በኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ዞንና ጋምቤላ ክልል በመሬት ወረራና የመንግስት ግዙፍ ልማት ፕሮጀክቶች ሳቢያ በሚደርሰው መፈናቀል ምክንያት የተለያዩ ብሄረሰቦች ለመፈናቀልና ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚደርስባቸው መነገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡
በተለይ በጋምቤላ ክልል ሰፋፊ ለም መሬቶች ለውጭ ሀገር ኩባንያዎች በርካሽ የዋጋ ተመን መቸብቸብ ከጀመሩ ወዲህ ዓለም ዓቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስት ዜጎችን ከቀያቸውና ከኑሮ ዘይቢያቸው አፈናቅሏል በማለት ክፉኛ ይከሳሉ፡፡ መንግስትም ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶቹን “የኢትዮጵያን ልማት ማየት የማይፈልጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች” እያለ ከማውገዝ አልቦዘነም፡፡
በቅርቡም በጋምቤላ ክልል የአኝዋክና የሌሎች አናሳ ብሄረሰቦች መብት ተሟጋቾች በነበሩት ፓስተር ኦሞት አጉዋ ኦክዋይ፣ አሽኔ አስቲን ቱቶይክ እና ጀማል ኡመር ሆጃሌን የተባሉ ሦስት ግለሰቦች ላይ የሽብርተኝነት ክስ መስርቶባቸዋል፡፡ (የቻላቸው ታደሰ ዘገባ ዝርዝሩን ይነግረናል-አድምጡት)
ፓስተር ኦሞት አጉዋ፣ አሽኔ አስቲን እና ጀማል ኡመር የተባሉት የጋምቤላ ክልል መብት ተሟጋቾች ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ባዘጋጁት በልማትና ምግብ ዋስትና ላይ በሚመክር ስብሰባ ላይ ለመታደም ወደ ኬንያ ናይሮቢ ሊያቀኑ ሲሉ ነበር፡፡
በሦስቱ ግለሰቦች ላይ መንግስት ክስ የመሰረተባቸው በሀገሪቱ የፀረ-ሽብር አዋጅ መሰረት ነው፡፡ የክሱ ጭብጥ ግለሰቦቹ በካናዳ፣ እንግሊዝና ኤርትራ ከሚገኙ “ሽብረተኞች” ጋር በመተባበር የጋምቤላ ክልልን ለማስገንጠልና ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ ሲንቀሳቀሱ እንደተደረሰባቸው ያስረዳል፡፡