ዋዜማ ራዲዮ-በቅርብ ቀን በፓርላማ አባላት ፊት አራት የሳተላይት የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን እስከመዝጋት የሚደርስ እርምጃ ለመውስድ የዛቱትን የብሮድካስት ባለስልጣን ዘርዓይ አስገዶም አስተያየት ተከትሎ ኢቢ ኤስ ቴሌቭዥን ጉዳዩን በውይይት ለመፍታት እየጣረ መሆኑን ገልጿል።

የኢቢኤስ ቴሌቭዥን መስራችና ሀላፊ አቶ ነብዩ ያሬድ ለዋዜማ እንደተናገሩት በመንግስት በኩል የተነሱትን የባለቤትነትና የውጪ ሀገር የስራ ፈቃድ ማቅረብን በተመለከተ ባለፉት ወራት ውይይት ሲካሄድ ቆይቷል።
የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ባለቤትነት በተመለከት ኢቢኤስ ቴሌቭዥን ባለቤትነቱን ወደ ኢትዮጵያውያን ለማዞር የሚቻልበትን መንገድ እየመረመረ መሆኑን አቶ ነብዩ አስረድተዋል።
መንግስት ዘርፉን ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ክፍት እንዲያደርግ ፍላጎት አለን ያሉት አቶ ነብዩ የህግ ማሻሻያ እንዲደረግ ለማግባባት እየሞከሩ መሆኑንም ይናገራሉ።
የኢቢኤስ ቴሌቭዥን በሀገርቤትም ሆነ በውጪ ሀገር ሙሉ ህጋዊ ስውነት ያለው ተቋም ሲሆን በሀገር ቤት የሚሰሩ አጋር ፕሮግራሞችን የሚቀበለው መሰረቱን አዲስ አበባ ባደረገ ህጋዊ የማስታወቂያ ድርጅት በኩል መሆኑንና ማናቸውንም ህጋዊ መስፈሮትች አሟልቶ እየሰራ መቆየቱን አቶ ነብዩ ይገልፃሉ።
አሁን መንግስት ያነሳቸውን ችግሮች በፍጥነት እልባት ለመስጠት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
የብሮድካስት ባለስልጣን ኢቢኤስ፣ ቃና ፣ ናሁና ኤል ቲቪ የተባሉ የሳተላይት የአማርኛ ስርጭቶች የኢትዮጵያን የህግ መስፈርት ስላላሟሉ እንዲዘጉ የህዝብና የፓርላማ አባላትን ትብብር ጠይቋል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ የድምፅ ዘገባችንን ከታች ይመልከቱ።

https://youtu.be/DQiIGtLFSeg