Tigray regional President Debretsion GMechael- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካዔል ከማዕከላዊው መንግስት ጋር ችግሮችን በዲፕሎማሲ ለመፍታት ሲደረግ የነበረው ጥረት “ባለመሳካቱና የሰላም መንገድ በመዘጋቱ የትግራይን ሕዝብ ነፃነት ለማረጋገጥ” የክልሉ ህዝብ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቀረቡ።

ደብረፅዮን በመቀሌ ሌሎች የሕወሓት አመራሮች ደግሞ በተለያዩ የትግራይ ዞኖች ከነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የትግራይ ህዝብ አሁን ያለበት የከፋ ስቃይ እንዲቀለበስና የትግራይ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዲረጋገጥ ለማድረግ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል ብለዋል።

“ሁሉም የፖለቲካ ችግር በሰላምና በዲፕሎማሲ እንደማይፈታ ብናውቅም አሁን የገባንበት ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድመን እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተናል” ብለዋል ደብረፅዮን በመቀሌ ከነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ።

በአለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸማጋይነት ጊዚያዊ ስምምነት ተደርጎ ወደ ክልሉ እህል መድሀኒትና ሌሎች ድጋፎች እንዲገቡ ጥረት ብናደርግም እስከ አሁን ድረስ የተገኘው ድጋፍ ችግሩን ለማቃለል በቂ አይደለም ብለዋል።


መላክ ያለበትን መልዕክት ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ባለን የመገናኛ መንገድ አድርሰናል ያሉት ደብረፅዮን የሚመለከታቸው ያሏቸውን አካላት አልዘረዘሩም።


መንግስት የተኩስ አቁም በሚል ሽፋን የመሳሪያና የሰራዊት ማሰባሰብ ስራ ላይ ነው ሲሉ የከሰሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የትግራይ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚረጋገጠው የኀይል የበላይነትን በመያዝ ብቻ መሆኑን ለተሰብሳቢዎች አስረድተዋል።

ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር(ሞንጀሪኖ)፣ አለም ገብረሐዋድና ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ነዋሪዎችን ያወያዩ ሲሆን ሕዝቡ ለመጨረሻው ምዕራፍ ትግል እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርስ ሁኔታዎችን ባመቻችም ሕወሓት ራሱ ዕርዳታ በማስተጓጎልና ተጎራባች ክልሎችን በመውረር እንቅፋት መፍጠሩን ይናገራል። የትግራይ አማፅያን በቅርቡ ይዘውት ከነበረው የአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ለቀው መውጣታቸውን አስታውቀዋል።


ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት የምዕራብ ዕዝ የመከላከያ ሰራዊትን በቦታው ተገኝተው ያበረታቱ ሲሆን ወታደራዊ ብቃቱን የሚያሳይ ትርዒትም ተመልክተዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]