አላቸው፣ እስከ ቅርብ ጊዜ የመንግስታቱ ድርጅት መልዕክተኛ፣ ከዚያ በፊት ለረጅም ዓመታት የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴዔታ የነበሩት አንጋፋው ዲፕሎማት ተቀዳ አለሙ። የዓረብ ሀገራቱን በጥንቃቄ መያዝም ልብ ሊባል የሚገባ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። በቅርቡ CRDC ለተባለ ሀገር በቀል የምርምር ማዕከል ካቀረቡት ዘለግ ያለ ፅሁፍ አንኳሩን ቻላቸው ታደሰ አሰናድቶታል።

የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደዔታ እና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደሞ በተመድ ጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ የነበሩት ዶክተር ተቀዳ አለሙ Centre for Dialogue, Research and Cooperation በተባለ ሀገር በቀል የፖሊሲ የምርምር ማዕከል ላይ ሰሞኑን ባስነበቡት ዘለግ ያለ መጣጥፍ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ደኅንነት ላይ የተደቀኑ አዳዲስ ስጋቶች ምን እንደሆኑ፣ የውጭ እና ብሄራዊ ደኅነነት ፖሊሲዋም ምን መምሰል እንዳለበት በስፋት ዳሰዋል፡፡ በጠቅላላው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እና በዐረቢያ ባሕረ ሰላጤ ወይም ቀይ ባሕር አካባቢ ልትከተለው ስለሚገባት አዲስ የውጭ ጉዳይና ብሄራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ላይ ነው ትልቅ ትኩረት ያደረጉት፡፡

እስከ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት ድረስ መንግስት ወጥ የሆነ እና በኢኮኖሚና ጸጥታ ረገድ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ያስጠበቀ የውጭ ፖሊሲ ሲከተል እንደነበር ይጠቅሳሉ- ተቀዳ፡፡ መለስ የነደፉት የ2002ቱ የውጭ ጉዳይ እና ብሄራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ዋና መሠረቱ ያደረገው በተለይ ድህነትን መቅረፍ ላይ እንደነበር በማስታወስም ይህም ትክክለኛ እና ወደፊትም መቀጠል ያለበት እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ በተግባር ግን መንግሥት ድህነትን ሳይቀርፍ መቅረቱ ሀገሪቱን ወደ መቀመቅ አፋፍ እንደገፋት፣ በውጭ ፖሊሲው አተገባበር ላይም አሉታዊ ጫና እንዳሳደረ ግን ጠቅሰዋል፡፡

ተቀዳ ብዙ ጠቃሚ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡ አሁን እየታዘቡት ያለውን እና ወደፊትም መሆን ያለበትን ለማመላከት ሞክረዋል፡፡ አንጋፋ ዲፕሎማት እንደመሆናቸው አገላለጻቸው ጥንቃቄ ቢታይበትም የዐቢይ መንግሥት በተግባር እየተከተለው ያለው የውጭና ብሄራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ግልጽነት የሌለው መሆኑ እና የሀገሪቱ ውስጣዊ ሁኔታም በጣም እንደሚያሳስባቸው አልሸሸጉም፡፡ ለዚህም ይመስላል ለመጣጥፋቸው “የወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አጣብቂኝ- ፍኖተ ካርታ ፍለጋ” የሚል ርዕስ የሰጡት፡፡

ከነባሩ የውጭ ፖሊሲ ወደፊትም መቀጠል ያለባቸው አንኳር መርሆዎች እና ብሄራዊ ጥቅሞች እንዳሉ የሚገልጹት ተቀዳ ለምን ክለሳ ሊደረግበት እንደሚገባ ምክንያታቸውን ዘርዝረዋል፡፡ በምዕራቡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘረኝነት፣ ቀኝ አክራሪነት እና ሕዝበኝነት እየተስፋፋ መምጣቱን እና ፖሊሲው በ2002 ሲነደፍ በዐለም ዐቀፉ የፖለቲካ ሥርዓት ላይ የነበረው አመኔታ እየጠፋ መምጣቱ፣ ያኔ ታሳቢ የተደረገው ግሎባላይዜሽን አሁን ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ወዘተ ለክለሳው በቂ ምክንያት መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡ በተለይ በቀይ ባሕር አካባቢ በመካከለኛ ደረጃ ያሉ ሃያላን ሀገሮች ሃላፊነት በጎደለው መልኩ የመን ላይ ጉልበታቸውን መጠቀማቸው ለአፍሪካ ቀንድ እና ለኢትዮጵያ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው በማለት በምሳሌነት ይጠቅሱታል፡፡ ሱማሊያም ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል፡፡

በርግጥ የኢትዮ-ኤርትራ ስምምነትን ተከትሎ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና በሥር ነቀል የለውጥ ሂደት ውስጥ እያለፈ መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ኤርትራ ከጅቡቲ እና ሱማሊያ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተሻሽሏል ወይም መሻሻል ጀምሯል፡፡ የኢኮኖሚ ትብብር እና ውህደት ተስፋዎች ለምልመዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይሄ ጠቅላይ ሚንስትሩን የሚያስመሰግን ጅምር የዲፕሎማሲ ስኬት ነው፡፡

በተለይ ኤርትራን በተመለከተ ሰላም ስምምነቱን አድንቀው ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰላም ለመፍጠር ሲለማመጡ የኤርትራ መንግሥት ለቁብ ያልቆጠረው ትኩረቱ ከመልዕክቱ ይልቅ ከመልዕክተኛው ማለትም ሥልጣን በያዘው አካል ላይ በመሆኑ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ዐቢይ ስልጣን ከያዙ በኋላ ግን ድንበሩ ሳይካለል ግንኙነቱ መሻሻሉ ወትሮውንስ ድንበሩ ነበር ወይ ዋና የችግሩ ምንጭ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል ሲሉ ትዝብታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አሁንም ግንኙነቱ በተቋማዊ፣ ሕጋዊ ማዕቀፍ እና በግልጽ ፍኖተ ካርታ ከመከናወን ይልቅ በመሪዎቹ የግል ግንኙነት እና መልካም ፍቃድ ላይ ብቻ መንጠልጠሉ መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

አሁን በቀጠናው ሀገሮች አወንታዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተፈጠረ ማለት ግን ሀገሮች በነባራዊ ሁኔታው ረክተው ይቀመጣሉ ማለት አይደለም፡፡ ለየራሳቸው ምን ዐይነት የላቁ ብሄራዊ ጥቅሞችን እናግኝ? እያሉ ውስጥ ለውስጥ ሥራቸውን ይሰራሉ እንጅ… ሀገሮች ደሞ ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ የሆኑ ብሄራዊ ጥቅሞች ሊኖሯቸው አይችልም፡፡ ጥቅሞቻቸውን የሚያስከብሩበት መንገድም ይለያያል፡፡ እንዲህ ያለው ነገር እንደሆነ ትናንትም ያለ እና ወደፊትም የሚኖር የሀገራት የዐለም ዐቀፍ ግንኙነት መለያ ባህሪ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እናም ከኤርትራ ጋር ዕርቅ ቢፈጠርም የኢትዮጵያን መሠረታዊ ብሄራዊ ጥቅሞች እና ዝርዝር አተገባበራቸውን መለየት ግን ጥልቅ ትንተና እና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ስራ መሆኑ አይቀርም፡፡

ባጭሩ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ የዐቢይን መንግሥት ተምኔታዊ እሳቤ እንዲይዝ ሊያደርገው አይገባም፡፡ ከኤርትራ ጋር ልቅ ግንኙነት ካሁን በፊት ያስከተለው መዘዝ መረሳት የለበትም፡፡ ቀጠናውም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከሃያላን ሀገራት እና ከባሕረ ሰላጤው ቱጃር ሀገሮች ጅኦፖለቲካዊ ሽኩቻ ጋር በጥብቅ እየተቆራኘ ስለመጣ ነባራዊው ሁኔታ ነገ ተነገ ወዲያ ምን መልክ እንደሚይዝ ፈጽሞ ርግጠኛ መሆን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡

ተቀዳ ወደፊት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ምን ዐይነት የውጭ ፖሊሲ መከተል እንዳለባት እና ለምን ጉዳዮች ትኩረት መስጠት እንዳለባት አንዳንድ ሃሳቦቻቸውን አጋርተዋል፡፡ በተለይ አጽንዖት የሰጡት ግን ፖሊሲው በፍጹም የዐረቢያ ባህረ ሰላጤን ጅኦፖለቲካዊ ሁኔታ መዘንጋት እንደሌለበት ነው፡፡ በተቀዳ ዕምነት አሁን በሱማሊያ እና ቀይ ባህር አካባቢ ያሉት ተለዋዋጭ ጅኦፖለቲካዊ ክስተቶች ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ደኅንነት ስጋት የሚደቅኑ ናቸው፡፡

እናም አዲሶቹ የውጭ ፖሊሲው ነዳፊዎች ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ማዶ ካሉት ሀገሮች ጋር በጋራ ጥቅም እና መከባበር ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዲኖራት ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ካልሰሩ ግን በጣም ትልቅ ስህተት ይፈጽማሉ ሲሉ ነው የሚያስጠነቅቁት፡፡ በቀጠናው እጃቸውን የሚያስገቡ ሀገሮችም ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ዲፕልማሲያዊ ግንኙነት ከፈለጉ በቀጠናው ያላቸው እንቅስቃሴ ወታደራዊ ወይም ጸጥታ ነክ መሆን አለመሆኑን ሊያሳውቋት ሃላፊነት እንዳለባቸው ያሰምሩበታል፡፡ ፖለቲካዊ እና ርዕዮተ ዐለማዊ ግቦችን ያዘለ የውጭ ፖሊሲ የሚያራምዱ ሀገሮችን አካሄድ ኢትዮጵያ ላለመከተል መጠንቀቅ አለባት ሲሉ በአጽንዖት ይመክራሉ፡፡ ተቀዳ ሀገሮቹን በስም ባይጠቅሱም የዐቢይ መንግሥት ከተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች እና ሳዑዲ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማመልከት እንደሆነ ግን መናገር ይቻላል፡፡

ችግሩ ኢትዮጵያ ከባሕረ ሰላጤው ቱጃር ሀገሮች ጋር የሚመጣጠን አቅም እንደሌላት የታወቀ ነው፡፡ ዲፕሎማሲ ደሞ በኢኮኖሚያዊ ጡንቻ ጭምር ይወሰናል፡፡

ተቀዳ ግን ሀገሪቱ ውስጣዊ አንድነቷን እና ጥንካሬዋን ካጎለበተች የዐረቢያ ባህረ ሰላጤው ቱጃሮች የምር ይወስዷታል ባይ ናቸው፡፡ ውስጣዊ አንድነት እና ጥንካሬን ለማጎልበት ደሞ ባሁኑ ጊዜ በፌደራል መንግሥቱ እና በአንዳንድ ክልሎች መካከል ያለውን አለመግባባት ባስቸኳይ መፍታት ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ነው በአጽንዖት የሚመክሩት፡፡ በሕዝቦች መካከል ክፍፍል ለመፍጠር የሚፈልጉ የውጭ ሃይሎችን ከሩቁ እጃቸውን ማሳጠር እንደሚያስፈልግም ያሳስባሉ፡፡ እንዳሁን ቀደሙ ሁሉ ሀገራዊ ህልውናን ማረጋገጥ በተለይም ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ወደፊትም የውጭ ጉዳይና ብሄራዊ ደኅንነት ፖሊሲው ቀዳሚ ትኩረት ሆኖ መቀጠል አለበት ባይ ናቸው፡፡ በዲፕሎማቱ ዕመነት ኢትዮጵያ አሁን በአርበኝነት ስሜት የተቃኘ የውጭ ፖሊሲ ያሰፈልጋታል፡፡

የሀገሪቱ ውስጣዊ አንድነት እና ሰላም ግን ገና ብዙ ፈተናዎች እንዳሉበት መናገር የሚቻል ይመስለናል፡፡ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ብሄርተኝነት እየተካረረ ነው የሄደው፡፡ ሀገሪቱ በግጭት ሳቢያ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ከዐለም ቀዳሚ መሆኗን ወዳጅም ጠላትም የሚያውቀው፣ ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ሆኗል፡፡ በተለይ ማነነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ደሞ ውስጣዊ ተጋላጭነትን በመጨመር ለውጭ ሃይሎች መግቢያ ቀዳዳ ሊከፍቱ ይችላሉ፡፡ በመላ ሀገሪቱ የሕግ የበላይነት እየተሸረሸረ ነው የሄደው፤ እንደ ትግራይ ያሉት ክልላዊ መንግሥታትም ለፌደራሉ መንግሥት ያለመታዘዝ አዝማሚያ እስከማሳየት ደርሰዋል፡፡ ከውስጥም በውጭም ከአፍሪካ በጥንካሬው የሚታወቀው ማዕከላዊ ሀገረ መንግሥት እየተዳከመ ይሆን? የሚል ጥርጣሬ አዘል ጥያቄም ይነሳል፡፡ እነዚህ ድክመቶች አድፍጠው የሚጠብቁ ሃይሎች አይኖሩም ማለት አይቻላም፡፡ ውስጣዊ አለመረጋጋቱ በውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖም ቀላል አይሆንም፡፡

ነባሩ የውጭ ፖሊሲ ውስጣዊ አደጋ ብሎ ያስቀመጣቸው ድህነት እና የዲሞክራሲ ዕጦት ናቸው፡፡ ዐቢይ አሁን በዲሞክራሲው አንዳንድ ጅምሮች ቢያሳዩም የድህነትና ሥራ አጥነት ቅነሳው ግን ገና ሁነኛ ፍኖተ ካርታ አልወጣለትም፡፡

አንጋፋው ዲፕሎማት ይችን መጣጥፍ ከጻፉ ከቀናት በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከአማራ እና ትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር በመሆን ከኤርትራ ጋር የሚያገናኘውን የኦምሃጀር-ሁመራ መንገድ ከፍተዋል፡፡ ከሕወሃት አመራሮች ጋር ቂም ያላቸው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም በስነ ሥርዓቱ ተገኘተዋል፡፡ በተለይ የቃላት ጦርነት ሲለዋወጡ የከረሙት የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ፊት ለፊት መገናኘታቸው ምናልባት አደጋ እያንዣበበት ላለው የሀገሪቱ ውስጣዊ አንድነት እና ሰላም ተስፋ ሰጭ ጅምር ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ማሳደሩ አልቀረም፡፡

እየተፈጠረ ባለው የዐለም ሃያላን በተለይም የቻይና እና አሜሪካ ፉክክር ውስጥ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ከሁሉም ጋር ግንኙነቷን መቀጠል እንዳለባት አጽንዖት ሰጥተውታል- ዲፕሎማቱ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ እና በዐረቢያ ቀጠና ያለው አሰላለፍ ለሃያላኑ ሀገሮች ፉክክር በር እንዳይከፍት መጠንቀቅ እንዳለባትም እንዲሁ… እንዲያውም ለዐመታት የምትታወቅበትን የገለልተኛነት ፖሊሲ ፈጽሞ ማጣት የለባትም ባይ ናቸው፡፡ ገለልተኛነቷ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን እንዳሁን ቀደሙ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የሚጣጣም ተለዋዋጭ ወይም በእንግሊዝኛው pragmatic የሚባለውን አካሄድ መከተል ጊዜው የሚጠይቀው እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡

ባሁኑ ጊዜ ዐለማቀፋዊ ክስተቶች በአፍሪካ አህጉር ላይ ስጋት ደቅኗል፤ ወደፊትም እየባሰበተ ሊሄድ ይችላል፡፡ እናም አፍሪካ የተባበረ ድምጽ እንዲኖራት ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ሚና መጫወት እንዳለባት እና ይህም ብሄራዊ ጥቅሟ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ በቀጠናው በምታደርገው እንቅስቃሴም የአፍሪካ ኅብረትን ማግለል ስህተት መሆኑንም ያነሳሉ፡፡ እዚህ ላይ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ስምምነት ሲደርስ አፍሪካ ኅብረትን አግልሎ የባህረ ሰላጤውን ሀገሮች እንደ አደራዳሪ መጠቀሙ ለተቀዳ እንዳልተዋጠላቸው መታዘብ ይቻላል፡፡ በርግጥም የሁለቱ ቱጃር ሀገሮች ሚና በትክክል ምን እንደሆነ፣ ከሁለቱ ድሃ ሀገሮች የሚፈልጉትስ ምን እንደሆነ እሰካሁን ግልጽ አልሆነም፡፡

የአዲሱ የውጭ ፖሊሲ አካሄድ ነባሩን ፖሊሲ ለነደፉት ሰዎች ጥላቻ በማሳየት ላይ መመስረት እንደሌለበትም ጠቅለል ያለ ምክራቸውን አስፍረዋል፡፡ ተቀዳ ይህን ሲሉ መለስ ዜናዊ የነደፉት የውጭ ፖሊሲ ብዙ ስኬቶችን ስላስገኘ በደፈናው እሳቸውን ተጠያቂ ከማድረግ እና ከማጣጣል መቆጠብ ያስፈልጋል ለማለት የፈለጉ ይመስላል፡፡ በዝርዝር ባያብራሩትም ነባሩ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ከሱማሊያ ሽብርተኞች ሰለጠበቃት ወደፊትም ያንኑ ጥሩ ጎኑን ወደ ጎን መግፋት አይገባም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

ባጠቃላይ ከምንጊዜው በተለየ ሀገሪቱ ግልጽ እና ጥርት ያለ የውጭ እና ብሄራዊ ደኅንነት ፖሊሲ መርሆዎችን የምትፈልግበት ወቅት አሁን መሆኑን ጠቅለል አድርገው አስቀምጠውበታል- ተቀዳ፡፡ ይህን ሲሉ የዐቢይ መንግሥት ከነባር የዲፕሎማሲ መርሆዎች ይልቅ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቹን ቢያንስ ላሁኑ በዘፈቀደ እያካሄደ መሆኑን በገደምዳሜ ለመግለጽ መፈለጋቸው እንደሆነ መናገር አያዳግትም፡፡

የዋዜማ አስተያየት- በርግጥም ዐቢይ የሚከተሉት የውጭ እና ብሄራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ምን ዐይነት መርሆዎች እና ቅርጽ እንዳለው አሁን አፍን ሞልቶ መናገር የሚቻል አይደለም፡፡ ያልጠራ የውጭ ፖሊሲና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ደሞ ሌሎች ሀገሮች ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትከተላቸው የነበሩትን ብሄራዊ ጥቅሞቿን እና የዲፕሎማሲ መርሆዎቿን የዐቢይ መንግሥት ትቷቸዋል ወይም ቀይሯቸዋል የሚል የተሳሳተ እሳቤ ሊፈጥር ይችላል፡፡ እዚህ ላይ “የተሳሳተ ዕሳቤ” ያልንበት ምክንያት የዐቢይ መንግሥት የውጭ ፖሊሲውን መሠረታዊ መነሻዎች፣ ነባር ብሄራዊ ጥቅሞችን እና ገዥ መርሆዎችን ወደፊትም ሊቀይር አይችልም ከሚል ዕምነት በመነሳት ነው፡፡ ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ

https://youtu.be/KSG__SsuJ0U