addis Ababa condominiumዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ካቢኔ ከሰሞኑ ዉሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮች ላለፉት አስር ዓመታት ሲንከባለሉ የነበሩ ናቸው፡፡ በሕገወገጥ የማኅበር ቤቶች፣ በልማት ተነሺ አርሷደሮችና የግንባታ መጀመርያ ጊዜ ባለፈባቸው አልሚዎች ላይ ቁርጥ ዉሳኔ አሳልፎ ተግባራዊ እንዲደረጉ ወደ ክፍለ ከተማ የይዞታ ኃላፊዎች መርቷቸዋል፡፡

የግንባታ መጀመርያ ጊዜ ያለፈባቸው አልሚዎች ከዚህ ቀደም በማንኛውም ሁኔታ እንዳይሰተናገዱ ራሱ ያስተላለፈውን ዉሳኔ በመሻር ‹‹ሁሉንም አልሚዎች ለመጨረሻ ጊዜ እድል ሰጥታችሁ አስተናግዷቸው›› የሚል መመሪያ ተላልፏል፡፡ የግንባታ መጀመርያ ጊዜ እንደ ግንባታው ስፋትና ዉስብስብነት ከ3- ወር እስከ አንድ ዓመት ተኩል የሚሰጥ ሲሆን በዚህ ጊዜ ግንባታ ያልጀመሩ አልሚዎች አጥጋቢ ምክንያት እስካላቀረቡ ድረስ ቦታቸው እንዲመክን ይደረግ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ደንብና መመሪያ ለሁሉም ዜጋ እኩል አያገለግልም ነበር፡፡ ለአብነት ያህል ከፍተኛ ባለሀብት የሆኑት ሼክ መሐመድ ሑሴን አላሙዲ በከተማው ልዩ ልዩ ስፍራዎች አጥረው የያዟቸው ቦታዎች ምንም አይነት ግንባታ ሳያካሄዱባቸው ከ5 እስከ 18 ዓመታት ቢቆዩም እስካሁን ቁርጥ እርምጃ ሳይወሰድባቸው ቆይቷል፡፡ ይህም በከተማዋ ኃላፊዎች ሳይቀር ኃፍረትን የፈጠረ ጉዳይ ነበር፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የሼኩ ይዞታዎች ግንባታ በወቅቱ ባለመጀመራቸው ካርታዎቻቸው ሙሉ በሙሉ እንዲመክኑ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ባለሀብቱ በግል አውሮፕላናቸው በአስቸኳይ ወደ አገር ቤት በመምጣት አሁን የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ሙክታር ከድርን ይዘው ከከንቲባው ጋር ባደረጉት የግል ውይይት የመጨረሻ የተባለውን ዉሳኔ ማስቀልበስ ችለው ነበር፡፡ እርሳቸው ግንባታ ላለመጀመራቸው ያቀረቡት ምክንያት አንድም ቦታዎቹ ላይ የዲዛይን ለውጥ በማስፈለጉ፣ በሌላ መልኩ ደግሞ በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ዉስጥ እያስገነቡት ያለውን  ግዙፍ ሆቴል የመሰሉ የዉጭ ምንዛሪን ማምጣት የሚችሉ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ፕሮጀክቶች ስላሉባቸውና እንዲህ አይነቶቹ ፕሮጀክቶች አገራዊ ፋይዳቸው ከፍ ያለ በመሆኑ ትኩረታቸውን በነዚህ ላይ በማድረጋቸው እንደሆነ ተናግረው ማሳመን ችለው ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወረደ መመሪያ ሁሉም የመከኑ ካርታዎቻቸው በአስቸኳይ እንዲመለሱላቸው ተደርጓል፡፡ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ሼክ አላሙዲንን በተመለከተ በየደረጃው ይኸው ተግባራዊ እንዲደረግ ትእዛዝ ተላልፎ ነበር፡፡ በወቅቱ የመከኑ ካርታዎቻቸውን መልሶ ለመስጠት የዘገዩ የክፍለከተማ ኃላፊዎች በማዕከል አለቆቻቸው ከፍተኛ ተግሳጽ ደርሶባቸው እንደነበር የዋዜማ ምንጮች ያወሳሉ፡፡

የሚገርመው ይህ ከሆነ ከዓመታት በኋላም ቢሆን ባለሀብቱ ያሳዩት አንዳችም ለውጥ አለመኖሩ ነው፡፡ በፒያሳው ፕሮጀክት የተወሰኑ የግንባታ እንቅስቃሴዎችና ማሽነሪዎች ታይተው ወዲያው ከስመዋል፡፡ በካዛንቺስ፥ በፍልዉኃ ና በፖሊስ ጋራዥ አንድም ለውጥ ሳይታይ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ፖሊስ ጋራዥ ከሰሞኑ ሙሉ በሙሉ በመፍረስ ላይ ቢሆንም፡፡

በጀርመን አደባባይና በለቡ ሬይስ ኢንጂነሪንግ አካባቢ ከልለው የያዟቸው ቦታዎች የትልልቅ ማሽነሪዎች ማደሪያ ከመሆን አላለፉም፡፡ ሼኩ በሁሉም ይዞታዎቻቸው ላይ አፋጣኝ ግንባታ ለማካሄድ አቶ አብነት ገብረመስቀልን ልዩ ሹመትና ዉክልና በመስጠት ሁዳ ሪልስቴትን እንዲመሩ ሾመዋቸው የነበረ ሲሆን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ዛሬም ድረስ ግንባታ አልጀመሩም፡፡ ካቢኔው አሁን ያስተላለፈው ዉሳኔ የመጨረሻ መጨረሻ እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡ አሁን ለባለሀብቱ የመጨረሻ የተባለ ዕድል የሰጠ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ አቶ አብነት በባለፈው ሳምንት በግንባታ ፈቃድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ቢሮ ተገኝተው  መወያየታቸውን የዋዜማ  ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

አዲሱ የካቢኔ ዉሳኔ ሼኹን ብቻ ሳይሆን ቦታ በሊዝ ወስደው ግንባታ ያልጀመሩና የግንባታ መጀመርያ ጊዜ ላለፈባቸው አልሚዎች ተመሳሳይ እድል የሚሰጥ ነው፡፡ አልሚዎችን በዚህ ደረጃ ካርታቸውን ከማምከን ይልቅ አንድ የመጨረሻ ዕድል እንዲሰጣቸው ዉሳኔ ተላልፏል፡፡ ዉሳኔው የሼክ አላሙዲንን ይዞታዎች ተከትሎ ይሁን አይሁን ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡

ከዚህ ቀደም ግልጽ አድልዎን በሚያንጸባርቅ ሁኔታ የአንዳንድ አልሚዎች ካርታ እንዲመክን ሲደረግ የሌሎች ግን ቸል ይባል ነበር፡፡  ‹‹እንዴት አንድ አስተዳደር ሁለት አይነት አሰራር ይኖረዋል›› የሚለው ቅሬታ በብዙ አልሚዎች ዘንድ መነሳቱም አልቀረም፡፡ በተለይም ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነውና ለገዢው ፓርቲ ቅርብ እንደሆነ የሚነገርለት የሪፖርተር ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ዘገባ በመስራት አሰራሩን ሲቃወም መቆየቱ አሁን ለተላለፈው ዉሳኔ ምክንያት ሳይሆን አልቀረም፡፡  ይህ በንዲህ እንዳለ ከዚህ ቀደም በወቅቱ ግንባታ ሳይጀምሩ ቀርተው ካርታቸው የመከነባቸውን ባለሀብቶች ይህ መመሪያ እንዴት እንደሚያስተናግዳቸው የታወቀ ነገር የለም፡፡ የዋዜማ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ግን መመሪያው ወደኋላ ሄዶ የሚሰራ ከሆነ ብዙ ምስቅልቅል መፍጠሩ እንደማይቀር ይናገራሉ፡፡ ‹‹በሺ የሚቆጠር መሬቱን የተቀማ አልሚ ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ‹ና ካርታ ተመልሶልሀል መሬትህን አልማ› ሊባል አይችልም›› ይላሉ የዋዜማ ምንጮች፡፡ ይህ ከሆነ ግን ነገሩ አስገራሚ ይሆናል፡፡

የማኅበር ቤቶችን በተመለከተ ካቢኔው ባስተላለፈው ዉሳኔ ከ1997 ጀምሮ በሕገወጥ መንገድም ይሁን በሕጋዊ መንገድ በማኅበር የተያዙ ቦታዎች ፍርድ ቤትና ፀረሙስና ጉዳያቸውን ካልያዘው በቀር ካርታ እንዲሰጣቸውና አማካይ የሊዝ ዋጋ ከፍለው ወደ ግንባታ እንዲገቡ የሚል ያልተጠበቀ መመሪያ አስተላልፏል፡፡ ምርጫውን ተከትሎ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ሐሰተኛ የሆኑ ማኅበራት እንደ አሸን ፈልተው በአዲስ አበባ ዙርያ ቦታ በወረራ ወስደው እንደነበር ይታወሳል፡፡ መስተዳደሩ ከፊሎቹ መጠነኛ ግንባታ በመጀመር ህጋዊ ለመሆን ያደረጉትን ጥረት  በማገድ ለ10 ዓመት ያህል  ምርመራ ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡ በተለይም በከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ ዘመን በብዛት ተፈጥረው ከነበሩት ሐሰተኛ ማኅበራት ከፊሎቹ በግለሰቦች እንጂ በማኅበር ያልተያዙ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህ መመሪያ በጥቅል ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ሁሉንም ወደ ሕጋዊነት መስመር ለማስገባት ሲባል ‹‹ካርታ ተሰጥቷቸው፣ የሊዝ ክፍያ ፈጽመው ወደ ግንባታ እንዲገቡ ይደረግ›› የሚል ትዕዛዝ ወደ የክፍለከተሞች ተልኳል፡፡ በዚህ ያልተጠበቀ በተባለ ዉሳኔ ደብዳቤ ላይ ‹‹በጥንቃቄ ይስተናገዱ›› የሚል አረፍተ ነገር ከመካተቱ ዉጭ የተብራራ የአፈጻጸም መመሪያ የለበትም፡፡

የልማት ተነሺ አርሷደሮችን በተመለከተ ካቢነው ባስተላለፈው አዲስ መመሪያ ማንኛውም ተነሺ አርሷደር ይዞታው በ19 88 እና በ1997 በተወሰደው የአየር ካርታ ላይ እስከተገኘ ድረስ በልማት ምክንያት የሚነሳ ከኾነ 500 ካሬ ቦታ በምትኩ ለባለቤቶቹ እንዲሰጥ፣ የቤት ግምትና ለግጦሽ መሬቱ ደግሞ የገንዘብ ካሳ እንዲከፈል ዉሳኔ አሳልፏል፡፡ የካሳ ክፍያው በሂደት እንደሚሻሻልም ጥቆማ ሰጥቷል፡፡

በዚህ የካቢኔው ውሳኔ ላይ እስከዛሬ ባልተለመደ መልኩ ለአርሷደር ልጆችም ልዩ የካሳ መብት  እንዲሰጥ ያዛል። በተነሺ አርሷደር ቤት ለሚገኙ የአርሷደር ልጆች 150 ካሬ ሜትር ቦታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲሰጥ ያዛል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር የአርሷደር ልጆች ምትክ ቦታ ለማግኘት የነበራቸው እድል በጣም አነስተኛ ነበር፡፡ እንደ መመዘኛም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ፣ ትዳር የመሰረቱና ከአባወራው አርሷደር ጋር በአንድ ግቢ ቤት ተሰርቶላቸው ይኖሩ እንደነበር ለማስመስከር ይገደዱ ነበር፡፡

ካቢኔው ያሳለፈው ያልተጠበቀ ውሳኔ ከዓመታት በኋላ በድንገት በመምጣቱ የኦሮሚያውን አመጽ ለማርገብ ታስቦ የተላለፈ ውሳኔ ሳይኾን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ ከአንድ ወር በፊት በተደረገ ሌላ እንቅስቃሴ ”ተፈናቃይ አርሷደሮችን ዘላቂ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው”  የተባለለት አዲስ ፕሮጀክት መጀመሩ ሲነገር ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ ዳጎስ ያለ የካሳ ጭማሪ ከመስጠቱም ጎንለጎን አርሷደሮች በዘላቂነት ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ተብሎለታል፡፡

ካቢኔው ከሁለት ሳምንት በፊት ባሳለፈው ሌላ ያልተጠበቀ ዉሳኔ በሕገወጥ ወረራ የተያዘ ይዞታ ከ1988 በፊት በነበረው የአየር ካርታ መታየቱ ከተረጋገጠ የሊዝ መነሻ ዋጋ ከፍሎ 75 ካሬ ሜትር ብቻ በሕጋዊነት መውሰድ ይቻላል የሚለውን ዉሳኔ በማሻሻል ‹‹በሊዝ መነሻ ዋጋ 150 ካሬ ማካተት ይቻላል›› የሚል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ የሊዝ ክፍያ መነሻ ዋጋ 191 ብር ሲሆን በዚህ ዋጋ በሕጋዊ ይዞታነት ሊያዝ የሚቻለው የመሬት ስፋት እጥፍ መደረጉ ብዙዎችን አስፈንጥዟል፡፡ ሰፋፊ ቦታዎችን ከ19 88 በፊት የያዙ ግለሰቦች ከ 75 ካሬ ሜትር  በላይ  ያለውን  ይዞታቸውን የአካባቢው አማካይ የሊዝ ዋጋ እስካልከፈሉ ድረስ ማካተት አይችሉም ነበር፡፡ ይህ ደንብ ይዞታቸውን ቆርሰው ለባለሀብቶች እንዲሸጡ ያስገድዳቸው ነበር፡፡ አሁን የተሻሻለው መመሪያ 150 ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ መነሻ ዋጋ እንዲወስዱ ይፈቅዳል፡፡

ካቢኔው ከዚህ በኋላ በሚኖረው ስብሰባው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተግባራዊ ስለተደረገው በሊዝ ክፍያ ላይ የተጣለ ተደራራቢ የወለድ ክፍያ ዉሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡