ዋዜማ- ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመለት የሥራ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ.ም የሚጠናቀቅ መሆኑን ተከትሎ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ሽኝት ተደርጎላቸዋል። ኮሚሽኑ ከሐምሌ 08 እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ያካሄደውን የምክክር ጉባኤ ተከትሎ የተጠናቀሩ 394 ምክረ ሀሳቦችን እና ከእነዚህ ምክረ ሀሳቦች መካከል በልዩነት “አንገብጋቢ” ናቸው ያላቸውን 81 ምክረ ሀሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስረከቡን በማንሳት “ሥራዬን በስኬት አጠናቅቄአለሁ” ሲል የኮሚሽነሮቹ ሥራ መጠናቀቁን ይፋ አድርጓል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 ኮሚሽኑ በምክክር የተገኙ ምክረ ሀሳቦችን ይፋ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ቢገልጥም፤ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ይህንን ኃላፊነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመስጠት ሥራቸውን ማጠናቀቃቸውን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት፤ ሰነዶችን በተለያየ መልኩ ለመሠነድ ለተጨማሪ ጊዜያት በሥራ ላይ እንደሚቆይ ቢገለጥም፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት ኮሚሽነሮች ግን በአዋጅ የተሰጣቸውን “የምክረ ሀሳቦች አፈጻጸምን ለመከታተል የሚያስችል ሥርዓት የመዘርጋት” ኃላፊነትንም ለፓርላማ አሳልፈው ሰጥተዋል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርአያ፤ የምክክር ምክረ ሀሳቦችን ለስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያስረክቡ፣ ይህም እስከ መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ እንደሚከናወን ገልጠው የነበረ ቢሆንም፤ መስከረም 23 ቀን በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደ መርሃ ግብር ምክረ ሀሳቦችን ለምክር ቤቱ የቀድሞ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ማስረከባቸው ይታወሳል። የምክክር ጉባኤው ከተጠናቀቀበት ቀን በኋላ ያሉ ሂደቶች ግልጽነት የጎደላቸው ናቸው ሲሉ ለዋዜማ የገለጡ የኮሚሽኑ ባልደረባ፤ የሥራ ዘመኑን አጠናቅቆ የተበተነው ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠርቶ ምክረ ሀሳቦችን እንዲረከብ ለማድረግ ተይዞ የነበረው ዕቅድ ግልጽ ባልተደረገ ምክንያት መሰረዙን ነግረውናል።
ምክረ ሀሳቦች ይፋ እንዲደረጉ የጠየቁ ወገኖች
ኮሚሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስረከባቸውን ምክረ ሀሳቦች የያዘውን ሰነድ ይፋ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን የነገሩን በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደው የአጀንዳ ማስረከቢያ መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር፤ ያቀረቡት ጥያቄ በወቅቱ መልስ አለማግኘቱን ገልጠዋል። የምክረ ሀሳብ ሰነዱን ለማግኘት ለኮሚሽኑ በደብዳቤ ጥያቄ እንዲያቀርቡ እንደተነገራቸውም አረጋግጠውልናል። ፓርቲያቸው፤ ኮሚሽኑ ከምክክር ጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ እያከናወነ ስለሚገኘው ተግባር የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኮሚሽኑ ማስገባቱን ለዋዜማ የገለጡ የፓርቲ አመራር ደግሞ፤ ምክረ ሀሳቦች ይፋ እንዲደረጉ ጭምር የሚጠይቀው ደብዳቤ ምላሽ እንዳላገኘ ነግረውናል።
ለጥያቄው መልስ ያላገኘው አማካሪ ምክር ቤት
ኮሚሽኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አሳትፎ ያቋቋመው አማካሪ ምክር ቤት ከምክክር ጉባኤው መጠናቀቅ ጀምሮ ከኮሚሽነሮች ጋር ስብሰባ ማካሄድ አለመቻሉን ምንጮች ነግረውናል። የምክር ቤቱ አባላት እየተከናወኑ ስላሉ ሥራዎችና የምክክር ምክረ ሀሳቦች ይፋ ስለሚደረጉበት መንገድ ውይይት እንዲካሄድ፣ ኮሚሽነሮችም ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቃቸውን የነገሩን ምንጫችን፤ ኮሚሽነሮች ግን ለአማካሪዎች ጥያቄ ምላሽ አለመስጠታቸውን ገልጠውልናል።
ኮሚሽኑ ለአማካሪ ምክር ቤት አባላት ቅዳሜ ጥቅምት 07 ቀን ባዘጋጀው የምስጋና መርሃ ግብር ላይም ከምክረ ሀሳቦች እንዲሁም ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የተደረገ ውይይትም ሆነ የተሰጠ መረጃ አለመኖሩን ሰምተናል። በመርሃ ግብሩ ላይ በርካታ የኮሚሽኑ ሠራተኞች መገኘታቸው፤ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማካሄድ አለማስቻሉን የነገሩን ምንጫችን፤ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ከአማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ለመወያየት ፍላጎት አለማሳየታቸውን ገልጠዋል።
የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት እጣ ፋንታ
የኮሚሽኑ ስምንቱ ኮሚሽነሮች ከጥቅምት 15 ቀን ጀምሮ በኮሚሽኑ ስም እንደማይንቀሳቀሱ የገለጡ ሲሆን፤ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ የሥነዳ ሥራ እንደሚያከናውን ሰምተናል። በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ተጠሪነቱ ለዋና ኮሚሽነሩ የሆነ ኃላፊ የሚመራው ጽሕፈት ቤት የኮሚሽኑን የአስተዳደርና የፋይናንስ አገልግሎት ይሰጣል። ዋና ኮሚሽነሩ ከጥቅምት 15 ጀምሮ በሥራቸው የማይቀጥሉ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘም፤ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን መወሰኑን ምንጮች ነግረውናል። ይሁንና ኮሚሽኑም ይሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ጽሕፈት ቤቱ ዝርዝር ኃላፊነትና ቁርጥ የሥራ ጊዜ በግልጽ ያሉት ነገር የለም። [ዋዜማ]
