ዋዜማ ራዲዮ– የትግራይ ክልል መንግስት የደርግ ስርዓት ወድቆ ህወሀት መር የሆነው የኢሕአዴግ አስተዳደር ስልጣን የያዘበትን የግንቦት ሀያ በዓል በክልሉ በዘላቂነት ለማክበር የረጅም ጊዜ እቅድ አውጥቷል።


ማዕከላዊው መንግስትና የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ግንቦት ሀያን ለማክበር በሚያንገራግሩበት በዚህ ወቅት የትግራይ ክልል መንግስት በዓሉን በደማቅ ሁኔታ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች በየዓመቱ ያከብራል። የዘንድሮው የግንቦይ ሀያ በዓል በአክሱም ከተማ የሚከበር ሲሆን በመጪው አመት ደግሞ በሽረ-እንደስላሴ ከተማ ለማክበር ታቅዷል።


በአክሱም ለሚደረገው ክብረ በዓል በበጎ ፈቃደኝነት ከተሰባሰቡ የክልሉ ተወላጆች፣ ከመንግስታዊ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፍ የተሰባሰበ ሲሆን የተለያዩ ፖለቲካዊ መልዕክቶችን ያዘሉ መፈክሮች፣ ቲሸርቶችና በራሪ ወረቁቶች በስፋይ እየተሰራጩ መሆኑን የዋዜማ ሪፖርተር ተመልክቷል።


በስፋት ከሚታዩ መልዕክቶች አንዱ “አነ ጌታቸው አሰፋ እየ” (እኔ ጌታቸው አሰፋ ነኝ) የሚልና ለቀድሞው የደህንነት ሀላፊ አጋርነትን የሚያሳይ መፈክር በስፋት ተሰራጭቷል።

ኑሮ እየከበደ ነው


ከፖለቲካዊ መጋጋሉ ባሻገር በትግራይ አሁንም የኑሮ ውድነት እየተባባሰ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። ሪፖርተራችን ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ከሁለት ወር ወዲህ በምግብ እህሎችና በአንዳንድ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ከሚጠበቀው በላይ ዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ለምሳሌ 2,700 ብር ሲሸጥ የነበረ ጤፍ አሁን 3,300 ብር ደርሷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጤፍ ከአዲስ አበባ -ሞጆ- በአፋር በኩል ዞሮ ስለሚመጣ ነው ተብሏል፡፡ እንደ በርበሬ፣ በቆሎ፣ አተር የመሳሰሉት ደግሞ ከ40 በመቶ እስከ 50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡


በትግራይ ክልል መቀሌ፣ አዲግራት፣ ሽረ፡እንደስላለሴ፣ አክሱም የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ቀደም ሲል በትግራይና በአማራ ክልል የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ሁለቱን ክልሎች የሚያገናኟቸው መንገዶች ሰላም አለመሆን እንደ ምክንያትነት ይጠቅሳል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎችም አልፎ አልፎ መንገድ ላይ ዝርፊ ስለሚገጥማቸው ከጎንደርና ከጎጃም ሲመጡ የነበሩ የምግብ እህሎች አሁን የሉም፡፡

ነጋዴዎች እንደሚሉት 14 ሺሕ ብር የነበረው የመኪና ኪራይ አሁን 26 ሺሕ ይጠየቃሉ፡፡ በጨለማና በድብቅ የሚገቡት የምግብ እህሎችም ዋጋቸው ከፍተኛ ነው፡፡
በፖለቲከኞች አለመግባባት ሁለቱ ሕዝቦች መቸገር የለባቸውም የሚሉት ነጋዴዎች ችግሩ ያለው ከላይ ከፖለቲከኞች ነው ይላሉ፡፡ ነዋሪዎች በበኩላቸው መንገዱ ሰላም እንዲሆን የሁለቱ ክልል ፖለቲከኞች ቁጭ ብለው መነጋገር እንዳለባቸው ይጠይ
ቃሉ።