ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በትግራይ ክልል መቀሌ በከፈተው አዲስ ጊዜያዊ የመስክ ቢሮ የኮንሱላር አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ዋዜማ ስምታለች።
ኤምባሲው አዲስ አገልገሎት የጀመረውና የመስክ ቢሮም የከፈተው በክልሉ የሚኖሩ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና አሜሪካውያንን ከነቤተሰቦቻቸው ለመድረስ ታስቦ መሆኑን የኤምባሲው ምንጮቻችን ለዋዜማ ተናግረዋል።
ኤምባሲው የመስክ ቢሮውን እንዲከፍት ያስገደደው በትግራይና በማዕከላዊ መንግስት መካከል የትራንስፖርትም ሆነ የመገናኛ አውታር በመቋረጡ ከአዲስ አበባ ሆኖ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ነው።
ባለፈው ዓመት በትግራይ ጦርነቱ ተፋፍሞ በነበረበት ወቅት የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹን ከክልሉ ለማስወጣት ጥያቄ ቢያቀርብም ከሁለቱም ተፋላሚዎ ይሁንታ ባለማግኘቱ በርካታ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሉበት እንዲቆዩ ተገደዋል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፈና የተሰወሩ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ግለሰቦች ከመመዝገብ አንስቶ ማንነታቸውን የሚገልፅ ስነድ ለጠፋባቸው ዜጎች ጊዜያዊ የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ መኖሪያ ሀገራቸው አሜሪካ እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሞከረ ነው።
በተለይም ለቅርብ ቤተሰቦቻቸው የጉዞ ሂደት ለማመቻቸት የሚፈልጉ እና አዲስ አበባ ወደሚገኘው ኤምባሲ ቀርቦ ሂደቱን ለማስፈፀም ለተቸገሩ የክልሉ ነዋሪዎችን አገልግሎት ለመስጠት እንደታሰበም ተነግሯል።
አንዳንድ ባለጉዳዮች ጊዜያዊ ሰነድ ካገኙ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከነቤተሰቦቻቸው አልያም በተናጠል ከሀገር መውጣት የሚያስችላቸው የተሟላ ሰነድ ያገኛሉ ተብሏል።
እነዚህን ዜጎችና ቤተሰቦቻቸውን በልዩ በረራ ከትግራይ በቀጥታ ወደ ውጪ ሀገር ለመውሰድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት መኖሩን የሚያረጋግጥ መረጃ ዋዜማ አላገኘችም። [ዋዜማ ራዲዮ]