በሳምንቱ ማብቂያ አዲስ የፀረ ሙስና ዘመቻ ተጀምሯል። መንግስት ስልሳ የሚጠጉ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎችን በቀጥጥር ስር አውሎ ጉዳያቸው እየተመረመረ ይገኛል። እነማን ታስሩ? በምንስ ወንጀል ተጠረጠሩ? ዋዜማ ጉዳዩን በበቂ ጥልቀት አቅርባለች። አንብቡት

ዋዜማ ራዲዮ- በፌደራል ፖሊስ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ከጥር ወር ጀምሮ ምርመራ ሲደረግባቸው ከቆዩ የሙስና ወንጀል መዝገቦች መካከል ሶስቱ ዛሬ ፍርድ ቤት ፋይል ተከፍቶላቸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ በፅህፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ እስካሁን 59 ገደማ የሚሆኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ይፋ አድርጓል፡፡


ሆኖም ትናንት ሚያዚያ 3 ቀን 2011 ዓም በቁጥጥር ስር የዋሉ እና በእነዚህ መዝገቦች የተካተቱ 21 ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችም ሚያዚያ 4 ቀን 2011 ዓም 10 ሰዓት ገደማ መዝገቡ በተከፈተበት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡


ለችሎቱ የቀረበው ሶስት መዝገብ ሲሆን ይህም ከመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ ከመድሀኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ እና ከኮንስትራክሽን ስራዎች ኤጀንሲ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ችሎቱ መጀመርያ ያስተናገደው ከመንገስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ኤጀንሲ ጋር በተያያዘ የቀረበለትን ጉዳይ ሲሆን በዚህ ውስጥም 7 ተጠርጣሪዎች ተካተውበታል፡፡
እኚህም አቶ ተስፋዬ ብርሀኑ፣ አቶ ሰሎሞን ኤኒመር፣አቶ ዮሴፍ ራፊሶ፣ አቶ ተክለብርሀን ገ/መስቀል፣አቶ ትሩፋት ነጋሽ፣ አቶ ዘርይሁን ስለሺ እና የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መንግስቱ ከበደ መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡


ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ጉዳይ በችሎት የተነበበ ሲሆን ለኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አገልግሎት ለገበያ ማረጋጊያ አላማ የሚውል 400, 000 ሜትሪክ ቶን ስንዴን ለመግዛት የመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ያወጣውን ጨረታ  በዝቅተኛ ዋጋ ማለትም 1ኛ የወጣው በ96.4 ሚሊየን ዶላር ወይንም 2ኛ የወጣው 98.4 ሚሊየን ዶላር እና 3ኛ 110.7 ሚሊየን ዶላር በጨረታው አሸናፊ ከሆኑት አቅራቢዎች መግዛት ሲገባቸው የውል ማስከበርያ አልቀረበም በሚል ምክኒያት ጨረታው እንዲሰረዝ እንደተደረገ ተገልፅዋል፡፡


ይህንንም አሁን ላይ በቁጥጥር ስር ካልዋሉ ግብረዓበሮቻቸው ጋር እንዳደረጉት የፖሊስ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ጨረታው ከተሰረዘ በኋላ ሌላ አዲስ ጨረታ እንዲወጣ በማድረግ ከአሸናፊው ተጫራች መንግሰትን ተጨማሪ ወጪ በማስወጣት 115.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ከተባለ ድርጅት እንዲገዛ አድርገዋል ብሏል፡፡
መንግስትንም በልዩነት የ17 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጣ አድርገዋል ተብሏል፡፡


አክሎም ከኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት በ1992 ዓም በተላለፈው መመርያ መሰረት በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መርከብ መጓጓዝ የሚገባውን ስንዴ በግል መርከብ እንዲጓዝ በማድረግ መንግስት 6 ሚሊየን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንዲያጣ አድርገዋል ሲል አካቷል፡፡


እስካሁን በነበረው የምርመራ ጊዜ የተለያዩ ሰነዶችን ከተለያዩ መስርያ ቤቶች መሰብሰባቸውን፣ የ18 ግለሰቦችን የምስክርነት ቃል መቀበላቸውን፣ በመንግሰት ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ በፌደራል ዋና ኦዲተር የምርመራ ኦዲት ማሰራታቸውን  ለችሎቱ ባስገቡት የፅሁፍ ሪፖርት ውስጥ ተካቶ ተነቧል፡፡


ሆኖም ከዚህ በኃላ ደግሞ ቀሪ የምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ያልተሰበሰቡ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰብ እና ከተጠርጣሪዎች የተገኙ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በሚመለከተው አካል ማስመርም ይቀረናል ብለዋል፡፡
እናም እነዚህም የምርመራ ስራዎች ለመስራት ፍርድ ቤቱ በስነስርዓት ህጉ አንቀጽ 59 መሰረት 14 ቀን እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡


በፍርድ ቤቱ በቀጣይ የሚኖራቸውን የክርክር ጊዜ አስመልክቶ ችሎቱ በምን አይነት ሁኔታ ክርክራቸውን እንደሚያደርጉ ለተጠርጣሪዎች ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ሁሉም ተጠርጣሪዎችም በየተራ ጉዳያቸውን በጠበቃ በኩል መከራከር እንደሚፈልጉ ነገር ግን ለጠበቃ የሚከፈል በቂ ገንዘብ የሌላቸው በመሆኑ መንግስት እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡


ፖሊስ ግን በብርበራ ወቅት በርካታ የመኪና ሊብሬዎች እና የቤት ካርታዎች እንዲሁም በባንክ ደብተራቸው ገንዘብ ያገኘ መሆኑን ለችሎት በመግለፅ የተጠርጣሪዎችን ጥያቄ ተቃውሟል፡፡


ሆኖም ግን አለኝ ከማለት ባለፈ በጊዜው ለችሎቱ ማቅረብ የሚችለው ማስረጃ ስላልነበረ ችሎቱ በቂ ሀብት እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ ካለው በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ለጊዜው ተቃውሞውን ውድቅ አድርገውታል፡፡
ይህን ተከትሎም ተጠርጣሪዎች እንደየ እምነታቸው ሀብት ንብረት የሌላቸው ስለመሆኑ ከማሉ በኋላ የመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ 


እናም የዚህን ጉዳይ የጊዜ ቀጠሮ ክርክር  ሰኞ ለማድረግ ቀጠሮ ተይዟል፡፡
ችሎቱ ሌላኛው የተመለከተው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽንን ጉዳይ ነበር፡፡በዚህ መዝገብ 10 ተጠርጣሪዎች የተካተቱ ሲሆን ጥቂቶቹ አሁን ላይ በዛ መስርያ ቤት እንደማይሰሩ ለችሎት ገልፀዋል፡፡ 


አታክልቲ ተካ፣ አንተነህ ቻለው፣ ብሩክ ዳንኤል፣ ይገርማል ሀይሉ፣ መልሳቸው ካሳ፣ ይልቃል ወርቁ፣ዘውዱ ጌታቸው፣ ሚፍታ ከማል፣ የሰራህ የሻው፣ እና ሳለህ ስሩሩ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ ለእነሱም በምን ጉዳይ ተጠርጥረው ችሎት እንደቀረቡ ተነቧል፡፡
በዚህም ከ2003- 2008 ባለው ጊዜ በአርማታ ብረት ግዥ እና ሌሎች ግዥዎች እንዲሁም የኪራይ መሳርያዎች እና የመኪና ኪራይ በሚል 65.4 ሚሊየን ዶላር የግዥ መመርያን በመጣስ ወጪ እንዲሆን አድርገዋል ሲል ፖሊስ የጠረጠረበትን አስቀምጧል፡፡
በዚህ መዝገብ ላይም በርካታ ሰነዶችን መሰብሰቡን እና የምስክሮችን ቃል መቀበሉን ገልጽዋል፡፡


ነገር ግን ቀጣይ የሚቀሩት የምርመራ ስራዎች በመኖራቸው በዚህኛውም መዝገብ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
በዚህ መዝገብ ላይ አታክልቲ ተካ፣ ይልቃል ወርቁ፣ዘውዱ ጌታቸው፣ የሰራህ የሻው የተባሉት ተጠርጣሪዎች ጉዳያችንን ለጊዜው በራሳችን እንከራከራለን ያሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ጠበቃ ለማቆም በቂ ገንዘብ የሌላቸው መሆኑን ለችሎቱ በማስረዳት የመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡


እናም ከላይ ከነበረው መዝገብ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ችሎቱ ተከላካይ ጠበቃ ለጠየቁት እንዲቆምላቸው ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን በራሳችን እንከራከራለን ያሉትን ደግሞ አዳምጧል፡፡


አቶ አታክልቲ በበኩላቸው እስካሁን የተጠቀሱትን በጠቅላላ በተደጋጋሚ ምላሽ ስጥተንበት የነበረ ጉዳይ በመሆኑ አሁን ላይ ፖሊስ የተደራጀ መዝገብ ነው የሚኖረው ያሉ ሲሆን በዚህም ምክኒያት የተጠየቀው ጊዜ ብዙ በመሆኑ ቀረብ ይበልልን ብለዋል፡፡
አቶ ይልቃል ደግሞ መስሪያ ቤቱን በ2007 ዓም መልቀቃቸውን በመጥቀስ የጊዜ ቀጠሮው እንዲቀርብ አልያም ደግሞ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው የጠየቁ ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለቱም ተመሳሳይ ሀሳብ ለችሎቱ አሰምተዋል፡፡


እንዲሁም ማን ምን ሰራ የሚለውን ተለይቶ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡
ችሎቱም የፖሊስን ጅምር የምርመራ መዝገብ አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ በጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ የሚደረግ ቀሪ ክርክርን ለማዳመጥ ተለዋጭ ቀጠሮ መያዝ አለበት በማለት ይህንንም መዝገብ ለሚያዚያ 7 ቀን 2011 ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


በስተመጨረሻ ችሎቱ ያስተናገደው ከመድሀኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ ጋር በተያያዘ የቀረበለትን መዝገብ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ መዝገብ ኦቶ ሀይለስላሴ ቢተው፣የማነብርሀን ታደሰ ፣ ሙከሚል አብደላ እና ወይዘሮ ሳፍያ ኑሩ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ቀርበዋል፡፡


ከ2000 እስከ 2006 ዓም የግዥ መመርያን በመጣስ የተለያዩ የህክምና አገልግሎት እቃዎች ግዥ  እና ሌሎችም ግዥዎችን በመፈፀም 9.5 ቢሊየን ዶላር ወጪ አለአግባብ እንዲወጣ አድርገዋል በዚህም በመንገስት ላይ ጉዳት አድረስሰዋል በማለት ፖሊስ ለችሎት አቅርቧል፡፡


እናም በስልጣን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል የጠረጠራቸው መሆኑን ጠቅሶ ቀሪ የምርመራ ስራዎችን እና የፎረንሲክ ምርመራዎችን ለማስደረገ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በዚህ መዝገብ ላይ ያሉት 3 ተጠርጣሪዎች በግላቸው ጠበቃ የማቆም አቅም እንዳላቸው ለችሎቱ የገለፁ ሲሆን ወ/ሮ ሳፊያ ግን በቂ ገንዘብ እንደሌላቸው በማስረዳት መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡


ችሎቱም ለወ/ሮ ሳፊያ የተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ካዘዘ በኋላ ቀሪዎቹ በግላቸው ማቆም የሚችሉበትን ጊዜ በማገናዘብ ለሚያዚያ 8 ቀጥሯል፡፡
በተያዘው ቀጠሮም በፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ ክርክር የሚደረግ ይሆናል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]