Jafar Book Store

ኢትዮጵያውያን ያነባሉ? የንባብ ባሕል ኢትዮጵያ ውስጥ አለ? የሚሉ ጥያቄዎች ተደጋግመው ሲነሱ ይሰማል። ብዙውን ጊዜም ምላሹ በጥናት ላይ የተደገፈ እንኩዋን ባይኾን አሉታዊ ነው። የኛ ሰው አያነብም የሚለው መደምደሚያ በብዛት ሲነገር ቢሰማም ልክ አይደለም ብሎ ለመከራከር የሚያበቃ አሳማኝ መረጃ ማግኘት ይከብዳል። አድምጡትማ!

ሌላው ቢቀር ማንበብ እና መጻፍ የማይችለው አብዛኛው ሕዝባችን፣ ቤተ መጽሐፍት የሌላቸው ትምህርት ቤቶቻችን ወይም መጽሐፍ አልባ ቤተ መጽሐፍት ባሉበት አገር ይህን ድምዳሜ ለመቃወም የሚያበቃ ምላሽ ማግኘት ይከብዳል። ያም ኾኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የንባብ ፍላጎት መኖሩን የሚያሳዩ ብዙ ነገሮች ሲከሰቱ ይታያል። ከነዚህም ነገሮች አንዱ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉት የንባብ ክበቦች ናቸው።
ለገሃር አካባቢ ከሚገኘው “ጃፈር መጽሐፍት መደብር” ጎራ ብሎ ያገኘኹት ወጣት ይህን የመሰለውን በደምሳሳው ትውልዱን የሚወቅስ አባባል አይዋጥለትም፡፡ ይህን የመሰለውን ሐሳብ ከብዙዎች ሲሰነዘር ቢሰማውም አንባቢ የለም የሚለውን ድምዳሜያቸውን አይቀበለውም፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዳ የሚያውቃቸውን ብዙ ወጣቶች እንደምሳሌ እየጠቀሰ ነው፡፡ በተለይ አሁን አሁን ከገበያ ጠፍተው የነበሩ ቀደምት መጽሐፍት በድጋሚ መታተማቸው እና ብዙ ታሪካዊ መጽሐፍትም መታተም መጀመራቸው ብዙ ሰዎች እንዲያነቡ እንደሚያበረታታ ያምናል፡፡ ብዙ ዋጋ ሲጠየቅባቸው የነበሩ መጽሐፍት አሁን በገበያ ላይ በመጠነኛ ዋጋ መገኘታቸውም ላንብብ ላለ ሰው አስደሳች መኾኑንም ታዝቧል፡፡ በተለያዩ ሆቴሎች በሚታደሙ የመጽሐፍት ክበቦችም በመገኘት ያየውም ስሜት ትልቅ የንባብ ፍላጎት እና ብዙ አንባቢዎች እየፈለቁ መኾኑን የሚያሳይ ምልክት እንደኾነም ያምናል፡፡
በርግጥም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ያሉ የውይይት ክበቦች ቀና ቀና ማለት መጀመራቸው ይታያል፡፡ ልቦለዶች እና የግጥም ስራዎች በመጽሐፍት መደብሮች ውስጥ ቢኖሩም በታሪክ እና በግለሰብ የሕይወት ታሪክ ላይ የተመሰረቱ መጽሐፍት ፈላጊያቸው ብዙ ነው። በተለይ በ 66ቱ አብዮት ውስጥ ተሳታፊ በነበሩ ጸሐፍት የተደረሱት መጽሐፍት ብዙ አንባቢ አላቸው። የብዙ መጽሐፍት ክለቦችም ምርጫ ከዚህ ብዙ የራቀ አይደለም። ለውይይት የሚቀርቡት መጽሐፍት ይህንኑ የመሰሉ ናቸው። እንደምሳሌ ያህልም በሕይወት ተፈራ የተጻፈውን “Tower in the sky” ፣በዳዊት ካህሳይ የተፃፈው “የአሲምባ ፍቅር” እና በቆንጂት የተፃፈው “ምርኮኛ” መጽሐፍት ላይ በተለያዩ የመጽሐፍት ክለቦች ውስጥ ውይይቶች ከተደረገባቸው መጽሐፍት መካከል የገኛሉ፡፡ ብዙ አንባብያን መጽሐፍቱን ከማንበባቸው በተጨማሪ ይህን በመሰሉ ውይይቶች ላይ መገኘታቸውን ሲያጋጥምም ከባለታሪኮቹ አፍ በቀጥታ የሚሰሙበትን እድል ብዙ እንደሚያተርፉበት ይናገራሉ፡፡
በቅርብ ጊዜ በተለይ በአዲስ አበባ የመጽሐፍት ክበቦች በብዛት መጀመራቸው እየታየ ነው፡፡ የነዚህ የመጽሐፍት ክበቦች መጀመር ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ለአንባብያን በሚያነቡት ጉዳይ ላይ በጋራ የሚወያዩበትን እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ ዘወትር የሚወቀሰውን የዚህን ትውልድ የንባብ ባህል ለማበረታታት እና ንባብን ለማሳደግ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው፡፡ በትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ ከሚደረጉት የመጽሐፍት ውይይቶች በተጨማሪም በቁጥር አነስ ብለው ተሰብስበው በጉዋደኛማቾች መካከል የሚመሰረቱ ትናንሽ የመጽሐፍት ክለቦችም እያቆጠቆጡ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚኾነው የ “እናንብብ መጽሐፍት ክበብ” ጅማሬ ነው፡፡ በአንድ መስሪያቤት አብረው በሚሰሩ ጓደኞች የተመሰረተው “እናንብብ የመጽሐፍት ክበብ” ጅምሩ የቡድኑ አባላት ሊያነቧቸው የሚፈልጓቸውን የመጽሐፍት ብዛትና የመግዛት አቅማቸውን ለማጣጣም የዘየዱት ዘዴ ነው፡፡ የመጽሐፍ ወጪያቸውን ለመጋራት በየወሩ ከደሞዛቸው 50 ብር በማዋጣት የሚፈልጓቸውን መጽሐፍት በጋራ መግዛት እንደጀመሩ የሚናገሩት የእናንብብ አባላት በዚህች ትንሽ ጅማሬ ብዙ ለማንበብ እድል እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ የቡድኑ አባላት አምስት ናቸው፡፡ አባላቱ ላለፉት ሶስት አመታት የቆየው የዚህ ክበብ መኖር የንባብ ፍላጎታቸውን ለማርካት አስተዋፅኦ እንዳደረገላቸው ይናገራሉ፡፡ የእናንብብ አባላት በየወሩ በጋራ ዘጠኝ የሚኾኑ መጽሐፍት ከገዙ በኋላ የተገዙትን መጽሐፍት ሁሉም አባላት በዙር እንዲያነቡ በየተራ እድል ይደርሳቸዋል፡፡ የቡድኑ አባላት ሊያነቡት የሚፈልጉት የመጽሐፍ አይነት ተመሳሳይ መኾኑ ያለችግር በጋራ የሚያነቡት መጽሐፍ ለማግኘት የጠቀማቸው ይመስላል፡፡ ባብዛኛው በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ላይ የሚያተኩሩ መጽሐፍትን እና ግለታሪኮችን ይመርጣሉ፡፡
እንዲህ በጋራ መጽሐፍትን እየገዙ ማንበብ የእናንብብ ክበብ የዘየደው ዘዴ ብቻ አይመስልም። ድሮም መጽሐፍትን እየተዋዋሱ ማንበብ የለመዱ ብዙ ጉዋደኛማቾች ይህችን ዘዴ እንደሚጠቀሙ ይታያል። በብሄራዊ ቲያትር አካባቢ ባሉ ካፌዎች ውስጥ ደምበኛ የሚያፈላልግ አንድ መጽሐፍ አዝዋሪም ይህን መሰሉ መጽሐፍትን በጋራ እየገዙ የማንበብ ዘዴ አዲስ ነገር እንዳልኾነ ይናገራል፡፡ በተለይ የአንዳንድ መጽሐፍት ዋጋ ከፍ ያለ በሚኾንበት ጊዜ ብዙ ሰዎች በጋራ በመግዛት ለማንበብ የሚያደርጉትን ጥረት ይኧው መጽሐፍ አዟሪ መታዘቡን ይናገራል፡፡
ንባብን የመሰለ ባሕል በአንድ ጀምበር የሚፈጠር ጉዳይ አለመኾኑ ግልጽ ቢኾንም እንዲህ ያሉ የመጽሐፍ ንባብ ከለቦች ብቅብቅ ማለት የጅማሬው መልካም ንግሮች ኾነው በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። ያዝልቅልን!

አዘጋጅ ብሩክ ካ. ከአዲስ አበባ:        አቅራቢ መዝገቡ ሀይሉ