Gambellaበጋምቤላ ክልል በንፁሀን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት ጉዳቱን “አድርሰዋል” በተባሉት የደቡብ ሱዳን ሙረሊ ታጣቂዎች ላይ የወሰደው እርምጃ በቂ አይደለም የሚል ወቀሳ እየቀረበበት ነው። ጥቃቱን ያደረሱትን ታጣቂዎች በእርግጠኝነት መለየት የተቸገረ የሚመስለው የኢትዮዽያ መንግስት ከስልሳ በላይ ሰዎችን ደቡብ ሱዳን ድንበር ድረስ ዘልቆ መግደሉን ተናግሯል።

የደቡብ ሱዳን መንግስት በበኩሉ ያለበቂ መረጃ የኢትዮዽያ ወታደሮች ድንበር ጥሰው በመግባት ግድያ መፈፀማቸው እንዳሳሰበው ገልጿል። የኢትዮዽያ እርምጃ አዲስ የጎሳ ግጭት ይቀሰቅስብኛል የሚል ስጋት ያደረበት የደቡብ ሱዳን መንግስት የኢትዮዽያ ጦር በሚወስደው እርምጃ የደቡብ ሱዳን ፈቃድ መጠየቅ ነበረበት ብሏል።

ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮዽያ መንግስት ጋር በመነጋገር ችግሩን በጋራ ለመፍታት እየተሞከረ ነው። አርብ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በአየር ሀይል የታገዘ የኢትዮዽያ ልዩ ሀይል ወደ ደቡብ ሱዳን ቢዘልቅም እስካሁን የገደላቸው የጥቃቱ ፈፃሚዎች ስለመሆናቸው በቂ ማረጋገጫ ሊገኝ አልቻለም። የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ባለፉት ሳምንታት ሀያ በላይ ኢትዮዽያውያንን በጋምቤላ ክልል ገድለው የሸሹ ሲሆን ችግሩ መኖሩ እየታወቀ መንግስት ለምን ሰራዊቱን በተገቢው ቦታ በማስፈርም ይሁን ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደዘገየ ግልፅ አይደለም።

የተገደሉ ዜጎች ቁጥር 208 ፣ የታገቱ ህፃናት ቁጥር ደግሞ ከ100 በላይ ደርሷል።

ተጨማሪ ዝርዝር ይዘን እንመለሳለን