ዋዜማ ራዲዮ- ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ደርግ ከአሜሪካ ገዝቷቸው ከነበሩ ሰባት የጦር መርከቦች አራቱን ሽጧቸዋል : ሶስቱን ደግሞ እስካሁን አልተረከባቸውም።
ኢትዮጵያ የባህር ሀይል ያስፈልጋታል : በቅርቡም ታቋቁማለች የሚል ንግግር ከመንግስት በተደጋጋሚ እየተሰማ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ዘመናዊና የባህር የአየር የየብስና የህዋ ተዋጊ ሀይል ለመገንባት እቅድ እንዳለውና ለዚህም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በዚህ ሳምንት ይፋ አድርገዋል። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና ሕንድ ውቂያኖስ አዋሳኝ የባሕር ሃይል ጦር ሠፈር ልትገነባ ማሰቧን ምክትል የጦር ሃይሎች ኤታማዦር ሹም እና የዘመቻ መምሪያ ሃላፊው ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር በመሆኗ ባሕር ሃይል እንደሚያስፈልጋት ተወስኗል- ብለዋል ጄኔራሉ፡፡ የባሕር ሃይሉን መልሶ ለማቋቋም ከሌሎች ሀገሮች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እዚህ ጋር ግን ኢትዮጵያ ባላት አቅም እንዴት ውድ የሆኑ የጦር መርከቦችን ገዝታ ነው የባህር ሀይልን የምታቋቁመው? የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ለመሰረታዊ ቁሶች እንኳ እስካሁን ያጠረው የውጭ ምንዛሬ ሲታሰብ ጥያቄው ተገቢ ይሆናል። ኢትዮጵያ አሁን ባላት አቅም አይደለም የጦር መርከቦችን መግዛት ፣ የባህር በር ሳይኖራት በርካታ የንግድ መርከቦችን መግዛቷ ለከፍተኛ ኪሳራና ተዳርጋለች። የባህር ሀይል ለማቋቋም ስትወስን የዕቅዱን ውስብስብ ገፅታ ዘንግታው ነው ማለት ይቸግራል። የባህር ሀይል ባለቤት መሆን የሚፈጥረው ሀገራዊ ኩራትና ክብር እንዳለ ሆኖ እንዲህ ባለ የሽግግር ጊዜ ይህ ቁልፍ ወታደራዊ ዕቅድ ከየት መነጨ?  ብሎ ማሰብም አስፈላጊ ነው።

ለቤታቸው ያልበቁት መርከቦቻችን

ዋዜማ ራዲዮ ከታመኑ የቀድሞ የባህር ሀይል ከፍተኛ አመራር እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ በደርግ መንግስት የመጨረሻ ዘመናት ኢትዮጵያ ከአሜሪካን ከገዛቻቸው የጦር መርከቦች ውስጥ አራቱን ተረክባ ነበር። ደርግ የሶቭየት ህብረት መፈራረስ ሲቃረብ ቅይጥ ኢኮኖሚን አወጀ። አሜሪካም የጦር መርከቦቹን አልሰራም አላለችም። ከነዚህ ውስጥም አራቱን የደርግ መንግስት ተረክቧል። ሶስቱን የመረከብ ሂደት ሲጀመር ሻእቢያ ኤርትራን ተቆጣጠረ።

ለጦር መርከቦቹ ግንባታም ጭምር ቅርብ የነበሩት የቀድሞ የባህር ሀይል ለዋዜማ ራዲዮ እንዳሉት ሻእቢያ ኤርትራን ሲቆጣጠር ደርግ ካዘዛቸው የጦር መርከቦች ቀሪ ሶስቱ ጉዞ ላይ ነበሩ።  በተፈጠረው ለውጥ ሳቢያ  አሜሪካ መርከቦቹን መልሳቸዋለች።ኢህአዴግም ክፍያ የተፈጸመባቸው እንደመሆናቸው ሊረከብ የሚችልበት እድል ቢኖርም እስካሁን ድረስ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ጥያቄውን እንኳ አላቀረበም። ርክክብ የተፈጸመባቸውን አራት የጦር መርከቦችንም ለሳውዲ አረብያ፣ ለየመን፣ ለሱዳንና ጅቡቲ እንደሸጣቸው ምንጫችን ነግረውናል።

የአብይ አህመድ መንግስት እነዚህን መርከቦች ከአሜሪካን ለመጠየቅ ስለማቀዱ መረጃ የለም። ድንገትም የባህር ሀይል ለማቋቋም ሲታሰብ ይህን የተከፈለበት ንብረት የማሰባሰብ ፍላጎት ስለመኖሩም አልሰማንም።

የመቶ ቀን ዕቅድ
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ካቢኒ አዋቅረው ለካቢኒያቸው እሳቸውና ሌሎች ሙያተኞች ስልጠና ካሰጡ በሁዋላ ለእያንዳንዱ ሚኒስትር የመጀመርያ 100 ቀናት ስራን ሲሰጡ ለመከላከያ ሚኒስቴር የባህር ሀይል ማቋቋም የሚለው ከተሰጡት ስራዎች ውስጥ አንዱ ነው።
ሆኖም የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሀመድ ከሰሞኑ በመቶ ቀን መስሪያ ቤትዎ የባህር ሀይልን ያቋቁማል ወይ? ተብለው ተጠይቀው : በመቶ ቀን ባህር ሀይልን ማቋቋም ይከብደናል።ምናልባት የሌሎች ሀገራት ልምድ ልናይ እንችላለን እንጂ በመቶ ቀን ይህ ተቋም ይቋቋማል ብዬ አላስብም ብለዋል።

ለመንግስት እጅግ ከቀረቡ ምንጮች ለማረጋገጥ እንደሞከርነው ከሆነ የባህር ሀይልን ለማቋቋም  ጥቅል ጥናት መሰራቱን ከመግለፅ ውጪ ጉዳዩ ለረጅም ጊዜ የታሰበበት መሆኑን ይጠራጠራሉ። ድንገትም ጉዳይ ወታደራዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምስጢራዊ ጠባይ ኖሮት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።

አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው  የማሪታይም ህግ ባለሙያ አሁን ባለ ሁኔታና በተቀመጠ ጊዜ ኢትዮጵያ የባህር ሀይል የሚኖራት በድንገቴ ሊሆን ይችላል እንጂ የሚታዩ ነገሮች አዎንታዊ አይደሉም ይላሉ።
ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ።ለባህር ሀይል ባለቤትነት ሀገሪቱ የራሷ ልትቆጣጠረው የምትችለው የውሀ አካል ያስፈልጋታል።ኢትዮጵያ ይህ የውሀ አካል የላትም።ወይንም እንደነ ጅቡቲና ኤርትራ ካሉ ሀገራት ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ትስማማ አትስማማ የሰማነው ነገር የለም።ቢሆን እንኳ ከጅቡቲ የባህር ሀይል ባለቤት የሚያደርግ የውሀ ግዛትን ማግኘት ከባድ ነው። ምክንያቱም ይህ ስፍራ በሀያላን ሀገራት የተከበበ ነው።ምናልባት ከኤርትራ ጋር የውሀ አካል ይዞታ ስምምነት በሚስጥር ተደርጎ ሊሆን ይችላል። ይህም ቢሆን ለኤርትራ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ስለሆነ በቀላሉ የምትስማማበት ነው ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።

ለግርምት እንዘጋጅ?

ምክትል የኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሀኑ ጁላ ደግሞ ከኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያ የባህር ሀይል ለማቋቋም የባህር በርን ከህንድ ውቂያኖስና ከቀይ ባህር ለማግኘት ሙከራ እናደርጋለን አይነት ነገርን ተናግረዋል።ሆኖም ስፍራው ብዙ  ውስብስብ ፍላጎት ያለበት በመሆኑ የባህር ስፍራውን የማግኘቱ ነገር ቀላል ሆኖ አይታሰብም።
ታድያ የአብይ አስተዳደር ሶስት አስርት አመታት ን ፈርሶና ጠፍቶ የነበረውን  የባህር ሀይል ዘርፍ እንዴት በቅርብ ጊዜ ሊያስጀምረው እንዳሰበ ግልጽ አይደለም።

የሰው ሀይል ማሟላትን የመሳሰሉ ተግዳሮቶችም ብዙ ናቸው። እንደ ማሪ ታይም ህግ ባለሙያው ከሆነ መንግስት አሁን እያለው ባለው ደረጃ የባህር ሀይል ሊኖረው የሚችለው ከጀርባ ከፍተኛ የገንዘብና የፖለቲካ ጉልበት ያለው ሀገር ከደገፈውና ዕቅዱም ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የምዕራባውያን ይሁንታ ካለበት ብቻ ነው ብለው ያምናሉ። ይህ አይነቱ ዕቅድ ደግሞ ኢትዮጵያውያንንም ሆነ ሌሎችን ለግርምት የሚዳርግ የአንድ ማለዳ ስበር ዜና መሆኑ አይቀርም።
[ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/Kl_vfiXYQzE