Donald-Yamamotoዋዜማ ራዲዮ- የአፍሪቃ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ከፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ጋር በፀጥታና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ ለመመካከር ዛሬ ሀሞስ ዋሸንግተን ተሰብስበዋል።
ስብሰባውን ያዘጋጁት የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሪክ ቲለርሰን ሲሆኑ በአፍሪቃና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል በግርታ ተውጦ የቆየውን ግንኙነት ለማጥራት ያለመ ነው። ጉባዔው ለሁለት ቀናት ይቆያል።

በተለይ በፀጥታና ልማት ትብብር ዙሪያ አዲስ ፖሊሲ ለመቅረፅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ጊዜያዊ ረዳት ሀላፊ ዶናልድ ያማማቶ ተነግረዋል። ያማማቶ ረቡዕ ዕለት በጉዳዩ ላይ ለአፍሪቃ ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡ ሲሆን ጉባዔው ላለፈው አንድ አመት ምላሽ ሲጠብቁ የነበሩ የአፍሪቃ ጉዳዮችን በፖሊሲ ደረጃ ምላሽ ለመስጠት በዶናልድ ትራምፕ በኩል ፍላጎት መኖሩን ተነግረዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ለአፍሪቃ የሚመደበውን የልማት ዕርዳት ከመቀነስ ጀምሮ ለአስራ አራት ሀገሮች አምባሳደር ያለመመደቡ ለአህጉሪቱ ያለውን ዝቅተኛ የወዳጅነት ፍላጎት ሲያንፀባርቅ ቆይቷል።
በውጪ ጉዳይ ሚንስትሮቹ ጉባዔ ላይ ከፀጥታ ትብብር የዘለለ አዲስ ነገር እንደማይጠብቁ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የቀድሞ ባልደረቦች ይናገራሉ።
“ትራምፕ ስለ አፍሪቃ አያውቁም፣ በሀገር ቤት የገጠማቸውም ፖለቲካዊ ፈተና ስከን ብለው ነገሮችን ለማሰብ አላስቻላቸውም። አፍሪቃ ልትጠቅም የምትችልበትን ፖሊሲ ለመቅረፅ በቂ ዝግጅትና ፍላጎት ያለ አይመስለኝም” ትላለች በመስሪያ ቤቱ ለአስራ ስድስት አመት ያገለገለች ባልደረባ።
“ያሁኑ ጉባዔ በውጪ ጉዳይና በመከላከያ መስሪያ ቤቱ ውትወታ የተዘጋጀ ነው። እንዳውም ሊቀር ነበር”  ስትል ታክላለች።
ዶናልድ ያማማቶ ግን በጉባዔው የአፍሪቃና የዩናይትድ ስቴትስ የጋራ ጥቅሞችን በመነጋገር የተሻለ ፖሊሲ ለማዘጋጀት ፍላጎት አለ ሲሉ ይከራከራሉ። ከኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ይሳተፋል።