NBE Governor Yinager Dessie

ዋዜማ ራዲዮ- መንግስት ከወራት በፊት በወሰድኩት የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃ በተወሰነ መልኩ ተቆጣጥሬዋለሁ ያለው የአሜሪካ ዶላር የባንኮች ወይንም ይፋዊ የምንዛሬ ዋጋ እና የትይዩ (በተለምዶ የጥቁር ገበያ)  የምንዛሬ ዋጋ ልዩነት ተመልሶ ከፍተኛ ጭማሬ እያሳየ ነው።

ዋዜማ ራዲዮ ይህን ዘገባ እስካዘጋጀችበት ጊዜ ድረስ በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለው የምንዛሬ ዋጋ ልዩነት ወደ 17 ብር ተጠግቷል።ዕሮብ መጋቢት 28 ቀን 2014 አ.ም በነበረ ዋጋም አንድ የአሜሪካ ዶላር በባንክ 51 ብር ከ06 ሳንቲም የሚመነዘር ሲሆን በትይዩው ገበያ ደግሞ አንድን የአሜሪካ ዶላር ከ68 ብር ጀምሮ ይሸጠዋል።

በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሬውን (ዶላር) ለመግዛት በባንኮች እና ትይዩ ገበያ ያለው ልዩነት 18 ብር እንደሆነም ተረድተናል።

 መስከረም ወር በፊት ይሄው ልዩነት 20 ብር በመጠጋቱ ሳቢያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ብድር በሀገር አቀፍ ደረጃ ታግዶ እንዲቆይና ሌሎች ገንዘብ ነክ እርምጃዎችን በመወሰዱ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት ተቋማት የቤት ሽያጭ ለጊዜው እንዲቆም ማድረጋቸው በመጠኑም ቢሆን በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለውን የምንዛሬ ተመን ልዩነት አጥቦት ቆይቷል

ለበርካታ ጊዜያትም የአሜሪካ ዶላርና የብር የባንክ እና የትይዩ ገበያ የምንዛሬ ልዩነት ዘጠኝ እና አስር ብር ገደማ ቆሞ ነበር። ይሄም ልዩነት ሰፊ የሚባል ቢሆንም መንግስት ልቆጣጠረው የምችለው ልዩነት ነው በሚል ትቶት ነበር።

 ባለፈው ሳምንት ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻም የጥቁር ገበያው ዋጋ እስከ ሶስት ብር ጭማሬን አሳይቷል። ይህም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያለው የመንግስት መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት 1.6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ማዕከላዊ ባንኩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ የታየ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ለዋዜማ ራዲዮ ሰጥተዋል። የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችቱ ከአንድ  ወር ብዙም ፈቅ ለማይል ጊዜ የገቢ እቃዎች ነው የሚበቃው መባሉም የትይዩ ገበያውን ዋጋም ሳያንረው እንዳልቀረም ነው ባለሙያዎች የሚገምቱት።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ለሶስት ወራት የገቢ ምርቶችን ሊሸፍን የሚችል የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ የነበራት ቢሆንም አሁን ያለው ክምችትም እየተፈጠረ ላለው እጥረት ማሳያ ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል የበጀት አመቱ የስድስት ወራት የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ ወደ ሁለት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ቢሆንም የገቢ ምርቶች የጠየቀው የውጭ ምንዛሬ ግን ከእጥፍ በላይ መጨመሩ የፈጠረው እጥረትም የጥቁር ገበያው ዋጋ መልሶ እንዲጨምር እንዲያሰፋ ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።

በንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አንድ ግለሰብ ባለፉት ሳምንታት ኢትዮጵያ በተለያዩ የአሜሪካ ህጎች የማዕቀብ ሰለባ ትሆናለች የሚሉ መረጃዎች መናፈሳቸውም የጥቁር ገበያ ፍላጎትን ማናሩን እንዳስተዋሉ ገልጸውልናል። [ዋዜማ ራዲዮ]