Andargachew Tsige
Andargachew Tsige

(ዋዜማ)-የኢትዮዽያ መንግስት የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ስዎች በተለያዩ ምክንያቶች በቁጥጥር ስር በማዋል ታሳሪዎቹ የሚገባቸውን የኮንሱላር አገልግሎት እንዳያገኙ ሲከለክል ይታያል። አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ ሌሎች ታሳሪዎችን ለመደበቅና ዜግነት ከሰጣቸው ሀገር የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ለማዋደቅ የሚጠቀመው ስበብ እኤአ በ1963 የተደነገገውን የቪየናውን የቆንስላ ግንኙነቶች ድንጋጌ ነው። ኢትዮዽያ የዚህ ስምምነት ፈራሚ አይደለችም። ለምን? ታስቦበት ወይስ በአጋጣሚ? ተከተዩ ዘገባ ይህን ይመለከታል –በድምፅ አልያም በንባብ ዝለቁት

ኢትዮጵያ የቆንስላ ግንኙነቶችን የሚመለከተውንና በእንግሊዘኛው አጠራር Vienna Convention on Consular Relations ተብሎ የሚታወቀውን ዓለም ዓቀፉን ድንጋጌ ካለማፅደቋ ጋር ተያይዞ ብዙ አወዛጋቢ ነገሮች ይነሳሉ።

በኢትዮጵያ ከሽብርተኝነት፣ ብሄራዊ ደህንነት፣ ከሰራተኛ ቅጥርና አያያዝ እንዲሁም ከመሬትና ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ የተለያዩ የውጭ አገር ዜጎች ከመንግስትና ግለሰቦች ጋር ክርክር ውስጥ ሲገቡና ጉዳያቸውም በፍርድ ቤት ሲታይችግሮች ሲፈጠሩ ይታያል። የተጠርጣሪ የውጭ አገር ዜጎች የቆንስላ መብት ጥያቄዎች በሚነሱበትና ኤምባሲዎችና መንግስታት ተጠርጣሪ ወይም ፍርደኛ ዜጎቻቸው በዓለም አቀፍ ህግጋትና መርሆዎች መሰረት ተገቢው ሰብአዊ መብት እንዲከበርላቸው፣ በተደጋጋሚም የመጎብኘት መብት እንዲኖራቸውና የተፋጠነ ፍትህም እንዲያገኙ መጎትጎት ይጀምራሉ፡፡ ሀገሪቱ የቪየናውን ድንጋጌ አለማፅደቋ የሚያስከትለው ዲፕሎማሲያዊ አንድምታና የሀገሪቱ ፍትህ ስርአትድክመት ቁልጭ ብሎ የሚታየውም ያኔ ነው።

እዚህ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የቪየናውን ዓለም ኣቀፍ የቆንስላ ኮንቬንሽን ያልፈረመው ለምን ይሆን? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ምንም እንኳ አስተማማኝ ምላሽ መስጠት ቢያስቸግርም በብሄራዊ የደህንነት ጉዳዮች ምክንያት መንግስት ተጠርጣሪዎችን ላልተወሰነ ጊዜ ለፍርድ ሳያቀርብ በቁጥጥር ስር አውሎ ለማቆየት እንዲያመቸው ነው? ወይስ የፍትህ ስርዓቱ ደካማነት ዓለም ኣቀፍ መርሆዎችን ማሟላት የሚችሉበት ደረጃ እስኪደርሱ ጊዜ እየገዛ ይሆን?የሚሉ መላ ምቶች መሰንዘራቸው አይቀርም፡፡

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት በርካታ ዓመታት በሽብርተኝነትና በሌሎች ወንጀሎች የጠረጠራቸውን የውጭ አገር ዜጎች በተለያየ ጊዜ ለእስር ዳርጓል፡፡ ምንም እንኳ ቁጥራቸውን በትክክል መናገር ቢያስቸግርምእስካሁንም ለፍርድ ሳይቀርቡ ለረዥም ጊዚያት በቁጥጥር ስር ያሉ ውጭ ዜግነት ያላቸው እስረኞች አሉ፡፡ በእርግጥ የሀገሪቱ ህገመንግስት ሰብዓዊ መብት አንቀፆች ማንኛውም ታሳሪ በፍጥነት ለፍርድ የመቅረብ፣ በጠበቃ የመወከል፣በቤተሰብም ሆነ ሌሎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የመጎብኘትና የተፋጠነ ፍትህን  ማግኘትን  የመሳሰሉ ሰብአዊ መብቶች እንዳሉት ቢደነግጉም መብቶቹ ግን በአግባቡ ተፈፃሚ እንደማይኾኑ ይታያል።

የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌ አለመፈረሙ በተለያዩ ምክንያቶች የሚያስራቸውን የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ላልተወሰነ ጊዜ ፍርድ ቤት ሳያቀርብ ለማቆየት እንዳገዘው መታዘብ ይቻላል፡፡ ከእነዚህም መካከልየኖርዌይና የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ከኦጋዴን ነፃ አውጭና ከጋምቤላ ነፃ አውጭ ድርጅቶች እንዲሁም ከሰበአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ምክንያት ለእስር የተዳረጉና ቅጣትም የተወሰነባቸው ትውልደ-ኢትዮጵያዊያንይገኙበታል፡፡ ከጥቂት ዓመታትም  በፊት ሁለት ስዊድናዊያን ጋዜጠኞች ከኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ጋር በመተባበር ያለ ህጋዊ ፍቃድ በህገወጥ መንገድ ወደ ኦጋዴን ገብተዋል በሚል ወንጀል ተከሰው ለበርካታ ወራት በእስር ከከረሙበኋል የስዊድን መንግስት ባደረገው ብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መፈታታቸው ይታወሳል፡፡

የአኝዋክ ተወላጅ የሆኑት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ኦኬሎ አኳይ ደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ ላይ እኤአ በ2014 በደቡብ ሱዳን የፀጥታ ሃይሎች ከታሰሩ ጀምሮ በፀረ-ሽብር አዋጁ መሰረት መንግስትን በኃይል የመገልበጥናየጋምቤላን ክልል በኅይል የመገንጠል ሴራ ክሶች ተመስርተውባቸው  ወህኒ ይገኛሉ፡፡ እስካሁንም የፍርድ ውሳኔ ሳያገኙ በእስር በመማቀቅ ላይ ናቸው፡፡ በስደት ከቆዩ በኋላ የኖርዌይ ዜግነት የያዙት የአቶ ኦኬሎ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ እንደ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሁሉ በኖርዌይ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በዓለም አቀፍ የቆንስላ ግንኙነቶች ላይ የተደነገጉ የታሳሪ የውጭ ዜጎች መብቶች ጉዳይ  እንዲነሱ ማድረጉ አልቀረም፡፡

 የኖርዌይ መንግስት በአቶ ኦኬሎ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ግፊቶች ቢደረጉበትም ልክ እንደ እንግሊዝ መንግስት ሁሉ በሌላ አገር የፍትህ ሂደት ውስጥ ጣልቃ እንደማይገባ ግልፅ አድርጓል፡፡ ከኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተገኙመረጃዎች እንደሚያሳዩት የኖርዌይ ኢምባሲ ባለፈው ዓመት አቶ ኦኬሎን እንዳይጎበኝ በተደጋጋሚ ዕገዳ ተጥሎበታል፡፡ የኖርዌይ  መንግስት በአቶ ኦኬሎ እስር የመጀመሪያ ሳምንታት ተፈቅዶለት የነበረውን የመጎብኘት መብትም ባልታወቀምክንያት ተመልሶ እንደተነጠቀ ይገልፃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ታሳሪው በፖሊስ ምርመራ ወቅት ኢሰብዓዊ ግርፋት ተፈፅሞባቸው ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳለው ሲገልፅ ይደመጣል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት አቶ አንዳርጋቸውን በእንግሊዝ ኤምባሲ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለስልጣናት በቶሎ እንዲጎበኙ ያላደረገውና ጥያቄው ከቀረበለትም በኋላ ነገሩን ሲያጓትት የታየው ይህንኑ ዓለም አቀፍ ስምምነት ባለመፈረሙ አጣዳፊአስገዳጅ ሁኔታ እንደሌለበት በማመን እንደሆነ ይገመታል፡፡ ቆንስላዎች በተወከሉበት ሀገር ያሉ ዜጎቻቸውንና ድርጅቶቻቸን ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የየሀገሩ ህግ በሚፈቅደው መሰረት በፍርድ ቤት ለተከሰሱ ወይም በሌሎችመንግስት ተቋማት ጉዳይ ላለባቸው ዜጎቻቸው የህግ ጥብቅና የማቆም መብት አላቸው፡፡ በቪየናው ድንጋጌ መሰረት ስምምነቱን ያፀደቁ ሀገሮች የውጭ አገር ዜጎችን በተለያዩ ምክንያቶች በሚያስሩ ጊዜ ወዲያውኑ ለሚመለከተው ቆንስላእንዲያሳውቁ ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡

ባለፈው ጥር የስራ ዘመናቸውን ጨርሰው የተሰናበቱት የእንግሊዙ አምባሳደር እና የእንግሊዝ የህግ መወሰኛው  ምክር ቤት የተወሰኑ አባላት አቶ አንዳርጋቸውን ለመጎብኘት የተፈቀደላቸው አቶ አንዳርጋቸው  ከተያዙ ከዓመት በኋላ ነበር፡፡አምባሳደሩ በስራ ዘመናቸው መጨረሻ ላይ ለአንድ የአገር ውስጥ መፅሄት በሰጡት ቃለ ምልልስ በአስራ ስምንት ወራት ውስጥ በመንግስት ፍቃድ ስድስት ጊዜ ብቻ ታሳሪውን እንደጎበኟቸው ቢናገሩም ስለ ጤንነት ሁኔታቸው ግን ምንምፍንጭ ሰጥተው አያውቁም፡፡

የኢትዮጵያን መንግስት በሃይል ለመጣል በኤርትራ የሚንቀሳቀሰውና በመንግስት በሽብርተኛነት የተፈረጀው “ግንቦት ሰባት” ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው እኤአ በ2014 በየመን ፀጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር እንደዋሉለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው የተሰጡት ወዲያውኑ ነበር፡፡ የዴቪድ ካሚሮን መንግስት በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና እንግሊዛዊያን የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ በአግባቡ አልተከታተለም የሚል ጠንካራ ወቀሳና ግፊትሲደረግበት ቆይቷል፡፡ የታሳሪው ቤተሰቦችም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተፅዕኖ በማድረግ አቶ አንዳርጋቸውን ከኢሰብዓዊ አያያዝ እንዲታደጋቸው ተከታታይ አቤቱታዎች አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዜግነት ሕግ ድርብ ዜግነት መያዝን አይፈቅድም፡፡ በመሆኑም አቶ አንዳርጋቸውም ሆኑ  አቶ ኦኬሎ በታሰሩበት ጊዜ የውጭ ዜግነት የነበራቸው በመሆኑ እንደ ውጭ አገር ዜጎች መታየታቸው የግድ ነው፡፡ ያም ሆኖ ኢትዮጵያየቪየናውን ድንጋጌ ባለመፈረሟ ታሳሪዎቹ መብቶቻቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡ ተሰናባቹ የአንግሊዝ አምባሳደርም በሰጡት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የቪየና ድንጋጌ አለመፈረሟ ችግር ፈጣሪ እንደሆነበተዘዋዋሪም ቢሆን ጠቁመው ነበር።

ሌላው የኢትዮጵያ መንግስት የቪየናውን ድንጋጌ ላለመፈረሙ እንደ ታሳቢ ምክንያት ሊቀርብ የሚችለው የፍትህ ስርዓቱ ከፍተኛ የአቅም ማነስ ችግር ያለበት መሆኑ ነው፡፡ በተለይ የውጭ ዜጎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሲያጋጥሙት ደግሞየፍርድ ሂደቱ የተጓተተና ደረጃውን ያልጠበቀ መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ተሰናባቹ የእንግሊዝ አምባሳደር የፍትህ ስርዓቱን ተቋማዊ ድክመት በተደጋጋሚ መታዘባቸውን ለሀገር ውስጥ ፕሬስ በሰጡት ቃለ ምልልስ አልሸሸጉም፡፡ የአገሪቱፍርድ ቤቶች የዳኞች ቶሎ ቶሎ መቀያየርና  ተሟልቶ አለመገኘት፥  በአቃቤ ሕግም በኩል ማስረጃ የማሰባሰብ ድክመትና አፋጣኝ ውሳኔ ባለመስጠትና በመሳሰሉ ውስብስብ ችግሮች እንደተተበተቡ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡  ኢትዮጵያየቪየናውን የቆንስላ ግንኙነቶች ድንጋጌ አፅድቃ ቢሆን ኖሮ የፍትህ ስርዓቷና ፍርድ ቤቶቿ በድንጋጌው የሚጠበቅባቸውን ዓለም ኣቀፍ ግዴታዎቸ ማሟላት ይችሉ ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ አጠራጣሪ የሚሆነውም ለዚሁ ነው፡፡

 

እኤአ በ1963 የተደነገገውን የቪየናውን የቆንስላ ግንኙነቶች ድንጋጌ 177 ሀገሮች አፅድቀው የህጋቸው አካል አድርገውታል፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችም ከደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ በስተቀር ኤርትራና ሱማሊያን ጨምሮ ሁሉም ሀገሮችአፅድቀውታል፡፡ ግብፅም እንዲሁ ድንጋጌውን መፈረም ብቻ ሳይሆን አፅድቃ ተግበራዊ አድርገዋለች፡፡ እንደሚታወቀው የቪየናውን ድንጋጌ የሚያፀድቁ ሀገሮች የማይፈልጓቸውን የተወሰኑ አንቀፆች ለይተው ያለመቀበል ወይምበእንግሊዝኛው የ “reservation” መብት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከነአካቴው ድንጋጌውን መፈረምም አለመፈለጓ አነጋጋሪ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በህግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች ጠበቃ የማግኘትና ለረዥም ጊዜ በተናጠል ከመታሰርየመጠበቅ የመሳሰሉ መብቶችን ያካተተውን ዓለም አቀፉን የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ድንጋጌ ና ተዛማጅ ዓለም አቀፍ ሰነዶች አፅድቃ የህጓ አካል ካደረገቻቸው በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

 

እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የልማት ዕርዳታ ከሚለግሱት ምዕራባዊያን ሀገሮች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ላይ የምትገኝ ናት፡፡ ሁለቱ መንግስታት በዓለም ዓቀፉ ፀረ-ሽብር ጦርነት ዙሪያም ትብብር ያደርጋሉ፡፡ የእንግሊዝ መንግስትበአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እንዲሰፍን ስለሚፈልግና ለቀጠናው መረጋጋትም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርና ግዙፍ ጦር ሰራዊት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና እንደምትጫወት ስለሚያምን የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ግንባር ቀደምአጋር ሆኖ መቆየት እንደሚፈልግ በሰፊው ይታመናል፡፡

 

ምንም እንኳ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አያያዝ ጉዳይ ከዲፕሎማቶች ባሻገር በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃም ካሁን በፊትም ውይይቶች እንደተደረጉበት ቢታምንም ከውስጥ ለውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ልምምጥ አልፎ ለሁለቱ ሀገሮችግንኙነት መሻከር ምክንያት የሚሆን ልዩነት ግን በይፋ ታይቶ አያውቅም፡፡ ሁለቱ መንግስታት ካላቸው ጥብቅ ግንኙነት አንፃር ወደፊትም ይታያል ተብሎ እንደማይጠበቅ በርካታ ታዛቢዎች ይስማሙበታል፡፡