Photo Credit ENA

ዋዜማ ራዲዮ- በርካታ ነባር ሰራተኞቹን በአዳዲስ ባንኮች የተነጠቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጋጋለውን ፉክክር ለመወጣት ለሰራተኞቹ አዲስ የማትጊያ ብድር  መርሀገብር አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። 

የባንክ ዘርፍ ውድድር የተጋረጠበት መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሰሞኑ በባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቢ ሳኖ የተፈረመበትን አዲስ የሰራተኞች የብድር አጠቃቀምን  የሚወስን አሰራርን ተግባራዊ እንዲሆን አድርጓል።

ዋዜማ ራዲዮ የተመለከተችው የአዲሱ የማትጊያ ብድር መርሀገብር ሰነድ ባንኩ ከአስር አመት በላይ ልምድ ያላቸው ሰራተኞቹ አንዴ ለቤትም መግዣ የተበደሩትን ብድር እየመለሱ ሌላ ብድር እንዲወስዱ እንደተፈቀደ ያሳያል።

ከዚህ ቀደም በነበረ አሰራር አንድ የባንኩ ሰራተኛ ለቤት ብድር መውሰድ የሚችለው ሁለቴ ብቻ ሲሆን ሁለተኛውን የቤት ብድር መውሰድ የሚችለው የመጀመርያውን የከፈለ እንደሆነ ብቻ ነው። መኪና ለመግዛት ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብድር ይፈቀድ ነበር። ቀጥሎም እንዲቆም ተደርጎ ነበር።

ከአስር አመት በላይ ላገለገሉት ሰራተኞቹ ከፈቀደው ያልተገደበ ብድር በተጨማሪ አንድ ሰራተኛ ብድር ወስዶ ሳለ ብድሩን ባይመልስም በግማሽ ደሞዙ ተሰልቶ ተጨማሪ ብድር መውሰድ እንደሚችል ከተረጋገጠ ብድር እንዲፈቀድለት ተደርጓል። መኪና ለመግዛት የሚፈልጉ ሰራተኞቹ ከዚህ ቀደም ይጠበቅባቸው የነበረው የ15 በመቶ የመኪናው ዋጋ መዋጮ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲልም ተወስኗል። ሰራተኞች በቆጣቢ ወለድ ማለትም በ7 በመቶ የስድስት ወር ደሞዛቸውን ብድር እንዲያገኙም ተፈቅዷል።

ይህ የባንኩ እርምጃ  በቅርቡ በተደረገው የደሞዝ እርከን  ጭማሬ ያኮረፉ ሰራተኞቹን በመጠኑም ሊያስደስት ይችላል ተብሏል።ንግድ ባንክ ለሰራተኞቹ ያደረገው የአራት እርከን የደሞዝ ጭማሬ ብዙዎቹን ያላስደሰተ እንደነበር ተነስቷል። በርካታ ባንኮች ከ25 በመቶ እና ከዛ በላይ የደሞዝ ጭማሬን ማድረጋቸው ሲታይም የመንግስታዊው ባንክ ከ ዝቅተኛ ነው ሊባል የሚችል ነው። ስራ በቅጡ ሳይጀምሩ የደሞዝ ማስተካከያ ያደረጉ ባንኮች ነበሩ። 

የበጀት አመቱን በከፍተኛ ትርፍ መጠናቀቅን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሰራተኞቹ የከፈለው የሶስት ወር ደሞዝ ጉርሻ ከባንክ ኢንዱስትሪው ውድድር ብዙም ዝቅ አላደረገውም። በበጀት አመቱ መጠናቀቂያ አዋሽ ባንክ አስከ ስድስት ወር የሚደርስ የደሞዝ ጉርሻ ለሰራተኞቹ የሰጠ ሲሆን ፣ዳሽን እና ዘመን ባንክ በአፈጻጸም ላይ የተመሰረተ የአምስት ወር ደሞዝ ጉርሻ ለሰራተኞቻቸው ሰጥተዋል። ህብረት እና አቢሲኒያ ባንኮች ደግሞ እያንዳንዳቸው የሁለት ወር ከግማሽ ደሞዝን ነው ጉርሻ የከፈሉት። ከዚህ አንጻር ሲታይ ንግድ ባንክ መሀል ላይ የሚቀመጥ ነው።

ሆኖም በብድር ረገድ የጀመረው አሰራር በሰራተኛ አያያዝ ረገድ የተሻለ እንዲሆን ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰኔ ወር ላይ በተጠናቀቀው የበጀት አመት የተቀማጭ መጠኑ ከ890 ቢሊየን ብር ያለፈ ሲሆን ትርፉም ከ27 ቢሊየን ብር በላይ እንደሆነ መገለጹ ይታወሳል።

ባንኩ በተለይ አቶ ባጫ ጊና በፕሬዝዳንትነት ይመሩት በነበረ ጊዜ ገብቶበት በነበረ የገንዘብ ቀውስ ሳቢያ ለሰራተኞቹ  ሁለት ጊዜ ይሰጥ የነበረው የቤት ብድር አንዴ እንዲሆን ቀጥሎም እንዲቆም ተደርጎ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ባጫ ጊና ባንኩን ይመሩ በነበረበት በ2012  የበጀት አመት የመጀመርያ ስድስት ወራት ንግድ ባንክ ያሳየው የስራ አፈጻጸም በባንኩ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ዝቅተኛ ነበር። ባንኩ በዚሁ ጊዜ 38.3 ቢሊየን ብር ቁጠባን ከደንበኞቹ ለማሰባሰብ አቅዶ ያሰባሰበው ቁጠባ 24.6 ቢሊየን ብር ነው። ይህም የቁጠባ አፈጻጸም ቀድሞ ከነበሩት አመታት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተገምግሟል። ነገር ግን ባንኩ በተመሳሳይ ጊዜ ከሰበሰበው ቁጠባ በ15 ቢሊየን ብር ብልጫ ያለው 40 ቢሊየን ብርን ብድር በመስጠቱ ያልተመጣጠነ ወጪና ገቢው የገንዘብ እጥረትን ፈጥሮበት ለሰራተኞቹ የሚሰጠውን ብድር እስከማቆም ደርሶ ነበር። [ዋዜማ ራዲዮ]