• የብርን የምንዛሪ አቅም በማዳከም የውጪ ንግድን ለማሳደግ የተደረገው ሙከራ የተፈለገውን ውጤት አላስገኘም

ዋዜማ ራዲዮ- የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት የኢኮኖሚ ተሐድሶ ፕሮግራም ተግባራዊ የሆነውን የብር የምንዛሪ አቅምን በማዳከም የውጪ ንግድን የማሳደግ አሰራር ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የዳሰሳ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ከሁነኛ ምንጮች ሰምታለች። 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከፍተኛ የስራ ሐላፊ እንደነገሩን ብርን ከሀገሪቱ የንግድ ሸሪኮች መገበያያ ገንዘብ አንጻር እየተተገበረ ያለውን ዕለታዊ ዋጋ የማዳከም አሰራር የሚገመግም  የዳሰሳ ጥናት እየተሰራ ነው። በጥናቱ ላይ በመመርኮዝም ብርን በየዕለቱ የማዳከሙ ነገር “ይቀጥል” ወይንስ “አይቀጥል” የሚለው ላይ ከውሳኔ ይደረሳል ።

ዕለታዊ የብርን የውጭ ምንዛሬ ተመን ከንግድ አጋር ሀገራት መገበያያ አንጻር በፍጥነት የማዳከሙ እርምጃ ከሁሉም የማክሮ ኢኮኖሚ መመዘኛዎች አንጻር የማያዋጣ  ከሆነ ብሄራዊ ባንኩ ሌሎች አማራጮችን ለመከተል ይገደዳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከ2012 አ.ም ጀምሮ “የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ” በሚል ስያሜ እየተገበረ ባለው የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን አሰራር፣  የኢትዮጵያን ብር ትክክለኛ ዋጋውን እንዲያገኝ እና የወጪ ንግድን ለማሳደግ ይረዳል በሚል የብርን የምንዛሬ ተመን ከንግድ አጋር ሀገራት ተመን አንጻር እያዳከመ መጥቷል።

ዕለታዊው ፈጣን ምንዛሬን የማውረድ እርምጃ ከ2012 አ.ም ተጀምሮ በዚህ አመት(2014 አ.ም) እንዲያልቅና ኢትዮጵያ በገበያ የሚመራ የምንዛሬ ተመን እንዲኖራትም ታስቦ ነው ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው።

የምጣኔ ሐብት ፖሊሲ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን መንግስት አካሄድ ከእነ አለም ባንክና አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር ለማግኘት በጫና የወሰደው እርምጃ እንጂ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሊባል አይችልም ሲሉ ትችት ሲሰነዝሩ ይደመጣል።

ለአብነት በ 2012 አ.ም አመት መጀመርያ ላይ አንድ የአሜሪካን ዶላርን በባንክ ሲቀርብበት ከነበረው 29 ብር ይህን ዘገባ እስከሰራንበት ዓርብ ዕለት የካቲት 5 2014 አ.ም ዋጋው ወደ 50 ብር ከ32 ሳንቲም አድጓል። በነዚህ ጊዜያት የኢትዮጵያ ብር የምንዛሬ ተመን ከዶላር አንጻር በ58 በመቶ እንዲዳከም ተደርጓል። 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የ2013 አ.ም የመጨረሻ ሩብ አመት ሪፖርት እንደሚያሳየውም በአንድ አመት ብቻ የኢትዮጵያ ብር የምንዛሬ ተመን ከዶላር አንጻር 25.6 በመቶ ፣ ከእንግሊዝ ፓውንድ አንጻር ደግሞ በ41.6 በመቶ ተዳክሟል። 

ይህ አይነት የውጭ ምንዛሬ ተመን አሰራር ከዚህ ቀደም ተተግብሮ የማያውቅ ነው። ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ባስተዳደረባቸው ጊዜያት በ2003 እና በ2010 አ.ም ብርን በአንዴ በ22 እና በ15 በመቶ ያዳከመ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን በአመት ከስድስት በመቶ በላይ የብር የምንዛሬ ተመን እንዳይዳከም ገደብ ያስቀምጥ ነበር።

አሁን መንግስት እየተከተለ ያለው የምንዛሬ ተመን አሰራር የገቢ እቃዎችን ዋጋ በማስወደድ የዋጋ ንረትን የፈጠረ በመሆኑ ይተቻል።የምንዛሬ ተመኑ ተግባራዊ ከተደረገ አንስቶ የየወሩ አጠቃላይ የዋጋ ንረት ከ20 በመቶ በላይ ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ ከ30 በመቶ በላይ ሆኗል። የጥር ወር የዋጋ ንረት 34 በመቶ ሲሆን የታህሳስ ደግሞ 35 በመቶ እንደነበር ይታወሳል። 

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ካለው ጦርነት ጋር ተዳምሮም አብዛኛውን ዋና ዋና እቃዎች ከውጭ ለምታስገባው ሀገር የምንዛሬ አሰራሩ ለከፍተኛ ዋጋ ንረት ተዳርጋለች።

የምንዛሬ ተመን አሰራሩ ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ ባለፈው አመት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የተባለውን የምንዛሬ ገቢን ከወጪ ንግድ አግኝታለች። 3.6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የነበረው ያለፈው አመት ገቢ ከቀደመው አመት የ600 ሚሊየን ዶላር ብልጫ አሳይቷል። ነገር ግን ይህ የወጪ ንግድ ገቢ ጭማሬ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በመዳከሙ ሳቢያ ከተፈጠረ ተወዳዳሪነት የመጣ ሳይሆን በወቅቱ በአለም አቀፍ ገበያ ጥሩ ዋጋ ከነበረው ወርቅ ሽያጭ የተገኘ ጭማሬ ነበር። ከ600 ሚሊየን ዶላሩ ጭማሬ ወርቅ ብቻ ወደ 470 ሚሊየን ዶላሩን ጭማሬ አስገኝቷል። ይህም የምንዛሬ ተመን አሰራሩ በወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይ ለውጥ ማምጣቱ  ላይ ጥያቄን አስነስቷል።

ብሄራዊ ባንክ እያደረገ ያለው ጥናት በቀጣይ አመት  አሁን ያለውን የምንዛሪ ተመን አሰራር ባለበት ለመቀጠል አልያም የተለየ መንገድ ለመምረጥ አብይ መንገድ አመላካች ሆኖ እየተጠበቀ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]