Milkየኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ለተመጋቢዎች የሚቀርበው ወተት በአፍላቶክሲን “ተመርዟል” መባሉን እያስተባበለ ነው። ምርምሩን ያደረገው ዓለም አቀፍ የእንስሳት ጥናት ኢንስትቲዩት በእንግሊዘኛው ምህፃረ ቃል ILRI የተባለው ድርጅት ነው።
ኢንስትቲዩቱ ይህንን የምርምሩን ውጤት Food Control በተባለ የሳይንስ መጽሔት ላይ ባለፈው ሰኔ አሳትሞት ነበር። ጥናቱም አብዛኛው በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ለተመጋቢ የሚቀርበው ወተት ካንሰር አማጭ በኾነው አፍላ ቶክሲን የተባለ ንጥረ ነገር ከሚገባው በላይ የተበከለ ነው ብሎ ነበር። ይህ የሻጋታ ተረፈ ምርት የሆነው አፍላቶክሲን ለምሳሌ ኤም 1 የሚባለው አይነት በአንድ ሌትር ወተት ውስጥ ከ 0.05 ማይክሮ ግራም በላይ እንዲኖር አይመከርም ፡፡

(መዝገቡ ሀይሉ በድምፅ የተዘጋጀ ዝርዝር አለው አድምጡት)


ጥናቱ እንዳሳሰበው ይኸው አፍላቶክሲን የተባለ ንጥረ ነገር በካንሰር አምጭነቱ የታወቀ ከመኾኑም በተጨማሪ የሰውነትን የመከላከያ ኃይል የሚቀንስና እድገትን የሚገታ ባህርይ ያለው ነው። በዚህ ጥናት ምርመራ የተካሄደባቸው ናሙናዎች የተሰበሰቡት በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የሚገኙ 1 መቶ ወተት አምራቾችና 10 ወተት ሰብስበው የሚያከፋፍሉ ድርጅቶች ናቸው።

ጥናቱ እንደሚያሳየውም ሁሉም የወተት ናሙናዎች ይህ ንጥረ ነገር በተለያየ መጠን ተገኝቶባቸዋል። ይህን ያህል የተበከለ ወተት በከተማዋ መኖሩ 3 ሚሊዮን በሚበልጠው የከተማዋ ነዋሪ በተለይም ወተትን እንደዋነኛ ምግብ በሚመገቡት ሕፃናት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት አሳሳቢ ነው የሚል ድምዳሜም ተሰጥቶት ነበር።
ጥናቱ በከብቶች መኖም ላይ ያለውን የአፍላቶክሲን መጠን መመርመሩን ይግልጻል። ለከብት እንደመኖ በጥቅም ላይ ከሚውሉትም ነገሮች መካከል የዘይት ፋብሪካዎች ተረፈ ምርት የኾነው ፋጉሎ ዋነኛው የመርዙ ምንጭ መኾኑንም አሳይቷል። ከፋጉሎም ሌላ በቆሎን በመሰሉ ለከብቶች በምግብነት የሚቀርቡም ጥራጥሬዎች ላይ የሚፈጠረው ሻጋታ ለአፍላ ቶክሲን መፈጠር ምክንያት መኾኑንም አስታውሷል።

ይህ ጥናት ለህትመት ከበቃ በኋላ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሰጥተውት ነበር። አሁን ከመንግስት የመገናኛ ብዙኃን እየተሰማ ያለው ግን መንግስት የጉዳዩ አሳሳቢ እንዳልኾነና ቀድሞ በተዘገበው መጠን አስጊ አለመኾኑን ለማሳመን ጥረት ማድረግ ነው።

ችግሩ አሳሳቢ ነው በማለት አስቸኳይ ርምጃ እንዲደረግበት ሲጠይቅ የነበረው ILRIም አስቀድሞ ከሰጠው ማሳሰቢያ የተለየ መግለጫ አውጥቷል። ለጥናቱ የተጠቀመባቸው ሁሉም የወተት ናሙናዎች በአፍላ ቶክሲን የተመረዙ መኾናቸውንና ከነዚህም መካከል 92% የሚኾኑት በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅትና በ FAO ከተቀመጠው ዝቅተኛ መጠን ያለፈ መበከል እንደሚታይባቸው አሳይቶ ነበር። ይኸው ጥናትና ጥናቱን ተከትሎ የተሰጠው ገለጻ እስካሁንም ድረስ በየድረገጾቹ ይገኛል።
International Livestock Research Institute (ILRI) ቀድሞ በታተመው ጥናት ላይ 92 በመቶ የሚኾነው የወተት ናሙና ያለበትን አደገኛ ኹኔታ ቢያሳይም አሁን በወጣው መግለጫ ላይ ደግሞ 92 በመቶ የሚኾነው የወተት ናሙና በአውሮፓ የጥራት ደረጃ መሰረት ሲታይ በአስጊ ሁኔታ የተበከለ ቢመስልም አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች በብዙ አገሮች ባለው ደረጃ መሰረት የመበከሉ መጠን የሚያሳስብ አይደለም ይላል መንግስት። እንዲያውም ከአሜሪካው የመበከል መጠን ደረጃ በአማካይ ያነሰ ነው የሚልም መከራከሪያ አቅርቧል።
ኢትዮጵያ ምግብ እንዲህ ባሉ መርዞች መበከላቸውን የሚቆጣጠሩበት ደረጃ ከሌላቸው ጥቂት የዓለም አገራት አንዷ ነች። ከዚህ በፊት በርበሬና ለውዝ ተመሳሳይ ጥናት ተደርጎባቸው ይኸው መርዝ ተገኝቶባቸው ነበር። ይሁንና የጥናቱ ውጤት ያስከተለው ርምጃ አልታየም። እስካሁንም ይህን ለማድረግ ዝግጅት ያለ አይምስልም። ከሌሎች ምግቦች መበከል ጋር ሲነፃጸር አሳሳቢ የሚኾነው የወተት መበከል መኾኑን ባለሞያዎች ይናገራሉ። በወተት ላይ ይህን የመሰለ ጥናት በኢትዮጵያ ሲደረግም ይህ የመጀመሪያው እንደኾነ ተነግሯል።
በአፍሪካ በቀዳሚነት የሚጠቀስ የቀንድ ከብት ብዛት ያላት ኢትዮጵያ በወተት አቅርቦት በኩል የታደለች አይደለችም። በአፍሪካም ቢኾን ዝቅተኛ የወተት አቅርቦት ያለባት አገር ናት። ከምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ኬንያ 120 ሌትር ወተት በአመት ለአንድ ሰው በምግብነት የሚቀርብባት አገር በመኾኗ በቀዳሚንት የምትጠቀስ አገር ስትኾን ኢትዮጵያ ከሁሉም የምስራቅ አፍሪካ አገራት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 20 ሌትር በዓመት ለአንድ ሰው የደርሳል። ይህ የወተት አቅርቦት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አስፈላጊ ከታየው በዓመት ለ አንድ ሰው 200 ሌትር የማድረስ ግብ ጋር ሲተያይ ያለንበትን ደረጃ በጣም ዝቅ ማለት ያጎላዋል።
በዚህ የወተት አቅርቦት አንስተኝነት ላይ ለሰው ሕይወት አደጋ የሚያስከትሉ እንደ አፍላቶክሲን ያሉ መርዞች መከሰታቸው ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።