ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመሰረተው ክስ የህብረት ማኑፋክቸሪንግ እና ማሽን ግንባታ ኢንዱስትሪ የሰራተኞች ንፅህና መስጫ (ላውንድሪ) አገልግሎት ኢንዱስትሪው በራሱ ማድረግ የሚችለበት አዋጪ ጥናት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም 1ኛ ተከሳሽ የሆነው ሌተናንት ኮሎኔል ተሰማ ሃላፊነቱን ያላግባብ በመጠቀም ጥናቱን ውድቅ እንዳደረገ ገልፅዋል፡

ይልቁንም ባለቤቱ የሆነችው 3ኛ ተከሳሽ ሌተናል ኮለኔል ዙፋን በርሄ ፣ ጓደኛው የሆነችው 2ኛ ተከሳሽ ኬሪያ ዋስእ እና ወንድሟ ባለድርሻ የሆኑበትን ክሊን ወሽ ኃ.የተ.የግ.ማህበር የተባለ ድርጅት ለዚሁ ዓላማ ሲባል እንዲቋቋም ማድረጉን፤ መወዳደሪያ ዋጋ ሳያቀርብ፤ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ያላገኙትን የመስሪያ ቦታ፣ መብራትና ውሃ ኢንዱስትሪው እንዲያቀርብለት በማድረግ ክሊን ወሽ ኃ.የተ.የግ.ማ እንዲሰራው ማድረጉንም አክሏል፡፡

በዚህም ከጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም እስከ ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ለድርጅቱ ያላግባብ ብር 1,417,785.05 ብር በመክፈል ጥቅም ያገኘና ያስገኘ መሆኑን አካቶ ነበር፡፡

ይህ የክስ መዝገብ ከተከፈተበት ጊዜ አንስቶ ሌተናንት ኮሎኔል ተሰማ ግደይ እና ኬሪያ ዋስእ በቁጥጥር ስር ባለመዋላቸው ክሳቸው በሌሉበት ሲታይ ቆይቶ ነበር፡፡

3ኛ ተከሳሽ የሁኑት ሌተናት ኮለኔል ዙፋን በርሄ ላይ የመሰረተውን ክስ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሲያቋርጥ ሁለቱን ተከሳሾች ደግሞ ጉዳዩን የተከታተለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡

በዚህም መሰረት ሌተናት ኮለኔል ተሰማ ግደይ በሌሉበት የ9 አመት ፅኑ እስራት እና የ30 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ የተላለፈባቸው ሲሆን ኬሪያ ዋስእ ደግሞ የ9 አመት ፅኑ እስራት እና 50ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተፈርዷል፡፡