hmd AND SISIዋዜማ ራዲዮ-በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የተካረረውን የህዳሴው ግድብ ውዝግብ ተከትሎ የግብፅ የፓርላማ አባላት በመጪዎቹ ቀናት በካይሮ ጉብኝት የሚያደርጉት አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በሀገሪቱ ፓርላማ ተገኝተው ንግግር ለማድረግ የያዙትን ዕቅድ ተቃውመዋል።
የግብፅ ዕለታዊ ጋዜጣ እንደዘገበው አስራ ዘጠኝ የፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ወደሀገሪቱ ፓርላማ እንዳይመጡ ከባለሙያዎችና ከውሀና መስኖ ሚንስትር ጋርም እንዳይገናኙ የሚጠይቅ ማመልከቻ ለሀገሪቱ መንግስት አስገብተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያምን በግብፅ ፓርላማ እንዲናገሩ መፍቀድ ለኢትዮጵያ የልብ ልብ መስጠት ነው ብለው እንደሚያምኑ አብራርተዋል።

የግብፅ መንግስት በጉዳዩ ላይ ይፋ ምላሽ አልሰጠም።
በሁለቱ ሀገሮች መካከል በቅርቡ ሲደረግ በነበረው ድርድር በህዳሴው ግድብ ተፅዕኖ ዙሪያ በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ በተፈጠረው አለመግባባት አዲስ ውጥረት ተከስቷል።
በተያያዘ ዜና ባለፈው ስምንት በዩጋንዳ ካምፓላ በተደረገ የናይል ተፋሰሰ ሀገሮች ትምህርታዊ የልምድ ልውውጥ ጉባዔ ላይ የተገኘው የግብፅ ልዑካን ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱ ተነግሯል።
የግብፅ ልዑካን ስብሰባውን ረግጦ የወጣው ኢትዮጵያውያን በጉባዔው ላይ በፅሁፍ አቅራቢነት ተጋብዘው ከግብፅ ወገብ ማንም ተናጋሪ አልተጋበዘም በሚል ነው።
የጉባዔው አዘጋጆች መርሀግብሩን ከልሰው የግብፅ ልዑካን እንዲናገር ቢጋበዝም ስብሰባውን ረግጦ መውጣትን መርጧል።
በቅርቡ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በተከሰተው አለመግባባት ዙሪያ ዩናይትድ ስቴትስ ጣልቃ እንድትገባ የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ጠይቀዋል።
ግብፃውያኑ የህዳሴውን ግድብ ለሀገር ውስጥ የፖለቲካ ድጋፍ ማሰባሰቢያ እንደመሳሪያ የሚጠቀሙበት ሲሆን በተለይ ምርጫና የፖለቲካ ቀውስ በሚገጥማቸው ወቅት ውዝግቡን አጀንዳ አድርገው በማቅረብ ይታወቃሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት ከግማሽ በላይ የተጠናቀቀውን የህዳሴው ግድብ ለመስራት የማንም ፈቃድና ድጋፍ አያሰፈልገኝም ሲል የግብፅን ዛቻ ለማለዘብ ሲሞክር ይታያል።

ከውዝግቡ ጋር በተያያዘ በድምፅ የተሰናዳውን ዘገባ ከታች ያድምጡት

https://youtu.be/63wM6nIuo1c