ዋዜማ ራዲዮ- ሸገር የጦር ቀጠና ሆናለች፡፡ ፈራሽ፣ አስፈራሽና አፍራሽ ተፋጠዋል፡፡ 54ሺ ሄክታር የምትለጠጠው አዲስ አበባ 34ሺ ሄክታሯ ፈርሶ ይገነባል፡፡ ታዲያ ምንድነው ወረገኑ እያሉ ማላዘን፣ ስለምንድነው ቀርሳ ማንጎ እያሉ መሟዘዝ፡፡

ጉድ እኮ ነው! አሜሪካን ግቢ ለብቻው ያለቅሳል፣ ባሻ ወልዴ ችሎት ለብቻው ያለቅሳል፣ ቴድሮስ አደባባይ ጀርባ ለብቻው ያለቅሳል፣ ገዳም ሰፈር፣ ካዛንቺስ፣ ባምቢስ፣ ኡራኤል ለየብቻቸው ያቅሳሉ፡፡ ወረገኑ ሲፈርስ ቀርሳ ነግበኔ ብሎ አልጮኸም፡፡ ይህ ነው የከተማዋ ችግር፡፡ ይህ ነው የአገሬ በሽታ፡፡ የአዲሳባ ስጋት ‹‹አተት›› ነው ይላሉ፡፡ አይደለም፡፡ የአዲሳባ አተት ‹‹ምናገባኝ›› ነው፡፡ የሸገር ወረርሽኝ ኮሌራ ነው ይላሉ፡፡ አይደለም፤ የሸገር ወረርሽኝ አለማበር ነው፡፡ ሌላው ሲነካ አብሮ አለመጮኽ፡፡

አስፈራሽና አፍራሽ የስልክ እንጂ የደም ግንኙነት የላቸውም፡፡ አስፈራሾች እኮ ከሚሞቀው ቢሯቸው እንኳ አይወጡም፡፡ ክረምት ነዋ! ማሞቂያ ከተበጀለት ቢሯቸው ወጥተው ወደ ሽንጣሙ ሊሙዚናቸው እስኪገቡ ብርዱን አይችሉትማ፡፡ ስለዚህ ከቢሮ አይወጡም፡፡ ቢበዛ ስልክ ነው የሚደውሉት፡፡ ወደ አፍራሾች፡፡ ‹‹ሕገወጦችን አንድባንድ አፍርሷቸው›› ይላሉ፤ በቀጭኑ ሽቦ ቀጭን ትዕዛዝ ያወርዳሉ፡፡ ይህን ጊዜ መመሪያ ወደ ወረዳ ወረደ እንላለን፡፡ አስፈራሾች አይደሉም፣ አፍራሾች ናቸው በየግንባሩ የሚዋደቁት፡፡ ያውም ለማያምኑበት ጥሪ፡፡ በአቢሲኒያ ምድር ይህ ሲሆን የመጀመርያ አይደለም፡፡ ልማዱን አስፍተን ያየነው እንደሆነ ከ10 ዓመት በፊት ሁለት እርስበርስ የሚናናቁ ሰሜናዊ የበረሀ ወዳጆች በተኳረፉ 70ሺ የዋሕ ደቡባዊ ነፍስ ረግፏል፡፡ የ70 ሺ የድሀ ልጅ ደም በከንቱ ፈሷል፡፡ ምን ለማግኘት? ምንም፡፡ ቤት የሌላቸው ፖሊሶች ቤት የሌላቸው ሲቪሎችን ለመግደል ሲሉ ሞተዋል፡፡ ለዝክራቸው የሚሆን ኮንዶሚንየም እንኳ ያልተበጀላቸው ናቸው፡፡ ፈራሽም አፍራሽም ቤት እንዳይኖራቸው ያደረገው አካል ሁልጊዜ ጠግቦ ያገሳል፣ ይፎልላል፡፡ ድሀን በድሀ ላይ እያስነሳ ትዊስት ይደንሳል፣ በጋራ ጉሪ ተራራ ባስገነባው ቤተ መንግሥት ይንፈላሰሳል፡፡

የወረዳ 1 አስተዳዳሪ ሟች ታሪኩ ገና ድክ ድክ የሚል የ2 ዓመት ልጅ አባት ነበር፡፡ ልጁን ስሞ እንኳን አልጠገበም፡፡ ስለልጁ የነገ ተስፋ ከመጨነቅ ይልቅ የፓርቲው ጭፍን ትዕዛዝ አስጨነቀው፡፡ እንደወታደር በረረ፤ ወደ ቀርሳ ኮንቶማ፡ ከንቱ ሞት ሞተ፡፡ ሬሳው ወደ ትውልድ አገሩ ሸንኮራ ሲሸኝ የተገኙት ከንቲባውና ምክትላቸው ከቀብር ሽኝት ሲመለሱ የውስኪ መለኪያ ጨብጠው ስለሚፈርሱ ሌሎች ሰፈሮች ሲማከሩ ነበር፡፡ ስለሟቹና ያላባት ስላስቀረው ልጅ ቀጣይ ተስፋ ለሰከንድም እንደማያስቡ ድርጊታቸው ይመሰክራል፡፡ ለሰው ልጅ ለማያምንበት ግዳጅ እንደመሞት ከንቱ ሞት አለን?

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!
መንግሥታችን የከተማ ድህነትን ለማጥፋት አሁን አቋራጭ መንገድ የተገለጠለት ይመስላል፡፡ ድሆችን ማጥፋት፣ ማጨድ፣ ከቀያቸው ማፈናቀል፡፡ ወደመጡበት መመለስ፡፡ ወረገኑ የተጀመረው ድሀን የመጥረግ ዘመቻ በሌሎች ክፍለከተሞች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ አቃቂ ቃሊቲና ሉቄ ተራራ ባለሳምንት ናቸው፡፡ ይህ የክረምቱ ‹‹ሲዝን›› እንደተጠናቀቀ ደግሞ ፈረሳው ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ እንደነገርኳችሁ ሸገር ሁለት ሦስተኛዋ ፈራሽ ናት፡፡ 34ሺ ሄክታር ከድሀ መጽዳት ይኖርበታል የሚል አቅጣጫ ተቀይሷል፡፡

ክቡራትና ክቡራን!
በዚህ ጊዜና ወቅት…የሸገርን ሕዝብ በጥቅሉ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ከሕዝብ ዘርፎ የ40 ሚሊዮን ብር ቤት የሚሠራና የወዳደቀ እንጨት ለቅሞ ዛኒጋባ የሚሠራ፡፡ እውነት ነው ለፍቶ አዳሪዎቹ የላፍቶ ቀርሳ ሰፋሪዎች ሕጋዊ አልነበሩም፡፡ 13 ሚሊዮን ረሀብተኛ ባለበት በ40 ሚሊዮን ብር ቤት የሚገነቡት ገዢዎቻቸው ሕጋዊ እንዳልሆኑት ሁሉ፡፡ እርግጥ ነው የላፍቶ ቀርሳ ነዋሪዎች መሬት ወራሪዎች ናቸው፤ ሥርዓቱ ወራሪ እንደሆነው ሁሉ፡፡

ትዝታን እናዚም! ምርጫ 97ን ተከትሎ ካድሬዎች የቻላችሁትን ያህል መሬት ዉረሩ ተባሉ፡፡ በማን? በዱርየው መንግሥት፡፡ መሬት ወረሩ፣ ዓመታት ተቆጥረው ሕጋዊ ሆነላቸው፡፡ ይህን ተግባር መሬት አልባ ዜጎች ተመለከቱ፡፡ ተበረታቱ፡፡ አደረጉትም፡፡ ዝም ተባሉ፡፡ ይህ ምን ነውር ነበረው? ነውረኛው ‹‹ውረሩ›› ብሎ ወረራን ሕጋዊ ያደረገ ሥርአት ነው፡፡ መጠየቅ ካለበትም ይህንን ሕገወጥነት ፈልፍሎ የፈጠረው ሥርአት ነው፡፡ እንጂማ ባገኙት ገላጣ መሬት፣ በገዛ አገራቸው መታወቂያ አውጥተው፣ ኮብል ስቶን አንጥፈው፣ መብራትና ዉኃ ገጥመው፣ ወልደውና ከብደው የኖሩ ዜጎች ስለምን‹‹ ሕገወጦች›› ይባላሉ?
ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!
ስፍራው ድረስ ሄጄ፣ ከእስር የተረፈ ወዳጅ አፍርቼ እንደተረዳሁት…የቀርሳ ኮንቶማ ሰፋሪዎች ለዓመታት ቃል ሲገባላቸው ኖረዋል፡፡ ሕጋዊ እንደሚሆኑ፡፡ በገዢው ፓርቲ የበታች አመራሮች ተታለዋል፡፡ ካድሬዎች በተደጋጋሚ ካርታ እንደሚሰጧቸው ሰብከዋቸዋል፡፡ እነርሱም ይህንን ቃል በግማሽ ልብም ቢሆን በማመን፣ ገንዘብ አዋጥተው፣ ለሰፈራቸው የፍሳሽ ቦይ አስቆፍረው፣ የኮብልስቶን ንጣፍ አበጅተው፣ የአረንጓዴ ልማት ላይ ተሳታፊ ሆነው፣ በመለስ ዜናዊ ሲምሉና ሲገዘቱ ቆይተዋል፡፡ መብራትና ዉኃ በስማቸው ቆርጠዋል፤ የአፈር ግብር ገብረዋል፣ መታወቂያ ተረክበዋል፡፡ እንዴት ይህ ቀን ይመጣል ብለው ሊገምቱ ይችላሉ?

በቅስቀሳ የተሳተፈ የአካባቢው ነዋሪ ጎረምሳ እንዳጫወተኝ በምርጫ ሰሞን የበላይ ካድሬዎች ቀያቸው ድረስ መጥተው ‹‹እናንተን የነካ ንብን ነካ›› እያሉ ሸንግለዋቸዋል፡፡ ለምሳሌ ምርጫ 2007 ላይ በአካባቢው ኢህአዴግን ወክለው ሲወዳደሩ የነበሩት ሰው ነዋሪዎችን ሰብስበው ‹‹ፍላጎታችን የተወሰነ ክፍያም ቢሆን ከፍላችሁ በአስቸኳይ ወደ ሕጋዊነት እንድትዘዋወሩ ነው፡፡ ፓርቲያችን ሕዝብን ያከብራል፣ የሕዝብ ድምጽን ያከብራል፣ ማንንም የማፈናቀል ተልዕኮ የለውም፣ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ፓርቲያችንን በነቂስ ወጥታችሁ ስትመርጡ ነው›› ብለው በተስፋ ሸንግለዋቸዋል፡፡ አንዴ ብቻ አይደለም ሁለት ሦስቴ፡፡ ለዚህም ነው ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ከፍተኛ መራጭ ወጥቶ ከመረጠባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ዉስጥ የንፋስ ስልክ ላፍቶውን ወረዳ አንድን የሚስተካከል ያልተገኘው፡፡ ገዢው ፓርቲ በዚህ ደረጃ ቀጣፊና ውሸታም ነው፡፡ በግሌ በዚህ ዱርዬ ፓርቲ እየተመራሁ መሆኑ በራሱ ያሳፍረኛል፡፡

ክቡራትና ክቡራን!
አምላክ ለፓርቲዎች ገነትና ገሀነም ካለው የገሀነም ቁልፍን የሚረከበው ኢህአዴግ ይመስለኛል፡፡ ዉሸታም ነዋ! ሕዝብን ደጋግሞ የሚዋሽና ዐይኑን በጨው የሚያጥብ ፓርቲ ከኢህአዴግ ሌላ የት ይገኛል?
አንድ ጊዜ የቀርሳ-ኮንቶማ-ማንጎን ሕዝብ ሰልፍ ጠራ፡፡ ማን? ኢህአዴግ!
ሰልፉ ላይ ቲሸርት አለበሰ፡፡ ማን? ኢህአዴግ! ዘምሩ አላቸው፣ማን? ኢህአዴግ! ‹‹መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው›› እያሉ ጩኹ ተባሉ፡፡ እንደተባሉት ጮኽ ብለው ዘመሩ፡፡

እንደተነገረኝ ከሆነ በማንኛውም የኢህአዴግ ሰልፍ የቀርሳን ነዋሪ ያህል ቀድሞ የሚገኝ አልነበረም፡፡ የጽዳት ዘመቻ ሰልፍ፣ የአረንጓዴ ልማት መለስ ዜናዊ ሰልፍ፣ የማንኛውም ኢህአዴግ የሚደግፈውን ነገር የሚደግፍ የድጋፍ ሰልፍ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ሰልፍ፣ የወጣቶች ሊግ ሰልፍ፣ የሴቶች ሊግ ሰልፍ፣ የግንቦት 20 ሰልፍ፣ የሰማዕታት ሰልፍ፣ የታላቁ መሪ ርዕይ ሰልፍ…አንዱም አይቀራቸውም ነበር፡፡ የገነቡትን ቤት በልዩ ግብረኃይል ለማፍረስ ኢህአዴግ እያሴረ በነበረበት ወቅት እንኳን የሰማዕታትን ቀን ለማክበር በሰፈሩ ወጣቶች ዘንድ ደማቅ ዝግጅት ሲደረግ ነበር፡፡

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!
ቀርሳ ሲፈርስ ይህ የመጀመርያው እንዳልሆነ እንድትረዱልኝ እሻለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ሙከራ ተደርጎ ከሽፏል፡፡ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ማደስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከ9 ወራት በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ የአካባቢውን ወጣቶች ለማናገር በሞከረበት ወቅት የአንገት ሀብሉ ተበጥሶ፣ አንድ ሁለት ጥፊ ቀምሶ መመለሱን ያስታውሳል፡፡ ደግነቱ ተማቺም መቺም የድርጅት አባላት ስለነበሩ ውስብስብ ችግር ላለመፍጠር ነገሩ ተድበስብሶ አለፈ፡፡

ሟቹ የወረዳ 1 አስተዳዳሪ ታሪክ ፍቅሬ ይባላል፡፡ ወጣትና ታታሪ የኢህአዴግ አባል ነበር፡፡ ያን ቀን ከአለቃው ከአቶ ኸይሩ በተላለፈለት መመሪያ መሰረት ነዋሪዎቹን በቀጠና ከፋፍሎ እንዲያወያይ ይነገረዋል፡፡ አቶ ኸይሩም በስፍራው ዘግይተውም ቢሆን እንደሚገኙ ገልጸው እርሱን አስቀድመው ይልኩታል፡፡ ወጣቱ አስተዳዳሪ ወደ ቀርሳ ለመሄድ የተመደበለት ሾፌር በሰዓቱ ሊገኝለት አልቻለም፡፡ ሾፌሩን ከመጠበቅ ብሎ በሞተር ሳይክል ተፈናጦ በአካባቢው ይደርሳል፡፡ እየከነፈ፡፡ ልማቱን ለማረጋገጥ፡፡

ሥራ አስፈጻሚ ታሪኩ ፍቅሬ ነዋሪዎቹን አብጠርጥሮ ያውቃቸዋል፡፡ ብዙ የልማት ሥራዎችን አብሯቸው ሠርቷል፡፡ እርሱ በጭራሽ ያልጠበቀው ነገር ቢኖር የነዋሪዎቹን ቁጣ ነበር፡፡ የሚያውቃቸው ቀርሳዎች አልሆኑለት አሉ፡፡
እርግጥ ነው የኢህአዴግ አባላት የሚበዙባቸው የቀርሳ ነዋሪዎች የፓርቲያቸውን ባህሪ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ አባል የሆኑትም ‹‹ከታደገን›› በሚል እንጂ ፈቅደውና ወደው አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ፓርቲያቸው ሕግ ካጸደቀ በኋላ ለይስሙላ ሕዝብ እንደሚያወያይ ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ ገድዬ አድናለሁ እንደሚልም ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ እንወያይ ሲል ‹‹ልጨቁናችሁ ስለሆነ ፍቀዱልኝ›› ማለቱ እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ለ10 ዓመታት ሲኖሩ ኢህአዴግን በማስደሰት ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ቀርሳ ኮንቶማዎች የኢህአዴግ ክፉ የቤት ተከራዮች ሆነው ነበር የኖሩት፡፡ በጥንቃቄ፡፡

የወረዳ 1 አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩም ሆነ አለቆቻቸው ነገሮች እየተካረሩ እንደሆነ አልጠፋቸውም፡፡ ኾኖም ዘዴ ዘይደዋል፡፡ ነዋሪዎችን በቀጠና በቀጠና አድርጎ ማወያየትና በሐሳብ እንዲከፋፈሉ ማድረግ የሚል ስልት ነድፈው ነበር የሚንቀሳቀሱት፡፡ ይህ ስልት ብዙዉን ጊዜ ተቃዋሚዎችን ለመከፋፈል ይውላል፡፡ አቶ ታሪኩ ይህን እቅድ ነድፈው ተንቀሳቀሱ፡፡ ስብሰባውን ገና ከመጀመራቸው ታዲያ ከሩቅ ኡራኤል ሰፈር ጩኸት ተሰማ፡፡ ምንድነው ሲባል አፍራሽ ግብረኃይሉ መጥቷል የሚል ሆነ፡፡ ይህን ጊዜ የተወያዩ ቁጣ ገነፈለ፡፡ ‹‹አንተ እዚህ በስብሰባ ጠምደኸን በጎን ቤታችንን ታስፈርስብናለህ›› ብለው አስተዳዳሪውን መጎነታተል ያዙ፡፡

ወጣት ታሪኩ ሰዎቹ መረጋጋት የራቃቸው እንደሆኑ ስላሰበ ሽጉጡን አውጥቶ ሁለት ጊዜ ወደላይ ተኮሰ፡፡ ሰዎች ሲሸሹት በተፈጠረው ክፍተት፣ ከሚንቀለቀለው የሕዝብ ቁጣ ሰብሮ ለመውጣት ሲንደረደር እንቅፋት መታውና ወደቀ፡፡ መውደቁ ነገሩን አከፋው፡፡ ከየት እንደመጣ ያልታወቀ ገጀራ ጭንቅላቱ ላይ አረፈ፡፡ በወቅቱ አጅበውት የነበሩት የቀበሌ ሚሊሻዎች የሕዝብን ቁጣ ሊቋቋሙት ስላልቻሉ የራሳቸውን ነፍስ ለማዳን መፍጨርጨር ያዙ፡፡ ሦስት ፖሊሶች በተመሳሳይ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ ተስፋዬ ኃይሉና ምክትል ኢንስፔክተር ሚካኤል ሽፈራው ከሟቾቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ ሌላ አንድ ኮማንደር ቆስሎ ሆስፒታል ከገባ ከሁለት ቀናት በኋላ በዚሁ ሰሞን ሕይወቱ አልፋለች፡፡ በቁጥር 60 የሚጠጉ ሌሎች ፖሊሶች ልደታ ፖሊስ ሆስፒታል መተኛታቸውን ሸሽተው ካመለጡ የሸገር ፖሊሶች ሰምቻለሁ፡፡

ከዚህ በኋላ የሆነውን የሚያውቅ የለም፡፡ እናቶችና ሴቶች ይጮኻሉ፣ ወጣቶች ይታገላሉ፣ ከደቂቃዎች በኋላ የደረሰው አፍራሽ ግብረኃይል ሁኔታውን በቀላሉ መቆጣጠር አልቻለም፡፡ ነገሩን አስቸጋሪ ያደረገው ደግሞ ጥቂት የማይባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ታጣቂ ኾነው መገኘታቸው ነው፡፡
ታጋሽ የጦማሬ አንባቢዎች ሆይ!
እስቲ በአጭሩ አካባቢውን እንዳስቃኝ ፍቀዱልኝ፡፡
ነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሰፊ የቆዳ ስፋት ካላቸው ክፍለከተሞች አንዱ ነው፡፡ በውስጡ 12 ወረዳዎች ይገኛሉ፡፡ ችግሩ የተፈጠረበትን ወረዳ አንድን በስፋት የሚወዳደር ግን የለም፡፡ ወረዳ 1ን የሚልቅ ወረዳ እንኳን በንፋስ ስልክ በመላው አዲስ አበባም ተፈልጎ አይገኝም፡፡ በነፋስ ስልክ ላፍቶ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ተደምረው፣ የአስራ አንዱም ወረዳ ቆዳ ስፋት ተደምሮ ወረዳ አንድን አያህልም፡፡ በሌላ ቋንቋ በንፋስ ሰልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ወደ 98ሺ የነዋሪ ፋይሎች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ዉስጥ ከ45ሺ በላይ የሚሆኑት የወረዳ አንድ ፋይሎች ናቸው፡፡ ስፍራው የሚገኘው ከሃይሌ ጋርመንት ወደ ፈጣን የአዳማ መንገድ እንደተገባ መብራት ኃይል የሚባለውን ሰፈር ይዞ በስተግራ ነው፡፡

ከ97 በፊት የተነሳው የአየር ካርታ ቦታው አንድም ነዋሪ እንደማይገኝበት ያሳያል፡፡ ከግጭቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የአየር ካርታ ቢነሳ እንኳን ለሰው ለመርፌ መውደቂያ የሚሆን ቦታ አይታይም፡፡ ዛሬ ካርታ ቢነሳ ደግሞ ከ97 በፊት ወደነበረው ምስል ተመልሷል፡፡ ሙልጭ ያለ መሬት፡፡
ቀርሳና ማንጎን አሁን ማፍረስ ለምን ተፈለገ?

ክፉ አከራይ እንኳን ሐምሌ ግም ካለ ከቤት አያስወጣም፡፡ ኢህአዴግ ግን ግድ የለውም፡፡ መንግሥታችን የክፉ አከራይን አዛኝ ልቦና እንኳ አልታደለም፡፡ ለምን ይሆን? ለምን በክረምት? እውነት ለመናገር ይህ ከክፋት የመነጨ አይደለም፡፡ ከድንቁርና እንጂ፡፡ በኢህአዴግ ቤት የሚያስብ ጭንቅላት አልተፈጠረም፡፡ የሚያመዛዝን አእምሮ አልበቀለም፤ ለነጻ ዉይይት ቦታ የለም፡፡ የኢሕአዴግ አእምሮ የዘመቻ አእምሮ ነው፡፡ አመራሩ ግብታዊ ነው፡፡ በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ የአመራሩ ጭንቅላት ኦና ሆኗል፡፡ እንደፈረሱት ቤቶች ፈርሷል፡፡
ለምሳሌ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ፍጥነት እንዲፈርሱ የተወሰነባቸው ሰፈሮች አሉ፡፡ ላለፉት 8 ዓመታት አንዳችም ግንባታ አልተካሄደባቸውም፡፡ ስንት ሺ ቤተሰብ በነዚህ ቦታዎች ላለፉት 8 ዓመታታ ተጠልሎ መኖር ይችል ነበር፡፡

አንዳንድ የፈረሱ ቦታዎች ልማት ርቋቸው ሌላ ዙር የጨረቃ ቤት ግንባታ የተጀመረባቸው እንዳሉ ታውቃላችሁ? ይህ ቦታም ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥመው በመስጋት ኃላፊዎች ቦታውን ባስቸኳይ ለአልሚዎች አስተላልፉት ተብለዋል፡፡
ቀርሳና ማንጎ እንዲፈርስ የተፈለገው በሦስት ፕሮጀክቶች ምክንያት ነው፡፡ አንዱ ለቄራዎች ድርጅት ነው፤ በ1.5 ቢሊዮን ብር ዘመናዊ ቄራ ተገንብቶ አሁን አገልግሎት የሚሰጠውን ቄራ ለመዝጋት ታስቧል፡፡ ቄራ ከሰሞኑ 250 ሺ ካሬውን በቅርጫ መልክ አርዶና በልቶ ወስዶታል፡፡ ግዛቱን ስጋና መሬት ከሚናፍቁ ዜጎች ለመጠበቅ በቆርቆሮ አጥር እያስከበረ ነው፡፡ ከድኃ የነጻው ቀሪው መሬት ደግሞ ለዋሊያ ብረታ ብረት ተሰጥቶታል፡፡ 50ሺ ካሬ ይበቃኛል ብሎ ይህንኑ ወስዷል፡፡ ከዚህ የተረፈው መሬት ደግሞ ለሀብታሞች በሊዝ እየተቆነጠረ የሚቸረቸር ነው፡፡

በነገራችሁ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሊዝ ለባለሀብቶች የሚሸጡ ቦታዎች እጥረት በመፈጠሩና መንግሥት ካቀዳቸው የተለጠጡ ፕሮጅክቶች አንጻር የበጀት እጥረት ስለገጠመው ለሁሉም ክፍለከተሞች ሰፋፊ የመልሶ ማልማት ቦታዎች እንዲዘጋጁ ለከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤቶች መመሪያ ተላልፏል፡፡ ለቀርሳ ነዋሪ መፍረስ አንዱ ምክንያትም ይኸው መመሪያ ነው፡፡
የቀርሳ ነዋሪዎች ምን ይላሉ?
የቀርሳ ኮንቶማና ማንጎ ነዋሪዎች ጥያቄያቸው ‹‹ከቻላችሁ ሕጋዊ አድርጉን፣ ካልቻላችሁ ኮንዶሚንየም መዝግቡን፣ቤት አለን ብለን ኮንዶሚንየም ሳንመዘገብ አመለጠን- አዘናጋችሁን›› የሚል ነበር፡፡ መልስ አጡ፡፡ ቀጠሉና ‹‹ቢያንስ በክረምት አታስወጡን›› አሉ፡፡ መልስ አጡ፡፡ ‹‹እሺ ተለዋጭ መጠለያ ስጡን፣ ድንኳን ነገር ወይም ትልቅ መጋዘን፣ ክረምቱን የምንጠለልበት›› አሉ፡፡ መልስ አጡ፡፡ ይህን ጥያቄያቸውን አንድ ጊዜ አይደለም ያቀረቡት፡፡ በተደጋጋሚ ነው፡፡ ‹‹እኛ ይህ ቦታ ህጋዊ ይደረግላችኋል ተብሎ ስለተነገረን ኮንዶምንየም እንኳ አልተመዘገብንም፤ ቢያንስ ኮንዶምንየም እጣ ላይ መዝግቡን›› የሚለውን ጥያቄያቸውን የሰሙ ሹሞች ደግሞ ሳቁባቸው፡፡ ‹‹1 ሚሊዮን ተመዝጋቢ ተሰልፎ ቤት እየጠበቀ እናንተ ኮንዶምንየም ስጡን ስትሉ አይከብዳችሁም?›› አሏቸው፣ ጥያቄውን አንሻፈው፡፡

አዘኑ፡፡ ኾኖም ተስፋ ሳይቆርጡ ሰልፍ ማሰናዳት ያዙ፡፡ ግጭቱ ከመከሰቱ በፊት አቤቱታቸውን ለሴቶችና ሕጻናት ሚኒስቴር፣ ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ሥራ አስፈጻሚ፣ ለክፍለከተማው የኢሀአዴግ ጽሕፈት ቤት በጽሑፍም በቃልም አቅርበዋል፡፡ ወደ ሁሉም ቢሮዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሒደዋል፡፡ እናቶች በተለይ ደማቅ ሰልፍ ነበር ያካሄዱት፡፡ የሚሰማቸው ጠፋ እንጂ፡፡ በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸው በመሰማቱ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በደኅንነት ኃላፊዎች ተገለጸላቸው፡፡ በእንቢተኝነት ፀኑ፡፡ ለሰልፉ ቀጠሮ ይዘው ሳለ ሁሉንም ነገር የቀየረችው ቀን ደረሰች፡፡

ቀርሳና ኮንቶማ ዛሬ አይሲል ጥሎት የሸሸው የኢራቅ ግዛት እንጂ የሸገር መልክ የላትም፡፡ በፈረቃ አካባቢውን የሚጠብቁና በቀን 3 ጊዜ ኮቾሮ ብስኩት የሚታደላቸው ወታደሮች እዛም እዚም ይታያሉ፡፡ ከወጣት ነዋሪዎች ሲሶዎቹ ተለቅመሰው እስርቤት ተወርውረዋል፡፡ ቀሪዎቹ ክፍለ አገር ዘመድ ጋር ተደብቀዋል፡፡ ጥቂቶች ደግሞ በረሀ አቋርጠው አረብ አገር ለመሄድ ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ መሄጃ ያጡ እናት የድሀ ድሀዎች ላስቲክ ወጥረው ከአካባቢው አንለቅም ብለው ቆይተዋል፡፡ ፖሊስ በነዚህ ላይ ምን እርምጃ እንውሰድ በሚል ጥያቄ ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት አቅርቦ የነበረ ሲሆን ከንቲባው በማኅበራዊ ሚዲያ ጫና የተነሳ ጊዜያዊ የቆርቆሮ መጋዘን ለአረንጓዴ ቦታ በተያዘ ስፍራ እንዲገነባና እጅግ የድሀ ድሀ የሆኑ ተፈናቃይ እናቶች ለጊዜው እዚያው እንዲያድሩ ወስነው የሰው ማጎርያ መጋዘኑ በግንባታ ላይ ነው፡፡
ዉድ የጦማሬ ተከታታዮች!
ሸገር ሁለት ሦስተኛዋ ፈራሽ ናት፡፡ ይህ የሞተ ጉዳይ ነው፡፡ ሸገር ከዚህ ወዲያ ለድሀ የሚሆን ቦታ የላትም፡፡ ይህንን ጽሑፍ የምታነቡበት ቤት ከወራት በኋላ እንደማይፈርስ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁን?
እኔ ግን እላለሁ፡፡ በዚህች ከተማ ‹‹ሕገወጥ›› የምለው እናንተን አይደለም፡፡ ለኔ የከተማዋ ሕገወጥ ሕዝብ ሳይመርጠው 10 ዓመት በስልጣን ላይ የቆየውን ፓርቲ ነው፡፡ መፍረስ ካለበትም ፓርቲው እንጂ እናንተ አይደላችሁም፡፡
እግዚአብሔር ሸገርን ከአተትና ከኢህአዴግ ይጠብቅ!

አውግቸው ቶላ
ለዋዜማ ራዲዮ